1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማርኛ ቋንቋን አጠቃቀም ግድፈት

ሐሙስ፣ ሰኔ 2 2008

« በአማርኛ ቋንቋ ፤ በሥነ ድምፁ ሥነ ምላዱ፤ በዓርፍተ ነገሩ፤ በቃላት አጠቃቀም በጣም በጣም ብዙ ለዉጦች እና ግድፈቶች ናቸዉ ያሉት። «ጋ» እና «ጋርን» እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

https://p.dw.com/p/1J3x7
Argobba – Shonke Dorf Äthiopien
ምስል DW

የአማርኛ ቋንቋን አጠቃቀም ግድፈት


በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሥነ-ልሳን መምህርና በቋንቋ ጥናት ጋዜጠኝነትና የኮሚኒኬሽን ኮሌጅ ዲን ዶክተር ዘላለም ልየዉ፤ የአማርኛ ቋንቋ በመንግሥታት ለዉጥ፤ በሚል ባለፈዉ ሳምንት ባቀረብነዉ መሰናዶ መጨረሻ ላይ የሰጡን አስተያየት ነበር። በኢትዮጵያ በነበሩት የተለያዩ መንግሥታት በሚያራምዱት መርህም ሆነ በወቅቱ በዓለም ላይ በሚታየዉ የኤኮኖሚ፤ የቴክኖሎጂ እንዲሁም የፖለቲካ አካሄድ ለዉጥ ማንኛዉም ቋንቋ ከሌላዉ እንደሚዋስ አዲስ ቃል እንደሚፈጠር፤ እንዲሁም በስፋት ሲነገሩ የነበሩ ቃላቶችም፤ እየመነመኑና እየጠፉ እንደሚሄዱ ባለፈው ሳምንት ዝግጅታችን ላይ የጋበዝናቸዉ ምሁራን አስረድተዋል። እንድያም ሆኖ በአማርኛ ቋንቋ ላይ «ህ» በ«ክ» «ን» በ«ኝ» የመተካቱ ክስተት ምናልባትም በቋንቋዉ ወደኋላ እየሄድን ሳይሆን እንዳልቀረና፤ ጥናት የሚስፈልገዉ ጉዳይ መሆኑን ምሁራኑ አሳስበዋል። በዛሬዉ ዝግጅታችን ደግሞ ፣በቋንቋ እንግዚዘኛን ቀላቅሎ መናገር፤ የዳበረ ቋንቋ እያለ የተቋማትም ሆነ የአነስተኛ ድርጅቶች ሱቆች፤ ሆቴሎች በእንግሊዘኛ ስያሜ መያዛቸዉ እንዴት ይገለፃል፤ በሚሉትና በሌሎች ነጥቦች ላይ ማብራርያ የሚሰጡንን ምሁራን ይዘን እናንተ አድማጮቻችን በዚሁ ርዕስ ላይ በዶይቸ ቬለ የፊስ ቡክ ገፅ ላይ ያስቀመጣችሁትን አስተያየቶች አካተናል።

Landschaft in Äthiopien
ምስል picture alliance/imagestate/Impact Photos


ባለፈዉ ሳምንት ባቀረብነዉ የመጀመርያ ክፍል መሰናዶ በርካታ አድማጮቻችን በአማርኛዉ የፊስቡክ ገፅ ላይ፤ በአማርኛ ቋንቋ ንግግር ላይ የሚታዩትን ግድፈቶች እንዲሁም አዳዲስ ያሏቸዉን ቃላቶችም ሆነ የአነጋገር ዘይቤዎች አካፍለዉናል። ለምሳሌ በ1 ለ 5 አደረጃጀት መሰረት የመጡ ለውጦች ናቸው ፤ ጀርባው ይጠና፤ ሌላ አመለካከት ይዟል፤ የትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማሳካት ፣ ልማታዊው መንግስታችን፤ ለህዳሴያችን፤ አክራሪ ፤ ልማት አደናቃፊ፤ ፅንፈኛ ፤ አሸባሪ፤ ጎራህን ለይ » ሲሉ ያስቀመጡልን አንድ አድማጫችን ናቸዉ። ሌላዉ የፊስ ቡክ ተከታታይ «ቋንቋን ማሻሻል ምን ጉዳት አለው ታካብዳላችሁ እንዴ?» ያሉንም አሉ በጥያቄ፤ ይሄ ታካብዳላችሁ የሚለዉም ቃል ቢሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስፋት የሚሰማ ቃል ሆኗል። ግን የአማርኛ ቋንቋን ከእንግሊዚኛ ጋር ቀላቅሎ መጠቀም ያስፈለገው ቋንቋችን በመቀጨጩ ነዉ የሚሉም አሉ። በርግጥ ይህ ከቋንቋ መቀጨጭ ጋር የተያያዘ ይሆን? በባሕር ዳር ዩንቨርስቲ የዐባይ የባህልና ልማት ጥናትና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉቀን አንዷለም እንደሚሉት ግን ምክንያቱ ሌላ ነዉ።


