1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማራ ክልል አዲስ ርእሰ መስተዳድር ሹመት መጽደቅ

ሰኞ፣ ሐምሌ 15 2011

የአማራ ክልል ምክር ቤት 13ኛ መደበኛ ጉባዔ የአቶ ተመስገን ጥሩነህን የርእሰ መስተዳድርነት ሹመት ዛሬ በጭብጨባ አፅድቋል። አዲሱ ርእሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ባደረጉት ንግግርም  ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ሰላም መረጋጋት ተናግቶ ቆይቷል ባሉት የአማራ ክልል፣ ሰላምን ለማረጋገጥ መከወን የሚገባው ሳይከናወን መቆየቱን አመልክተዋል።

https://p.dw.com/p/3MXZR
Temesgen Tiruneh Amhara
ምስል DW/A. Mekonnen

አቶ ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር

ከዚህም ሌላ  በሕግ እየተመሩ ስርዓትን በማስፈን የተረጋጋ የፖለቲካ መስተጋብርን እውን በማድረግ ረገድም በክልሉ ቀላል የማይባል ውሱንነት እንደነበርም ተናግረዋል። የወሰን እና የማንነት ጥያቄዎችም በሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ መንገድ መፈታት እንደሚገባቸው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።

የአማራ ዴሞክራሲ ፓርቲ-አዴፓ የርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸው መኮንንን ህልፈት ተከትሎ በቅርቡ አቶ ተመስገን ጥሩነህን እጩ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መምረጡ የሚታወስ ነው። የእጩ ርዕሰ መስተዳድሩን ሹመት ዛሬ የተሰበሰበው የአማራ ክልል ምክር ቤት ሹመቱን በተባበረ ድምፅ አፅድቆታል። ርእሰ መስተዳድሩ ቃለ መሐላ ከፈፀሙ በኋላ ረዘም ያለ ንግግር ያደረጉ ሲሆን ባለፉት ጥቂት ዓመታት በክልሉ ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም ዕጦትና ምክንቱን አንስተዋል። ከወሰንና ከማንነት ጋር በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች ለሕዝቦች መራራቅ እና በጥርጣሬ መተያያ ምክንያቶች እየሆኑ መምጣታቸውን የጠቆሙት አቶ ተመስገን፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እና በጋራ ምክክር እንደሚፈቱ አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር በንግግራቸው ጠቁመዋል።

Temesgen Tiruneh Amhara
ምስል DW/A. Mekonnen

ለሁሉም ችግሮች መነሻ የሰላም እጦት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተመስገን ይህን ችግር ለማስተካከል ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። ለአመራራቸው ውጤታማነት የሴቶችን፣ የወጣቶችን፣ የፀጥታ ኃይሎችን እና የሌሎችም አካላት እገዛም ጠይቀዋል። አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር ለውጥ ያመጣሉ ብለው እንደሚያምኑ አንዳንድ የጉባዔው ተሳታፊዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከዝቅተኛ አመራርነት እሰከ ከፍተኛ አመራርነት የሠሩ እና በቂ የአመራር ልምድ ያላቸው መሪ እንደሆኑ የአዴፓ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ዮሐንስ ቧያለው ተናግረዋል። ዝርዝሩን የባሕር ዳር ዘጋቢያችን ዓለምነው መኮንን ልኮልናል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ተስፋለም ወልደየስ