1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሱዳን ቀዉስና መዘዙ

ሰኞ፣ የካቲት 18 2011

አል በሽር ከሊቢያ፣ከኢትዮጵያ (የተለያዩ መንግስታት)፣ ከግብፅ፣ ከዩጋንዳ፣ ከኤርትራ፣ ከቻድ፣ ኋላ ደግሞ ከደቡብ ሱዳን ከሁሉም በላይ ከዩናይትድ ስቴትስና ከዓረብ ሐገራት የተቃጣባቸዉን ሴራ በጥበብ፣በሻጥርም፣የየጠላቶቻቸዉን ጠላት በመደገፍም ተራ በተራ አክሽፈዋል።

https://p.dw.com/p/3E4te
Sudan | Protest
ምስል Getty Images/AFP/A. Shalzy

የሱዳን ቀዉስና መዘዙ

ሰኔ 1989 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) የጠቅላይ ሚንስትር ሳዲቅ አል መሒዲ መንግሥትን በመፈንቅለ ባስወገዱ ማግሥት ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግገዉ ነበር።በአስርኛ ዓመቱ ሐሰን አልቱራቢን ከአፈ-ጉባኤነት ካስወገዱ በኋላ ሠፊዋን አፍሪቃዊት ሐገር አንድ ዓመት የገዙት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ነበር።ዘንድሮም የተነሳባቸዉን ሕዝባዊ አመፅ ለመደፍለቅ ባለፈዉ ቅዳሜ የአስቸኳይ  አዋጅ ደነገጉ።ፕሬዝደንት ዑመር ሐሰን አልበሽር።የሰላሳ ዘመን አገዛዛቸዉን ለመቀጠል ይረዳቸዉ ይሆን? የአል-በሽር የአገዝዝ ስልት መነሻ፣ የሱዳን ቀዉስ ማጣቀሻ፣ አካባቢያዊ ተፅዕኖዉ መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁን ቆዩ።

የሱዳን የብሔራዊ የደሕንነትና የመረጃ አገልግሎት (NISS በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ) ባለፈዉ ቅዳሜ የበተናት መረጃ ለካርቱም ገዢ ደጋፊዎች አስደንጋጭ፣በገዢዎቹ ላይ ላመፀዉ ህዝብ አስደሳች፣ ለተቃዋሚ ፖለቲከኞች ደግሞ አማላይ ነበረች።«ፕሬዝደንቱ ሥልጣን ይለቃሉ» ትላለች መረጃዋ።

አብዛኞቹ ነባር መገናኛ ዘዴዎች የመረጃዉን ሐሰት-ትክክለኝነት ለማረጋገጥ ሲባትሉ፣ አዛዥ አዛዥ የሌለባቸዉ የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች መረጃዉን እንደ ዜና ሲያራግቡት አረፈዱ።ቀትር ግድም ቀዳሚዉ መረጃ «ፕሬዝደንቱ ስልጣን አይለቁም ግን በመጪዉ ምርጫ አይወዳደሩም» በሚል ዓይነት አዲስ መረጃ ተለወጠ።

ኢትዮጵያዊዉ የአፍሪቃ የፖለቲካ አጥኚ ፕሮፌሰር መድሕኔ ታደሰ እንደሚሉት የአልበሽርን የሥልጣን መሠረት አጥብቀዉ የቋጠሩት ሁለት ወፍራም ገመዶች አሉ።አንዱ የስለላዉ መስሪያ ቤት ነዉ።ተቃዉሞዉም አላባራም።የሰዉዬዉ ስልጣንም እንዲሁ።ሱዳናዊዉ  ባለፈዉ ቅዳሜ ጠንካራዉ የስለላ መስሪያ ቤት ባሰራጫቸዉ መረጃዎች እዉነት-ሐሰትነት ሲሟጋት ሰዉዬዉ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ አሉ።«የሚከተለዉን መዘርዘር እፈልጋለሁ።ሀ) በመላዉ ሱዳን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጓል።ለ) ብሔራዊዉ መንግስት (ካቢኔዉ) ተሽሯል።መ) የክፍለ-ግዛቶች አስተዳደሪዎች ተሽረዋል።እዚሕ የተነጋገርንበትን በሙሉ ገቢራዊ የምናደርግባቸዉን ስልቶች እንወስናል።»

ዉሳኔዉ ብዙ አልዘገየም።አዲስ ካቢኔ ሰየሙ።ለየክፍለ-ግዛት አዳዲስ አገረ-ገዢዎች ሰየሙ።ብዙዎቹ ተሿሚዎች ፕሬፌሰር መድሕኔ የአልበሽር ስልጣን መሠረት የሚሉት የስለላዉና የጦር ኃይሉ ባልደረቦች ናቸዉ።ሹም ሽሩ የሕዝቡን ጥያቄ የሚመልስ አይደለም።አል-በሽር ግን ሹም ሽሩን ሲያጠናቅቁ ሰላሳ ዓመት ለገዟት ሱዳን አዲስ ታሪክ በረቀ አሉ።«ፈጣሪ ይሕን ዕድል ስለሰጠን እናመሰግነዋለን።ዛሬ ደግሞ በሱዳን ታሪክ ዉስጥ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ።»

Sudan Omar al-Bashir ARCHIV
ምስል Reuters/M. Nureldin Abdallah

የአል-በሽር ዉዳሴ መንግስታቸዉ በሚቆጣጠራቸዉ መገናኛ ዘዴዎች ከካርቱም ሲንቆረቆረ የካርቱም መንትያ ከተማ እዱሩማን በተቃዉሞ ሠልፈኛ ተጥለቅልቃ ነበር።ሠልፈኛዉ ይድረስ ለፕሬዝደንቱ ባለዉ መልዕክቱ «አላማችን ሥርዓቱን ማፍረስ ነዉ» ብሏል።«እንችላለንም።»

የሱዳን ሕዝብ አምባገን መሪዎቹን ከስልጣን ለማስወገድ ባደባባይ ሲሰለፍ የዘንድሮዉ የመጀመሪያዉ አይደለም።በ1964 «የጥቅምት  አብዮት» በተባለዉ የአደባባይ ሠልፍ የጄኔራል ኢብራሒም አቡድን ወታደራዊ መንግስት ከስልጣን አስወግዷል።በ1985 ሱዳንን ያጥለቀለቀዉ ሕዝባዊ አመፅም የጄኔራል ጃዓፈር አኑሜሪ መንግስትን አሽቀጥሮ ጥሏል።በድል ያሳረጉትን የቀድሞ ሕዝባዊ አመፆች ለአዲሱ አመፅ መሠረት፣ለአመፀኛዉ ወጣት ድፍረት አብነት እንደሆኑ ሁሉ፣ ፕሮፌሰር መድሕኔ እንደሚሉት ለአልበሽርም ረቂቅ ሥልት አስተማሪዎች ናቸዉ።

በርግጥም አል በሽር ከሊቢያ፣ከኢትዮጵያ (የተለያዩ መንግስታት)፣ ከግብፅ፣ ከዩጋንዳ፣ ከኤርትራ፣ ከቻድ፣ ኋላ ደግሞ ከደቡብ ሱዳን ከሁሉም በላይ ከዩናይትድ ስቴትስና ከዓረብ ሐገራት የተቃጣባቸዉን ሴራ በጥበብ፣በሻጥርም፣የየጠላቶቻቸዉን ጠላት በመደገፍም ተራ በተራ አክሽፈዋል።

ከዉስጥም አልቱራቢን የመሰሉ የአክራሪ ሙስሊሞችም፣የሙሕራንም፣ የአንድ የአረብ መንግስታትም ድጋፍ የነበሯቸዉን ኃይላት እያሽመደመዱ ጥለዋል።በ2013 የተቀሰቀሰባቸዉን ሕዝባዊ አመፅም በቀላሉ ደፍልቀዉታል።እና ያቺን ሰፊ፣ የደጎች ሐገር ሰላሳ ዓመት ገዝተዋል።ዕድሜያቸዉም ገፍቷል።ሰባ አምስት ዓመት።

ከእንግዲሕም ስልጣናቸዉን ለማረዘም በሚወስዱት እርምጃ እስካሁን የተገዟቸዉን ዜጎቻቸዉን ከሚያስገድሉ «ለምን በክብር አይለቁም» እያሉ የሚጠይቁ ታዛቢዎች ብዙ ናቸዉ።ፕሮፌሰር መድሕኔ ግን አልበሽር  የኬንያዉን ሞይ ወይም የኢትዮጵያዊዉን ሐይለማርያም አይደሉም ይላሉ።