« ምናልባትም በሌሎች ስላልተገዛንም ሊሆንም ይችላል፤ እንደሌሎቹ የሌሎቹን ቋንቋ እንደትልቅ አድርገን የምናይበት ሁኔታ እዚህ አገር ላይ ይታያል። እንግሊዘኛ ዓለም አቀፋዊ ቋንቋ በመሆኑ ምክንያት፤ ብዙ ሰዎች እንግሊዘኛ ቋንቋ በመናገራቸዉ ሊቅ የሆን ወይም ደግሞ እንደ አዋቂ እንቆጠራለን ብለዉ የሚያስቡ ብዙ ሰዎች አሉ። ይህ በተለይ በፖለቲካዉ አካባቢ ያሉ ሰዎች ይበዛሉ። አንድ አርፍተ ነገር እስከ መጨረሻዉ ድረስ ለመናገር ቀላቅለዉ ይናገራሉ። ይህ ፍፁም ስህተት ነዉ።»
«እኔን የሚያሳዝነኝ ተምረዋል ተብለው ትልቅ ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች የሚያደርጉት ቋንቋን የመደበላለቅ አባዜ ነው። ለምሳሌ አገራችን ውስጥ 85% ገበሬ እንዳለ ይታወቃል። ነገር ግን ግብርናን በተመለከተ የሚደረግ ስብሰባ ላይ አላግባብ የሆኑ የውጭ ቋንቋዎች ሲዥጎደጎዱ እንሰማለን። ስለዚህ ይሄ ችግር የመንግስትን ንዝህላልነትን ነው የሚያመለክተው።» ያሉን ሌላዉ የፊስቡክ ተከታታይ ናቸዉ። እያሳሰበ ያለዉ የአማርኛ አጠቃቀም ፣ እንግሊዘኛን ቀላቅሎ መናገሩ ነው ያሉን፤ በደቡባዊ ጀርመን ባየር ግዛት በሙኒክ ከተማ በሚገኝ ዩንቨርስቲ በምርምር ሥራ ላይ የሚገኙት ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ ናቸው።
« አንዳንድ ግዜ ከመንግሥት አካባቢ በሚነገረዉ ሁኔታ አማርና ሊያድግና አንዳንድ ቃላት ወደ ሕዝቡ መጠቀሚያ ዉስጥ እንዲገቡ የሚደረግበትም ነገር አለ። ይህን በአጠቃላይ ስናይና ሰፋ አድርገን ስንመለከተዉ አማርኛ ተናጋሪዎችን በአራት ልንመድባቸዉ እንችላለን። የመጀመርያዉና በአብዛኛዉ ሰዉ የሚናገረዉ የባላገር ዘየ የምንለዉ በየክፍለ ሃገሩ የሚኖሩ የሚናገሩት ነዉ። ስለዚህ በሸዋ ላይ ያለዉ ዘዬ ከወሎ ይለያል፤ በወሎ ያለዉ ከጎንደር ከጎጃም ይለያል። ስለዚህ በአጠቃላይ በየአካባቢዉ ያሉ ዘየዎችn ስናይ የመጀመርያዉና አብዛናዉ ተናጋሪ ያለበት ይህ ነዉ። በሁለተኛ ደረጃ የአማርኛ ቋንቋ መደበኛ ተናጋሪ የምንለዉ ትምህርት ቀመስ የሆነዉ ሰዉ በከተማ አካባቢና ትምህርት ቀመሱ በአብዛኛዉ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን የሚያዘወትሩት አማርኛ እንደመደበኛ ተናጋሪ ሆኖ የሚወሰድበት ሁኔታ አለ። በሦስተኛ ደረጃ የቤተ-ክህነት ቀመስ አማርኛ የምንለዉ ደግሞ አለ። ይህ ማለት በአብዛናዉ የቤተ/ክህነቱ ምሁራን ፀሐፊዎች በትምህርት ዜርያ ፤ በዩንቨርስቲዎች ዙርያ አንዳንድ ደግሞ በየመስኩ ሞያዊ ቃላትን ስያሚዎችን ለመስጠት የሚጠቀሙት ሁሉ፤ ከቤተ-ክህነት ቀመስ አማርኛ ጋር የተገናኙ ናቸዉ። በዉጭ ሃገር ያሉ ሳይንሳዊ ቃላት ሲመጡ ፍች ለመስጠት በእዉነት የቤተ-ክህነቱ ምሁራን በሰፊዉ ያገለግላሉ።»

