1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአለም እግር ኳስ ግጥሚያ

ዓርብ፣ ሐምሌ 2 2002

ጥንት የዳች ነጭ ሰፋሪዎችን ያከበረች-ያነሰረችዉ ደቡብ አፍሪቃ-ዘመኖቹን ዳቾች የአለም ዋንጫ ክብርን ታጎናፅፍ-ይሆን።መልሱ----እሁድ እንጠብቅ።

https://p.dw.com/p/OFCN
ቪያ(ስጳኝ) እና ማቲዛሰን (ኔዘርላናድ)ምስል AP/DW-Montage

09 08 10

ለአንድ ወር ያክል የአብዛኛዉን ዓለም በጣሙን የወጣቱን ትኩረት ስቦ የከረመዉ የዓለም እግር ኳስ የዋንጫ ግጥሚያ የፊታችን እሁድ የስጳኝና የኔዘርላንድስ ቡድናት በሚያደርጉት ግጥሚያ ይጠናቀቃል።ከፍፃሜዉ በፊት ቅዳሜ ጀርመንና ዩራጓይ ለሰወስተኝነት ደረጃ ይጫወታሉ።አፍሪቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀችዉ አስራ-ዘጠናኛዉ የእግር ኳስ ግጥሚያ ብዙ የተጠበቁ ቡድናት እየተሸነፉ የወጡበት ብዙ የማይታወቁ ወይም ያልተጠበቁ ቡድናት ለድል የበቁበት ነበር።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።

የዛሬ አራት አመቱን ፉክክር በሁለተኝነት ደረጃ ያጠናቀቀችዉ ፈረነሳይ ዘንድሮ ሳይረፍድባት ከዉድድሩ ውልቅ አለች።የዛሬ አራት አመት በእግራቸዉም-በአፋቸዉም ብለዉ ፈረንሳዮችን አሸንፈዉ ዋንጫ የወሰዱት ጣሊያኖች ዘንድሮ-አንዱም አልሆነላቸዉም።በጊዜ-ፈረንሳዮችን ተከተሉ።

ኢንግላዶችም የዘመናዊዉን እግር ኳስ ጥበብ ሕግ የመፍጠር-ማዳበራቸዉን ያክል ከአለም ዋንጫ እንደራቁ የቆዩበትን ብዙ ዘመን በአራት አመት ገፉት-ዘንድሮ።ጀርመን ነበር ተስፋቸዉን ያቀጨጨዉ። በብዙ ዘመን ታሪካቸዉ ለዋንጫዉ ግጥሚያ ቀርበዉ የማያዉቁት ዳቾች ወይም ኔዘርላንዶች የአለም ዋንጫን በመዉሰድ የአለም ሪኮርድን የጨበጡትን ብራዚሎችን ሲረቱ በርግጥ-የኳስ ድቡልብልነትን ማማኻኛ ከመናገር ባለፍ-የተባለ አልነበረም።

ደቡብ አፍሪቃ ነጭ ስታዉቅ ከዳቾች ነበር የጀመረችዉ።እስከ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር 1994 ጥቁሮቹን በግፍ እየረገጠ ይገዛ የነበረዉ የአፓርታይድ ስርዓት መሠረቱም እኒያ ዳቾች ነበሩ።የዳች ሠፋሪዎች መጀመሪያ የረገጧት-የኬፕ ታዉን ነዋሪ ግን ትናንት ዛሬ አይደለም-ሲል ነዉ የሰበተዉ።

Fußball, WM 2006, WM Bilder des Tages, Zitterpartie, 03.07.2006
የጀርመን ደጋፊምስል AP

ባለፈዉ ማክሰኞ የኔዘርላንድስ ቡድን ዩራጋይን ሲገጥም-የከተማዉ ሕዝብ ብርቱካናማ ሸሚዝ-ባንዲራ አጥልቆ-ወይ እያዉለበለበ ዳቾችን ይደግፍ ነበር።አሸነፉ።ሰወስት-ለሁለት።አመስተርዳም። ዘ-ሔግ ጤሱ።ኬፕ ታዉንም ጨፈረች።ቡድኑ በርግጥ ኮራ-ራፋኤል ፋን ዴር ፋአት

«በጣም ነዉ የኮራነዉ።ዛሬ አንድ ሌላ ከባድ ጨዋታ ነበር።ግን ታገልን። ከዚሕም በተጨማሪ ትንሽ እድለኞችም ነበርን።በመጨረሻም በጣም ደስተኞች ነን።»

የጋና ጥቁር ኮኮቦች ጥቂት ተከራክረዉ ነበር።ግን ሻኪራ ተራዉ የአፍሪቃ ነዉ ብትልም-ከማስተናገድ ባለፍ--ለአፍሪቃ እንደ እስከ ዘንድሮዉ ሁሉ ዘንድሮም ከያዉ በገሌ-ብዙም አልተሻለም።ሰርቦች ጠጠር-ጋናዎች ጠንከር ብለዉበት የነበረዉ የጀርመን ቡድን-ኢንግላንድን አራት ለ አንድ፥ አርጀቲናን አራት ለዜሮ ሲሸኝ ዋንጫ በርሊን ገባች አሰኝቶ ነበር።የስጳኝ ቡድን ጉድ አደረገዉ።ሮብ በርሊን-ኩም አለች።ማድሪድ ባንፃሩ።ሰወስተኝነቱ ግን ቅዳሜ ይለያል።አብዛኛዉ የጀርመን ኳስ አፍቃሪ ለቅዳሜዉ ጨዋታ ብዙም ጉጉት ያለዉ አይመስልም።ተባባሪ አሰልጣኝ ሐንስ-ዲተር ፍሊክ ግን እሱንስ ቢሆን---አይነት ይላል።

«ዛሬ በቅጡ አርፈን እና ዳግም ተደራጅተን ለትንሹ የፍፃሜ ግጥሚያ መዘጋጀት አለብን። ሰወስተኛነትም ጥሩ ደረጃና ትልቅ ግብ ይመስለኛል።እና በመጨረሻም ጥሩዉ የአለም እግር ኳስ የዋንጫ ግጥሚያ ፍፃሜ ይሆናል።»

WM Pokal
ወዴት ይሄድ ይሆንምስል picture alliance/augenklick

ታሪክ-እና ትዝታ ሲቀር።ጥንት የዳች ነጭ ሰፋሪዎችን ያከበረች-ያነሰረችዉ ደቡብ አፍሪቃ-ዘመኖቹን ዳቾች የአለም ዋንጫ ክብርን ታጎናፅፍ-ይሆን።መልሱ----እሁድ እንጠብቅ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለስ