1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአመድ ጉምና የበረራ ቀዉስ

ሰኞ፣ ሚያዝያ 11 2002

ከሁለት መቶ አመት በፊት ብዙ ምድሯን የገለባበጠዉ እሳተ ጎመራ-የአዉሮጳን አየር በክሎት ነበር።እንደ ዘንድሮ ግን ድፍን አለምን ያወከበት ዘመን የለም።አለም እንዲሕ አይነት ይረግመዉ፥ ያወግዝ፥ ይወጋዉ የማይቻለዉ ግን ደግሞ አለምን ያልወጋ ሰዉ-ያልገደለበት ጠላት አጋጥሞት አያዉቅም

https://p.dw.com/p/N0Pj
የአመዱ ጉምምስል AP

እሳቸዉ አይስላንዳዊ ናቸዉ።ገበሬ።

«መናገር ያቅተኛል።ይሕ በዉነቱ በጣም መጥፎ ጊዜ ነዉ።»

መጥፎዉ ጊዜ አዉሮጳ ለመድረስ ጊዜ አላጠፋም።

«የበረራዎቹ አስተማማኝነት፥ የንግድ አዉሮፕላኖች አደጋ እንደማይገጥማቸዉ ማረጋገጪያ እስኪገኝ ድረስ በረራ አይደረግም።»

የብሪታንያ የበረራ ደሕንነት ቃል አቀባይ-ሐሙስ።አዛዉንቱና ባለቤታቸዉ ሐሙስ ስቶክሆልም ለመግባት ነበር እቅዳቸዉ።ፍራክፈርት አዉሮፕላን ማረፊያ አደሩ።አርብን ሊደግሙ ሆነ።ተናደዱ። ጠየቁም።

«እዚሕ እንዴት እንደተኛን ታዉቃለሕ?»

ጊዜዉ ለተራዉ ገበሬ-ለተራዉ መንገደኛ ለትላልቆቹ መሪዎችም እኩል መጥፎ ሆነ።ከግዙፎቹ የአየር መንገድ፣ የአስጎብኚ፣ የሆቴል ኩባንዮች እኩል ባለታክሲ፣ ፖስተኛ፣ የፅዳት ሠራተኛዉም አከሰረ።የአመድ ጉም-ጉድ ሥላደረገዉ አለም ጉድ እያነሳን ላፍታ ጉድ እንበል።አብራችሁኝ ቆዩ።

ሲዊድናዊዉ አዛዉንት የሐገራቸዉን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በአካል-ባያቋቸዉ በቴሌቪዥን በርግጥ አያጧቸዉም።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ካርል ቢልት ግን እኛ አዛዉንት በዚያ ሐሙስ ያሉበትን ሁኔታ-ሥፍራን ቀርቶ ማንነታቸዉን የሚያዉቁበት ምክንያት፥ አጋጣሚም የለም።የኑሮ ሥልጣን ሩቅ ለሩቆቹ ግን ያንድ ሐገሮቹ ዜጎች፣ የዚያን ቀን የነበሩባቸዉ ሐገራትም እንደ ሥልጣን ኑሯቸዉ ሁሉ የሩቅ ለሩቆች ናቸዉ።ጀርመንና ዩናይትድ ስቴትስ።

እቅዳቸዉ ግን አንድ ነዉ።-ሐሙስ መብረር።የሚበሩበትም ወደ አንድ ከተማ ነዉ።ስቶክሆልም። ዩናይትድ ስቴትስን ሲጎበኙ የሰነበቱት የጀርንዋ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ወደ በርሊን የሚበሩትም የዚያን ቀን ነበር።ከለደን-ወደ ስዊድን የሚጓዙት ወይዘሮ-ምናልባት ሜርክልን፣ቢልድትን በስም-ምስል ያዉቋቸዉ ይሆናል።ሁለቱ ባለሥልጣናት፣ አዛዉቱም እሷን-የሚያዉቁበት፣ እሷ አዛዉንቱን የምታዉቅበት አጋጣሚ ግን ጨርሶ የለም።

