1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

 የአማራ ወጣቶች ማኅበር አመራርና ደጋፊዎች መታሰር

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 26 2013

የአማራ ወጣቶች ማኅበር «አባሎቼና ደጋፊዎቼ በፖሊስ እየታሰሩብኝ ነው» አለ። ፖሊስ በበኩሉ ሰሞኑን በክልሉ የተደረጉ ሰልፎች ችግር የነበረባቸው ባይሆኑም፤ በባሕር ዳር ከተማ ለሦስተኛ ጊዜ የተደረገውን ስልፍ ወደ አልተገባ አቅጣጫ እንዲሄድ አደረጉ ያላቸውን ተጠርጣሪዎች መያዙን ግን ገልጧል።

https://p.dw.com/p/3sxDG
Äthiopien Bahir Dar | Proteste gegen Ermordung und Vertreibung von ethnischen Amharas
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

4 የማኅበሩ አመራሮ የእስር ትዕዛዝ እንደወጣባቸው ተናግረዋል

የአማራ ወጣቶች ማኅበር «አባሎቼና ደጋፊዎቼ በፖሊስ እየታሰሩብኝ ነው» አለ። ፖሊስ በበኩሉ ሰሞኑን በክልሉ የተደረጉ ሰልፎች ችግር የነበረባቸው ባይሆኑም፤ በባሕር ዳር ከተማ ለሦስተኛ ጊዜ የተደረገውን ስልፍ ወደ አልተገባ አቅጣጫ እንዲሄድ አደረጉ ያላቸውን ተጠርጣሪዎች መያዙን ግን ገልጧል። ሰሞኑን በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች መንግሥትን በብርቱ የሚቃወሙ እና የሚነቅፉ ሰልፎች በተከታታይ ቀናት ተካኺደው ነበር። የተቃውሞ ሰልፈኞቹ የአማራ ተወላጆች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በማንነታቸው ምክንያት እየተገደሉ፤ እየተፈናቀሉና እየተሳደዱ ባለበት ወቅት የክልሉና የፌደራሉ መንግስት ርምጃ አልወሰዱም በሚል  ነበር ተቃውሞዋቸውን ያስተጋቡት። 

የአማራ ተወላጆች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በማንነታቸው ምክንያት እየሞቱ፣ እየተፈናቀሉና እየተሳደዱ ባለበት ወቅት የክለሉና የፌደራሉ መንግስት እርምጃ አልወሰዱም በሚል ባለፈው ሳምንት በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞች መንግስትን የሚነቅፉ ሰልፎች ተካሂደዋል። 

በአብዛኘዎቹ ከተሞች ሰልፎች በሰላም የተጠናቀቁ ሲሆን የአማራ ክልል መንግስት በይፋ የሰልፉን አስተባባሪዎችና ሰልፈኞችን አመስግኗል፡፡ ይሁን እንጂ በባሕር ዳር ለሦስተኛ ቀን በተካሄደውና በፍኖተ-ሰላም ሰልፎች ወደግጭት አምርተው በፍኖተ-ሰላም አንድ የፀጥታ አባል፣ በባሕር ዳር ደግሞ የአንድ ሰልፈኛ ሕይወታቸው አልፏል፣ የአካል ጉዳት ደርሷል፣ ንብረትም ወድሟል፡፡

በተለይ በባሕር ዳር ከተማ ሚያዝያ 14 ቀን፣ 2013 ዓ.ም በባሕር ዳር የተደረገውን ሰልፍ ተከትሎ «አመራሮቼና ደጋፊዎቼ እየታሰሩ ነው» ሲል የአማራ ወጣቶች ማህበር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አመልክቷል፡፡

የቅርንጫፍ ማኅበሩ ሊቀመንበር ወጣት ቴዎድሮስ ጌታቸው ለዶይቼ ቬለ (DW) እንደተናገረው  «በእለቱ ከነበረው  ሰልፍ ጋር በተያያዘ  የማኅበሩ ጸሐፊ ትህትና በላይ (ቲና) ‘እስረኛ ለማስፈታትና የሴቶችን ሰልፍ አስተባብረሻል’ በሚል ታስራለች» ብለዋል፡፡ ከጸሐፊዋ በተጨማሪ አንድ የልዩ ኃይል አባልንና ሌላ የሕግ ባለሞያን ደጋፊዎች ጨምሮ ሌሎች 11 ሰዎች መታሰራቸውን ወጣት ቴዎድሮስ ተናግሯል፡፡ 

እንደ ወጣት ቴዎድሮስ እርሱን ጨምሮ ሌሎች 4 የማህበሩ አመራሮች የእስር ትዕዛዝ እንደወጣባቸው ገልጧል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የባህር ዳር ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ዛሬ በዋለው ችሎት ትህትና በላይንና አስረስ ማረን በ10ሺህ ብርና ሌሎች 3 ተጠርጣሪዎችን በ3ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈቱ፣ አንዱን ደግሞ በነፃ እንዲሰናበት መወሰኑን የአማራ ወጣቶች ማኅበር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ሥራ አስፈፃሚ አባል ኃይለሚካኤል ባየህ ለዶይቼ ቬለ በስልክ ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ከፋለ አንዷለም ግን ሚያዝያ 14/2013 ዓ ም በከተማዋ  የተካሄደውን ሰልፍ ወደአልተፈለገ አቅጣጫ ለመምራት የሞከሩ ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ሰልፉን አስፈላጊ ወዳልሆነ አቅጣጫ ለመምራት ሰልፈኞች መንገድ ዘግተዋል፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቆም አድርገዋል፣ ተቋማትን ለመስበር ሞክረዋል፣ በፀጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል ነው ሉት ረዳት ኮሚሽነሩ፡፡

ሰልፈኞች እስረኛ ለማስፈታት መሞከራቸውን የተናገሩት ኃላፊው በእለቱይነበረውን ህገወጥ እንቅስቃሴ የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉንም ተናግረዋል፡፡
ሚያዝያ 14 ቀን፣ 2013 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ በተደረገው የተቃውሞ  ሰልፍ 30 የፀጥታ ኃይሎችና 4 ሰልፈኞች ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን የባሕር ዳር ከተማ ምክትል ከንቲባ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ ሰሞኑን ለዶይቼ ቬይሌ መናገራቸው ይታወሳል።

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