የአማራጭ የኖቤል ተሸላሚዋ ኢትዮጵያዊት

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:05
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
14:05 ደቂቃ
29.09.2017

«ለውጥ ማምጣት የማይፈራ ትውልድ ማፍራት እፈልጋለሁ።» የትነበርሽ ንጉሤ

የአካል ጉዳተኞችን ሁኔታ ለማሻሻል፣ የሴቶች እና ልጃገረዶችን መብት ለማስከበር፣ አካል ጉዳተኞችን በትምህርቱ እና በሌላውም ዘርፍ የማያገል አካታች ሥርዓት ለመፍጠር ያደረጉት ያልተቆጠበ ጥረታቸው ለራይት ላይቭሊሁድ አዋርድ አብቅቷቸዋል፣ ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሤ።


የሕግ ባለሙያዋ  ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሤ ለተለያዩ ችግሮች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መፍትሔዎችን በማፈላለግ የተሻለች ዓለም ለመፈጠር ለሰሩ ትጉህ ግለሰቦች እና ድርጅቶች የሚሰጠው ራይት ላይቭሊሁድ አዋርድ የተባለው አማራጭ የኖቤል ሽልማት የዘንድሮ ተሸላሚ መሆናቸው ሰሞኑን በይፋ መገለጹ የሚታወስ ነው። ስቶክሆልም የሚገኘው ሽልማቱን የሚሰጠው ድርጅት እንዳስታወቀው፣  የ35 ዓመቷ ወይዘሮ የትነበርሽ  ከጎርጎሪዮሳዊው 1980 ዓም ወዲህ ለሚሰጠው ሽልማት የበቁት የአካል ጉዳተኞችን ሁኔታ ለማሻሻል፣ የሴቶች እና ልጃገረዶችን መብት ለማስከበር፣ አካል ጉዳተኞች በተምህርቱ እና በሌላውም ዘርፍ የማያገል አካታች ሥርዓት ለመፍጠር ባደረጉት ያልተቆጠበ ጥረታቸው ነው። ይኸው ጥረታቸው በዚህ ታዋቂ ሽልማት ዓለም አቀፍ እውቅና ማግኘቱ  ለርሳቸው ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸውልናል። 

Äthiopien Gewinnerin des alternativen Nobelpreises, Yetnebersh Nigussie


ወይዘሮ የትነበርሽ ለአካል ጉዳተኞች እኩልነት መታገል ከጀመሩ ብዙ ዓመታት ሆኗቸዋል። በተወለዱበት እና ባደጉበታት ኢትዮጵያ ውስጥ አካል ጉዳተኝነት በብዙዎች ዘንድ እንደ እርግማን እና እንደ መጥፎ ነገር የሚታየው፣ በዚህም የተነሳ አካል ጉዳተኞች የመገለል እጣ እንደሚደርስባቸው ይታወቃል። ሆኖም፣ ለአካል ጉዳተኞች መብት በተሟገቱባቸው ባለፉት ዓመታት በህብረተ ሰቡ ዘንድ  ስለአካል ጉዳት ያለው ግንዛቤ፣ በተለይ መገለሉ እንደቀነሰ፣ ባጠቃላይ አንዳንድ ለውጥ እንደተደረገ አመልክተዋል።

በአምስት ዓመታቸው በማጅራት ገትር ሕመም ምክንያት የዓይናቸውን ብርሀን ባጡበት ጊዜ በተለይ ለዓይነ ስውራን በተከፈተ የመጀመሪያ ደረጃ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብተው ትምህርታቸውን የመከታተልት እድል ማግኘታቸው የዕድላቸውን በር እንደከፈተላቸው እና አካል ጉዳተኝነት ሊያስከትላቸው ከሚችሉ ችግሮች ነፃ እንዳወጣቸው ዛሬ የሚናገሩት ወይዘሮ የትነበርሽ  በተለይ አካል ጉዳተኞች የሚያጋጥማቸውን ችግር ሊያሸንፉ የሚችሉት በትምህርት ነው ብለው ስለሚያምኑ ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው ይሰራሉ።

Äthiopien Gewinnerin des alternativen Nobelpreises, Yetnebersh Nigussie

የሕግ ባለሙያ እና የመብት ተሟጋች ወይዘሮ የትነበርሽ የአማራጭ ኖቤል ተሸላሚ ሆኖ መመረጥ ያስገኘላቸው ዓለም  አቀፍ እውቅና ከፍተኛ  ኃላፊነትንም መያዙን አስታውቀዋል። ይህንኑ ኃላፊነታቸውን ለመወጣትም ወደፊት ለውጥ ማምጣት የማይፈራ ትውልድ ለማፍራት እና በተለይ በሴት አካል ጉዳተኞች እና ሴት ሕፃናት ትምህርት ላይ በይበልጥ አትኩረው የመስራት እቅድ እንዳላቸው ነግረውናል። 

ወይዘሮ የትነበርሽ የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት አባል የነበሩት ስዊድናዊው ጀርመናዊ ጋዜጠኛው ካርል ቮልማር ያኮብ ፎን ኡክስኪውል የመሰረቱት 315,000 ዩሮ የያዘውን በጎርጎሪዮሳዊው የፊታችን ታህሳስ አንድ የሚሰጠውን የዘንድሮውን ራይት ላይቭሊሁድ አዋርድ ወይም አማራጭ የኖቤል ሽልማትን ከህንዳዊ ጠበቃ ኮሊን ጎንሳልቬስ እና ከአዘርባጃኗ ጋዜጠኛ ኻድጃ ኢስማይሎቫ ከ ጋር  ይጋራሉ። አሜሪካዊው ጠበቃ ሮበርት ቢለት ደግሞ የክብር ተሸላሚ ሆነዋል። 

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