የአልክሆል መጠጥ ማስታወቂያ ገደብ

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:36 ደቂቃ
04.12.2018

ብርቅዬ የዱር እንስሳት ስያሜን ያገኙት መጠጦች ትውልዱን በራዥ ናቸው

ቴሌቪዥናችሁን ስከፍቱት፣ ሬድዮናችሁን ስታደምጡ ዝግጅቱን ስፖንሰር ያደረገ ተብሎ ሲነገር የቢራ አምራቾችን ማስታወቂያ መስማት የተለመደ የዕለት ገጠመኝ ነው።

የማስታወቂያው የሰአት ማስተካከያ ሊደረግ የታሰበው ትክክለኛ ውሳኔ ነው ይላሉ DW በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የቢጂአይ ኢትዮጵያ የገበያ ጉዳይ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢሳያስ አደራ።  ሆኖም ግን በቴሌቪዝንና በሬዲዮ ፕሮግራሞችን የሚሰሩ ይበልጥ ሊቸገሩ ይችላሉም ባይ ናቸው። 
ከአንድ አመት በፊት  መንግሥት በንግዱ ዘርፍ ላይ የተሰማሩትን አነጋግሮ እንደነበር ጠቅሰው ሆኖም በውይይቱ ላይ የተነሳው ሀሳብ ሊተገበር የማይችል ነበር ይላሉ። እንደኃላፊነት ውሳኔው ትክክል መሆኑን የሚናገሩት አቶ ኢሳያስ በቀጣይ በምን መንገድ የማስታወቂያ ሥራውን ማስኬድ አለብን የሚለውን ድርጅታቸው እንደሚወስንም ተናግረዋል።
``የስፖርት፣ የመዝናኛ እና የሙዚቃ ፕሮግራም ቢራ ማስታወቂያ ነው የሚደግፋቸው ከነሱ ቦታ ሆኖ ሲታይ ሊከብድ ይችላል።``
ከ10 በመቶ በታች የአልኮል መጠን ያለዉ ለገበያ የሚያቀረቡ ማንኛውም የኩባንያዎች ምርት በመገናኛ ብዙሀን ማስተዋወቅ የሚቻለው ከምሽቱ ሦስት ሰዓት እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት መሆን እንዳለበት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አቶ አሚር አማን በትዊተር ገጻቸው አመልክተዋል። 
በመገናኛ ብዙሃን የሚተላለፉ የአልኮል ማስታወቂያዎችንና የስፖንሰሮችን የሚያስተዋውቁበት መንገድ ሕፃናትና ወጣቶች የአልኮል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያበረታቱና ኃላፊነት የጎደላቸው ናቸው በማለት የሚተቹት የሁለት ልጆች አባት የሆኑት አቶ መላኩ ናቸው። 
ቴሌቪዥናችሁን ስከፍቱት፣ ሬድዮናችሁን ስታደምጡ ዝግጅቱን ስፖንሰር ያደረገ ተብሎ ሲነገር የቢራ አምራቾችን ማስታወቂያ መስማት የተለመደ የዕለት ገጠመኝ እንደሆነም ያብራራሉ፡፡ እንደ እሳቸው እምነት በኢትዮጵያ ብርቅዬ የዱር እንስሳት ስም የተሰየሙት ቢራዎች በሕጻናት ላይ ተጽእኖ እየፈጠሩ ነው። 
``የአልኮል መጠጥ ማስራወቂያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ለከት የላቸውም ነበር ማለት ይቻላል። በማንኛውም ሰዓት በየትኛውም ጊዜ የዕድሜ ገደብ ሳያደርጉ ይተላለፉ የነበሩት።``

የስፖርት ቦታዎች በአልኮል ማስታዎቂያዎች እና በቢራ አምራች ድርጅቶች ስፖንሰር እንደሚደረጉ የሚናገረው ደግሞ የስፖርት ጋዜጠኛው ሰኢድ ኪያር ነው፡፡ በአንድ ወገን የሀገሪቱን የእግር ኳስ ለማሳደግ ሲሰራ በሌላ በኩል  ሕፃናት እና ወጣቶች የአልክሆል መጠጥ ሰለባ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑንም አፅንዖት ይሰጣል። እናም በማስታወቂያ አቀራረብ ረገድ የተደረሰው ውሳኔ ዘግይቷል የሚል አስተያየት አለው፡፡ ስፖርት እና ማስታወቂያዎችን አስመልክቶም የአቶ ይድነቃቸው ተሰማን ለዓለም የተረፈ ጠንካራ ውሳኔ እንዲህ ያስታውሳል ሰኢድ። ``ብዙ ትውልድ ካበላሽ በሃላ ህፃናት ታዳጊዎች ችግር ከደረሰባቸው በሃላ ነው የመጣው። ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ የሚገኝ ትርፍ ለሀገርም ለግለሰብም አይጠቅምም። ``የኢካሽ ፕሮሞሽን ባለቤት አቶ ካሣሁን አሰፋም የሰአት ገደቡ አግባብ መሆኑን ቢያምኑበትም እንደሌሎች ሃገራት ለሕጻናት የሚተላለፉ የመገናኛ ብዙሀን ጣቢያዎችን የመለየት ነገር ቢኖር እና በሚከለከልበት ሰዓትም መተላለፍ ቢችል የሚል ሀሳብ አላቸው። ``እንደሌሎች ሀገራት ልጆች ሊያዩትና ሊሰሙት የሚገቡ መገናኛ ብዙሀን የመለየት ነገር ማድረግ ቢኖርና በሚከለከለው ሰዓት መናገር የሚችልበት ዕድል ቢኖር።``
ከአልክሆል መጠጦች በተጨማሪ የሲጋራ ማሸጊያ ከ70 በመቶ ላይ ማስጠንቀቂያዎችን ያካተቱ ምስሎች እና ባለ ሙሉ ቀለም ፎቶዎችን የያዘ መሆን እንደሚኖርበት በደንቡ ተካቷል። ከዚህም ሌላ በሥራ ቦታ፣ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች፣ በሕዝብ መጓጓዣ እና የጋራ መጠቀሚያ ስፍራዎች ትንባሆን ወይም የትንባሆ ምርቶችን ማጨስ ወይም መጠቀም እንደሚያግድም ተገልጿል። 

ነጃት ኢብራሂም 

ሸዋዬ ለገሠ

ተከታተሉን