ለንደን-ቀትር አለፍ ብሏል።ቤተሰባቸዉን አስከትለዉ ማለዳ ሒትሮ አዉሮፕላን ማረፊያ የደረሱት ወይዘሮ-ደክሟቸዋል።መቀመጫ ፍለጋ የመንገደኞቹን ባሕር ይቀዝፋሉ።አዛዉንቱ ባለቤታቸዉን አስከትለዉ ፍራንክፈርት አዉሮፕላን ጣቢያ ደረሱ።ጣቢያዉ በሰዉ ተጨናንቋል።

ካሊፎርኒያ ነጋ።የሜርክል ቀጠሮዎች። አፍቃኒስታን ሥለተገደሉ ወታደሮቻቸዉ-በርሊን ላይ የሚሉት አለ። እሁድ በተለይ ኖርድ-ራይን ቬስት ፋሊያ ክፍለ-ግዛት በሚደረገዉ ወሳኝ አካባቢያዊ ምርጫ ፓርቲያቸዉ እንዲያሸንፍ-እስከ ቅዳሜ ብዙ ሊሉ ሊያደርጉ አቅደዋል። እሁድ ዎርሶ-ለቅሶ ይደርሳሉ።እሁዱኑ ማታ ከኢጣሊያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ሲልቪዮ ቤርሎስኮኒ ጋር ሐኖፈር ላይ ከአዉሮጳ ትልቁን የኢንዱስትሪ ትርኢት ይከፍታሉ።ሌላ-ሌላም ብዙ።

Vulkan / Frankfurt / Flughafen / Island
በረንዳም አልጋ ነዉምስል AP

ብቻ የአዉሮጳን ሰማይ የጀቦነዉ አመድ እስኪለይለት ብለዉ ወደ በርሊን ሊያደርጉት የነበረዉን ጉዞ ሰረዙ።ቢልት ግን እንቢኝ አሉ።ወደ ስቶክሆልም የሚደረገዉ በረራ ቢዘጋም በለንደን አሳብረዉ ሐገራቸዉ ለመግባት ወሰኑ።ጉዞ ወደ ለንደን።ደረሱ።ወደ ሲዊድን ግን በረራ የለም።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ናቸዉ።እንደ ወይዘሮዋ እና እንደ ብዙ ብጤዎቻቸዉ አዉሮፕላን ማረፊያ መተፋፋግ የለባቸዉም።ሆቴል መቆየቱንም አልፈለጉትም።ከቤልጅግ ወደ ሲዊድን ለመብረር ከለንደን በባቡር ብራስልስ ገቡ።ብራስልስ ሲደርሱ ወደ ሰሜን አዉሮጳ የሚደረገዉ በረራ ተሠርዞ ጠበቃቸዉ።

አጋጣሚዉን ሚንስትሩ-ይፅፉ ያዙ።

ወይዘሮዋ፣ ቤተሰቦቻቸዉና በአስር ሺሕ የሚገመቱ ብጤዎቻቸዉ ሂትሮ፣ አዛዉንቱ ባለቤታቸዉና ብዙ ሺሕ መሰሎቻቸዉ ፍራክፈርት እንተኮራመቱ ሐሙስ-መሽቶ አርብ ነጋ።ሴትዮዋ ብርድም፣ እንቅልፍ -ተስፋ ማጣትም አቆራምዷቸዋል።አዘኑም።

«የሆነዉን ነገሩንና በረራችን መሰረዙን አስታወቁን።አስራ-ሁለት ሰአት ተኩል ገደማ (ጧት) ግን ፈትሸዉን አስገብተዉን ነበር።ከዚያ በሕዋላ ግን ምንም የሆነ ነገር የለም።እንደገና በረራዉ መሠረዙን ነገሩን።ምናልባት ነገ ትበራላችሁ አሉን።ምንም የምናዉቀዉ ነገር የለም።ያዉ እዚሁ ቆይተን ደግሞ የሚሆነዉን እናያለን።»

