1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል በሰሞኑ ግጭት 15 ሰዎች ሞተዋል አለ

ቅዳሜ፣ ጥር 26 2010

ላለፉት ሁለት ሳምንታት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች 15 ሰዎች መሞታቸውን የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት (ካቢኔ) አስታወቀ፡፡ ካቢኔው ዛሬ ባወጣው መግለጫ በወልዲያ ከተማ በጥምቀት ማግስት በተቀሰቀሰው ግጭት “የተፈጸመው የሰው ግድያ በምንም መስፈርት ተቀባይነት የለውም” ብሏል፡፡ 

https://p.dw.com/p/2s4WG
Äthiopien Ausnahmezustand
ምስል James Jeffrey

የክልሉ ካቢኔ በዛሬው መግለጫው “ምንም እንኳ አንዳንድ ቡድኖች የሃይማኖቱ ስርዓት በማይፈቅደው መልኩ ተንኳሽ ተግባራት መፈጸማቸው ስህተት መሆኑን ብናምንም፤ መነሻው ምንም ይሁን ምን የተፈጸመው የሰው ግድያም ሆነ በዚህ ስነ ስርዓት ላይ የተደረገ ተኩስ በምንም መስፈርት ተቀባይነት የለውም” ሲል የወልዲያውን ድርጊት አውግዟል፡፡ ከሰሞኑ መርሳ እና ቆቦ ከተሞችን ጨምሮ በሰሜን ወሎ ዞን ውስጥ ባሉ የተለያዩ አካባቢዎች ለተቀሰቀሰው ተቃውሞ መነሻ የሆነው በወልዲያ ከተማ ጥር 12 የተከሰተው ሁነት ነበር፡፡ በጥምቀት ማግስት በሚከበረው የቃና ዘገሊላ ሃይማኖታዊ በዓልን እያከበሩ በነበሩ የወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች እና የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት ሰባት ሰዎች መሞታቸውን የዞኑ ፖሊስ ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

ካቢኔው “ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓት በሚካሄድበት እና ክብረ በዓል በሚከበርበት ወቅትና ቦታ ጸጥታ ያደፈረሱም ይሁን በስነ-ስርዓቱ ታዳሚዎች ላይ ጥይት የተኮሱ፣ ሰው የገደሉ፣ ልዩ ልዩ ጉዳት ያደረሱ አካላት ጉዳዩ በዝርዝር ተጣርቶ በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ይደረጋል” ሲል በመግለጫው አትቷል፡፡ መግለጫው በወልዲያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ቦታዎችም “የሰው ህይወት ያጠፉ፣ አካል ያጎደሉ እና ሃብት፣ ንብረት ያወደሙ ማናቸውንም ወገኖች በክልሉ በተወከሉ ሙያተኞች እና በአመራሮች ደረጃ እያጣራ” በመረጃ ላይ ተመስርቶ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አትቷል፡፡ 

12.06.2013 DW Online Karten Basis Äthiopien Englisch

“በወልዲያ ከተማ የደረሰውን ጉዳት መቃወምና በመሰለው መንገድ ማውገዝ ህገ-መንግስታዊ መብት” መሆኑን ያስረገጠው የክልሉ ካቢኔ መግለጫ ሆኖም “አንዳንዶቹ የግጭት አዝማሚያዎች የህዝቦችን ጸንቶ የኖረ አብሮነትንና አንድነትን በሚጎዳ መልኩ የተከሰቱ ናቸው” ብሏል፡፡ በሀብት፣ ንብረት፣ በመንግስታዊ ተቋማት እና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ላይ የደረሰውን ውድመትም “በዚህ ዘመን ሊታዩ ማይገቡ አሳፋሪ ድርጊቶች ናቸው” ሲል ኮንኗቸዋል፡፡ “ይህ ሁሉ ክስተት ግን በምንም መንገድ ቢሆን ግጭቱ የተከሰተባቸውን የአካባቢ ህዝቦች የማይወክል ተግባር ነው” ሲል መግለጫው አክሏል፡፡ 

በሰሜን ወሎ ዞን የተከሰቱት ግጭቶች መሰረታዊ መነሻ ምክንያቶቻቸው “የህብረተሰቡ ዲሞክራሲያዊ እና ህገ-መንግስታዊ ጥያቄዎች እንዲሁም ቅሬታዎችና ብሶቶች መደማመርና ሳይፈቱ መዋል ማደራቸው” መሆኑን የካቢኔው መግለጫ ጠቁሟል፡፡ በወልዲያ እና በአካባቢው የተከሰተው የሰሞኑ ግጭት “በእጅጉ አሳስቦኛል” ያለው የክልሉ ካቢኔ “ለግጭቶቹ መነሻ የሆኑ ቅሬታዎችን እና ጥያቄዎችን ደረጃ በደረጃ ለመመለስ” የክልሉ መንግስት “ከምንጊዜውም በላይ ጥረት እያደረገ እና ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ” እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡    

የአማራ ክልል ካቢኔ በዛሬው መግለጫው በሰሞኑ ግጭቶች ስለሞቱ ሰዎች ብዛት ቢጠቅስም ስለቆሰሉ ሰዎች ያለው ነገር የለም፡፡  መግለጫው ከማቾቹ ውስጥ ሁለቱ የጸጥታ ኃይል አባላት እንደሆኑ ግን ግልጽ አድርጓል፡፡ የወልዲያ፣ የመርሳ እና የቆቦ ነዋሪዎች ሰሞኑን ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በየከተሞቹ በነበረው ግጭት ቢያንስ 22 ሰዎች የሞቱ ሲሆን በርካቶች ቆስለዋል፡፡  

ተስፋለም ወልደየስ
እሸቴ በቀለ