1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የንጹሕ ዉኃ አቅርቦት ጥያቄ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 13 2008

የዓለም የዉኃ ቀን መታሰብ ከጀመረ ዘንድሮ 24ኛ ዓመቱን ያዘ። የተመድ ዕለቱ እንዲታሰብ የወሰነዉ ሁሉም ስለዉኃ ተነጋግሮግ ለዉጥ የሚያመጣ ርምጃ እንዲወሰድ ግፊት ለማድረግ ነዉ። ባለፉት 15 ዓመታት በመንግሥታቱ ድርጅት በተቀረጹት የልማት ግቦች አማካኝነት በተለይ ንጹሕ ዉኃን የማዳረሱ ጥረት ለዉጥ ያመጣባቸዉ አካባቢዎች መኖራቸዉ ይነገራል።

https://p.dw.com/p/1IHm4
GMF13 Klick13106 Klick13 Bildergalerie Indien
ምስል Erolina Rodrigues

የንጹሕ ዉኃ አቅርቦት ጥያቄ

የዓለም የጤና ድርጅት ንጹሕ ዉኃ ማግኘት ማለት ከዉኃ ወለድ በሽታዎች ስጋት መዳን ነዉ ይላል። ዉኃ ዓለማችን ከተሸከመቻቸዉ የተፈጥሮ ሃብቶች የሚበረክተዉ ቢሆንም የአያያዝ ጉድለቱ እንዳለ ሆኖ ያለዉም ንጹሕ ዉኃ ለሁሉም መዳረስ አለመቻሉ ዛሬም መነጋገሪያ እንዲሆን አድርጎታል።

በዩኒሴፍ ኢትዮጵያ የዉኃ አቅርቦትና የንጽሕና አጠባበቅ መርሃግብር ኃላፊ ዶክተር ሳሙኤል ጎድፍሬ ኢትዮጵያ የንጹሕ ዉኃ አቅርቦት በሚያሳየዉ መሻሻል አበረታች መሆኑን ይናገራሉ።

ምንም እንኳን በአምዓቱ የልማት እቅድ መሠረት ንጽሕናዉ የተጠበቀ የመጠጥ ዉኃ ለማዳረስ ጥረት ቢደረግም አሁንም ቢሆን አብዛኛዉ ሕዝብ ዉኃ ለማግኘት ረዥም መንገድ በመጓዝ የወንዝ እና የምንጭ ዉኃን እንደሚጠቀምም ዶክተር ጎድፍሬ ያስረዳሉ።

Symbolbild Wasserknappheit in Asien
ምስል AFP/Getty Images

እንዲህ ያለዉን የዉኃ እጥረት እና የንጹሕ ዉኃ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ዩኒሴፍ ሌሎችም እንዲሳተፉበት በመጋበዝ የጀመረዉ እንቅስቃሴ መኖሩን በጽሁፍ ባሰራጨዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቅሷል። ዩኒሴፍ ከአጋሮቹ ጋር በመተባበር ፕሮጀክት ቀርጾ፤ እስከመጪዉ አራት ዓመት ድረስ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ንጹሕ ዉኃ እንዲያገኝ ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ ይገልጻል።

የአየር ንብረት ለዉጥ የዝናብ መታጣትን ብቻ አይደለም የሚያስከትለዉ። ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እና የተዛባ አመጣጥም ሌላዉ መገለጫዉ ነዉ። ሲያሻዉ ደግሞ ከሚገመተዉ በላይ ሊዘንብ ይችላል።

ዩኒሴፍ በመላዉ ዓለም ንጹሕ ዉኃ ለሁሉም እንዳይዳረስ እንቅፋት ከሆኑት ነገሮች አንዱ የጽዳት አጠባበቅ ጉድለት መሆኑን ያመለክታል። 2,4 ቢሊየን ሰዎች በመላዉ ዓለም ተገቢዉ የመጸዳጃ ቤት የመጠቀም እድሉም ሆነ አቅሙ የላቸዉም። በባህር ላይ እንደተገኘ የሚጣለዉ ቆሻሻና በካይ ኬሚካልም ሌላዉ የችግሩ መንስኤ መሆኑን ስለዉኃ ምንጮች ንጽሕና መጠበቅ የሚሟገቱ ወገኖች ደጋግመዉ ያሳስባሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