አዛዉንቱ ተናደዋል።ግን ከለንደን ብጤያቸዉ የተሻለ አንድ ተስፋ አላቸዉ።ሲዉድ ተስፋ-አማራጭ አያጣም።

«አዉሮፕላን ከእንግዲሕ ምንም አማራጭ አይሆንም።»

እንደ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉ ሌላ አማራጭ አማተሩ።ባቡር ወይም መኪና።

አይስላንዳዊዉ ወጣት ገበሬ ዮሐንስ ጊሰርሰን የፀደይ በጋዉን ፍካት የማየት፣ ፍካት-ሙቀቱ አረንጓዴ በሚያልብሰዉ መስክ ከፈርስ በጎቹ ጋር የመራወጥን ያክል የሚያስደስተዉ ጊዜ-ነገር፥ ጠቀም ያለ ገቢ የሚያገኝበት ሥራ-አጋጣሚም የለም።ኔዘርላንድስ የሚኖረዉ ሶማሊያዊዉ ስደተኛ አሊም (እዉነተኛ ስም አይደለም) የአዉሮጳዉ አየር ሞቅ-ደመቅ ሲል ቀለል-ዘና ይላል።ሸጦ-አትርፎ የድጎማ ገቢዉን የሚያዳጉስበት፣ ቅሞ የሚመረቅንበት ጫት ከኬንያ ሲደርሰዉ ደግሞ-ነብሱ በሐሴት ትወራጫለች።

ፀደዩ በርግጥ መጣ።መስኩም ለመለመ።ጊሰርሰን ተደሰተ።ዓሊም እንዲሁ።ገበሬዉ እና ስደተኛዉ ነጋዴ በያሉበት ሲፍነድቁ የጊሰርሰን መንደር እሳተገሞራም ይንፍቀፈቅበት ገባ።የአፍቃኒስታን ጦርነት፣ የፀረ-ኑክሌር ጉባኤ፣ የፖላንድ መሪዎች እልቂት፣ የቻይና የመሬት መንቀጥቀጥ ለጊሰርሰን ምንም ወይም በጣም የሩቅ ችግር ነዉ።

የሚንፈቀፈቀዉ እሳተጎሞራ የሚተፋዉ የንዳጅ-ክሳይ አመድ የሚወደዉን አረንጓዴ መስክ ቡልማ ሜዳ ሲያደርገዉ ግን ልቡ ተሰበረ።እሱ ከስምንት መቶ ብጤዎቹ ጋር አሰተማማኝ ከተባለ ሠፈር-ሲዘጋበት፣ ክረሙትን ከጋጣ ያልወጡ ፈርስ በጎቹ ዳግም ሲከረቸምባቸዉ ዘመኑን አማረረ።

«መናገር ያቅተኛል።ይሕ በእዉነቱ መጥፎ ጊዜ ነዉ።አሁን ፀደይ ነዉ።መስኩ የሚለመልበት ወቅት ነበር።እንግዲሕ እድለኞች ከሆንን ዝናብ ጥሎ አመዱን ያጥበዉ ይሆናል።»

ጊሰርሰንን ብዙ የማያስጨንቀዉ ጦርነት፣ ጉባኤ፣ የአዉሮፕላን፣ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ፣ ጊሰርሰንና ወገኖቹን ያስጨነቀዉ-አደጋም ብዙ የሚያስጨንቅ-የወገኖቹ ጭንቀት ላለበት ዓሊ የሚያስጨንቅ አይደለም።ሐሙስ ደግሞ ስሜቱንም-ኪሱንም በደስታ የሚሞላበት ነገር ደርሷለታል። የባለሥልጣኖቹ ዉጣ ዉረድ፣ የመንገደኞች መጉላላት፣ የኩባንዮች ክስረት እያሰላሰለ የገቢ-ሚርቃና ፍሰሐዉን የሚበክልበት ምክንያት የለም።ረሐ ነዉ።