ሽግግሩ ችግር ዉስጥ ይወድቃል ማለት የሕዝቡ አመፅ፣ የፀጥታ አስከባሪዉ እርምጃም ይከፋል ማለት ነዉ።እስካሁን ተቃዉሞ ሰልፈኛዉን ለመበተን ፀጥታ አስከባሪዎች በከፈቱት ተኩስ ሐምሳ ሰዉ መገደሉ ተዘግቧል።የቆሰለና የታሰረዉን የቆጠረዉ የለም።አልበሽር ባለፈዉ ቅዳሜ የደነገጉት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደግሞ ፀጥታ አስከባሪዉ በሠልፈኛዉ ላይ እስካሁን ከወሰደዉ የበለጠ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ ሕጋዊ ከለላ ይሰጠዋል።

Deutschland Sudanesen Protest vor UN Gebäude in Bonn
ምስል DW/J. Saad

የአስቸኳይ ጊዜ  አዋጁ አንድ ዓመት ይቆያል።ሱዳንን የሚያብጠዉ ፖለቲካዊ ቀዉስ የሚቆይበትን ጊዜ ማወቅ ቀርቶ መገመትም ከባድ ነዉ።የሰፊይቱ ሐገር ቀዉስ ብሶ ከቀጠለ ግን ዳፋዉ ለብዙ ሐገራት መትረፉ አይቀርም።እንደገና ፕሮፌሰር መድሕኔ።

ሱዳን ከአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የቆዳ ስፋት ስድት በመቶዉን ትሸፍናለች።ግብፅን፣ቀይ ባሕርን፣ ኤርትራን፣ ኢትዮጵያን፣ ደቡብ ሱዳንን፣ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክን፣ ቻድንና ሊቢያን ታዋስናለች።ሰባት ሐገር አንድ ባሕር።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ፣የኤርትራ፣ የደቡብ ሱዳን፣ ስደተኞችን ታስተናግዳለች።ኢትዮጵያና ሱዳን  የመሐመድ ወርዲ ሰበርታ፣ የሰይድ ኸሊፋ ወይም የጥላሁን ገሰሰ«እንደምናችሁ»፣ የሁሉም ከያኒያን «አኽዋን አኽዋን---» ብቻ አይደለም የሚያስተሳስራቸዉ።

ከአፄ ኃይለ ስላሴ እስከ ዐብይ አሕመድ የተፈራረቁ ኢትዮጵያዉያን መሪዎች ሲቆጡም፣ሲደሱትም፣ በየጠላቶቻቸዉ ላይ ሲዶሉትም ወደ ማካርቱም የማያማትሩበት ጊዜ የለም።ኤርትራዉያንም ሆኑ ኢትዮጵያዉን ፖለቲከኞች ከአፄ ኃይለ ስላሴ እስከ ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ከመለስ ዜናዊ እስከ ሌንጮ ለታ ሲሸሹም፣ ሲያምፁም፣ ነፃ ሊያወጡ ሲዋጉም፣ ዐባይን ሲገድቡም ካርቱምን «ሙጥኝ» ብለዉ ነዉ።ኢትዮጵያዉያንና ኤርትራዉያን በሳሕራ በረሐ ንዳድ ነደዉ፣የሜድትራንያን ዉኃ ጠልቀዉ፣ ወይም በበደዊኖች ተተልትለዉ ሞቱም-ዳኑ፣ አዉሮጳ ገቡም-ባሕር መሸጋገሪያቸዉ ሱዳን ናት።

Sudan Omar al-Bashir ARCHIV
ምስል picture-alliance/Photoshot/M. Khidir

ያቺ ሰፊ የየዋሆች ሐገር ሶማሊያን፣ የመንን ወይም ሊቢያን ሆነች ማለት መዘዙ ለኢትዮጵያም ተመዞ የሚያልቅ ዓይነት አይሆንም።ፕሮፌሰር መድሕኒ ይስማማሉ።

የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ከ2013 ጀምሮ የገጠሙትን ጦርነት ለማስቆም አዲስ አበባ ዉስጥ በተደጋጋሚ የሠላም ዉል ተፈራርመዋል።እስካሁን በአንጻራዊነት ገቢር ያደረጉትን ግን ባለፈዉ መስከረም ካርቱም ላይ የተፈራረሙትን ነዉ።የማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ ተፋላሚ ኃይላት ሠላም ለማዉረድ ቻድ፣ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ቤልጂግና ፈረንሳይ ሳይቀር ተደራድረዋል።14 አማፂ ቡድናትና መንግሥት የመጨረሻዉን ስምምነት የፈረሙትን ግን ካርቱም ዉስጥ በተከታታይ ከተደራደሩ በኋላ ነዉ።ካርቱሞች እንዴትና በማን ይዳኙ ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