አርብ።የፍራንክፈርቱ አዛዉንት የለንደኗ ወይዘሮ-በያሉበት ናቸዉ።የሲዊድኑ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ግን ይፃፋሉ፥ ይደዉላሉ፥ከቤልጅግ ጀርመን፥ ከጀርመን ዴንማርክ እያሉ ከዴንማርክ እያሉ በባቡር በመኪናም ወደ ስቶክሆልም ይጓዛሉም።መራሔተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክልም ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ ከዚያ በላይ መቆየት አልቻሉም።ረጅሙን ጉዞ አንድ አሉ።

መጀመሪያ ጀርመንን አልፈዉ ሊዝቡን ገቡ።ፓርቱጋል።የፖርቱጋሉ ፕሬዝዳት አኒባል ካቫኮ ሲልቫ ግን ሜርክልን መቀበል አይችልም።ፕሬዝዳንት ከብዙ ባለሥልጣኖቻቸዉ ጋር ከፕሬግ ወደ ሐገራቸዉ መመለሻ አጥተዉ ጊዜ ያሰላሉ፥ እንደ ብዙዉ አለም የባለሙያ ትንታኔ-ያያሉ ያደምጣሉ። የአይሳላንዳዊዲዉ የሥነ-እብን ተመራማሪ ሬይነር በድፋርሰንና ብጤዎጫቸዉ የሚሰጡት ትንታኔ ደግሞ ለአብዛኛዉ አለም ተስፋ አስቆራጭ ነዉ።

«ሁኔታዉ ከእንግዲሕም ለዕለታት፥ ለሳምንታት ምናልባትም ለወራት በዚሁ አይነት ሊቀጥል ይችላል።መላዉ አዉሮጳ ይነካል።ከአዉሮጳ አልፎ እንደ ንፋሱ ጥንካሬና አቅጣጫ ሰሜን አሜሪካም ይታወክ ይሆናል።አመዱ አሁን ባለዉ ጥንካሬዉ ከቀጠለ ደግሞ እጅግ በበዛ አካባቢ እየአየር ትራንስፖርት ይታወካል።»

ብሪታንያዊዉ መንገደኛ ሪያነን ቶማስ አርብ-ኒዮርክ አዉሮፓላን ማረፊያ ደረሱ።«የኬኔዲ አዉሮፕላን ማረፊያ የስደተኞች መንደር መስሏል።» አሉ።የስቶክሆልም። የኦስሎ፥ የሔልሲንኪ፥ የፍራንክ ፈርት፥ የለንደን፥ የበርሊን፥ የፓሪስ፥ የሮም፥ የብራስልስ መንገደኞች ከሐሙስ ጀምሮ-የቶማስ እጣ ደርሷቸዋል።የቶኪዮ፥ የኒዊ ደልሒ፥ የሲንጋፑር፥ የካላላፑርም፥ የጃካርታ አዉሮፕላን ማረፊያዎችም ከኒዮርክ ብዙ አይለዩም።

ቅዳሜ-የትንሺቱ አዉሮጳዊት ደሴት ጉደኛ አመድ አስተጋብኦቶ ከአዲስ አበባ እስከ ካይሮ፥ ከ ጁሐንስ በርግ እስከ ናይሮቢም ያስገመግም ገባ።የአዉሮፕላን ኩባንያዮች በየቀኑ ሁለት መቶ ሚሊዮን ዶላር እየከሰሩ ነዉ።በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሠራተኞች ለጊዜዉ ከሥራ ታገዱ።አሊም አዘነ።አዉሮፕላን የለም።ጃት-መጅሮ።ደስታ-ረሐም መጅሮ።የገበሬ ጊሰርሰን ተስፋ ያደረገዉ ዝናምም የለም።ደስታም እንዲሁ ሩቅ ነዉ።

አዛዉንቱ፥ ወይዘሮዋ፥ በመቶ ሺሕ የሚቆጠረዉ ሌላዉ መንደገደኛም እንደተጨናነቀ-በየ አዉሮፕላን ማረፊያ-ሆቴል በረንዳዉ እንደታጨቀ ነዉ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ካርል ቢልት ግን ከዴንማርክ ሽቅብ ወደ ሰሜን-ይገሰግሳሉ።ሜርክልም ከኢጣሊያ አግድም ወደ ምዕራብ ያዘግማሉ።ቢልት ደረሱ።

Merkel macht wegen Aschewolke Zwischenstopp in Rom
ሜርክል-ከሊዝበን ሮምምስል picture-alliance/dpa

ሜርክል ግን በኢጣሊያዎቹ የፍሎሬንስ እና የቦሰን ከተሞች መሐል የሚጓዙበት አዉቶብስ ጎማ ፈነዳባቸዉ።ቢሆን ቦሰን ገብተዉ አደሩ።እሁድ አዉሮጳ ነጋ።ፖላንድ ከሳምንት በፊት በአዉሮፕላን አደጋ የሞቱባትን ፕሬዝዳንቷንና ባለቤታቸዉን ለመሰናበት ታድማለች።ማክሰኞ ዕለት እነ-ሜርክልን እነ-ቢልትን ዋሽግተን ላይ የሰበሰቡት ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ እና ከነ ሜርክል ጋር ከተሰበሰቡት የሐምሳ ሐገራት መሪ-ባለሥልጣናት ብዙዎቹ እሁድ ዎርሶ ለመድረስ ቀጠሮ ነበራቸዉ።ብዙዎቹ መሪዎች በአዎሮፕላን አደጋ የሞተን ለመሰናበት ላዉሮፕላን አደጋ መጋለጥ አልፈለጉም።ቀሩ።

ሜርክል ግን ቢፈልጉ እንኳን አይችሉም ነበር።የአዎቶብሳቸዉ ጎማ ተቀይሮ ቦሰን ማደር ግን አላቃታቸዉም።ሜርክል ከቦሰን ወደ ጀርመን ከማቅናታቸዉ በፊት ምኞት-ተስፋቸዉን ሌሎችም ጭምር መሆኑን ገለጡ።

«ሌላዉ (ወደ ኋላ የቀረዉ) የልኡካን ቡድናችንም እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ።አዉሮጳ እና በመላዉ አለም ወደ የሐገራቸዉ የሚሔዱበትን ጊዜ የሚጠብቁት ሰዎች በሙሉ በቅርቡ ወደየቤታቸዉ እንዲገቡም እመኛለሁ።»

ፖላንድ ሲያለቅስ ሜርክል ጉዞ ወደ ጀርመን።ፖላንዶች መሪያቸዉን ተሰናበቱ።ሜርክልም እሁዱኑ በርሊን ገቡ።ሰኞ-እሁድ ማታ በሜርክል ምትክ የጀርመኑ በቤርሎስኮኒ ፋንታ የኢጣሊያኑ የኢኮኖሚ ሚንስትሮች የከፈቱትን የሐኑፈር የኢንዱትሪን-ሜርክል ጎበኙ።አዲስ ሳምንት-አሮጌ ተስፋ

የሰሜን አትላንቲኳ- ደሴት ትንሽ ናት።ከአንድ መቶ ሺሕ ስኪዮር ኪሎ ሜትር።ነዋሪዋ የአዲስ አባባን የከፍተኛ አምስት ሕዝብን እንኳን አያክልም።ሰወስት መቶ ሺሕ።እሳተ ጎመራ ነዉ-የፈጠራት። እሳተ ጎመራ ተለይቷት አያዉቅም።ከሁለት መቶ አመት በፊት ብዙ ምድሯን የገለባበጠዉ እሳተ ጎመራ-የአዉሮጳን አየር በክሎት ነበር።እንደ ዘንድሮ ግን ድፍን አለምን ያወከበት ዘመን የለም።አለም እንዲሕ አይነት ይረግመዉ፥ ያወግዝ፥ ይወጋዉ የማይቻለዉ ግን ደግሞ አለምን ያልወጋ ሰዉ-ያልገደለበት ጠላት አጋጥሞት አያዉቅም።ጉድ ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

Dw,Agencies

ነጋሽ መሐመድ ነኝ

አርያም ተክሌ