Argobba kinder
ምስል DW


በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሥነ-ልሳንና ፊሎጂ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፊሰር ደርብ አዶ፤ እንደሚሉት ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ትክክለኛ ቃላትና የአነጋገር ዘይቤ እንዳልሆኑ እያወቅን ፤ እነዚሁኑ ቃላት ደግመን እንጠቀምበታለን ።
« በተለይ በቋንቋ አጠቃቀም ላይ የመከተል ነገር ያለ ይመስለኛል እንደ ፋሽን። ቋንቋም ፋሽን ያለዉ ይመስለኛል። አንዳንዶቹ ነገሮች፤ መጥፎ ሆነዉ ወይም ትክክለኛ አለመሆናቸዉን እያወቅን፤ መልሰን የምንጠቀምባቸዉ ጊዜ አስፈላጊነቱ አይታየኝምና ትንሽ በቋንቋ አጠቃቀማችን አስተዉሎት ብንጨምር፤ በተለይ ደግሞ በሚዲያ ላይ። የየእለት ንግግራችን ሳንቀላቅል ብንናገር። አንድ ሰዉ እግር ጥሎት ወደ ገጠር ቢሄድ እየቀላቀለ መናገር የለመደ ከሆነ መግባባት ሊያቅተዉ ይችላል።»
ባለፉት ዓመታት በአማርና ቋንቋ ብዙ ለዉጦች ታይተዋል ያሉን ዶክተር ዘላለም ልየዉ፤በበኩላቸዉ፤
«ብዙ ነገር መግለፅም ይቻላል በአማርኛ ቋንቋ ፤ በሥነ ድምፁ ሥነ ምላዱ፤ በዓርፍተ ነገሩ፤ በቃላት አጠቃቀም በጣም በጣም ብዙ ለዉጦች ናቸዉ ያሉት።በጣም በጣም ብዙ ለዉጦች ይታያሉ። ይህንን ዉድቀት ነዉ አይደለም ለማለት ከባድ ነዉ ግን ለዉጦቹ በጣም የሚታዩ ናቸዉ። «ጋ» እና «ጋርን» እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። «ጋ» ማለት በግዕዙ «ዘንድ» ማለት ነዉ ቦታን አመልካች ነዉ «ጋር» ግን አብሮነትን የሚያመለክት ነገር ነዉ። አሁን አሁን ግን በቋንቋ አጠቃቀም ላይ «ጋ» እና «ጋር» ተምታተዉ ጥቅም ላይ ሲዉሉ ይደመጣል።»

Argobba – Shonke Dorf Äthiopien
ምስል DW


እንደ ምሁራኑ ማብራርያ አማርኛዉ ከግዕዝ ቢወስድ ምንም አልነበረም፤ «ክ» እና «ኝ» የመሳሰሉት አላስፈላጊ ቅጥያ ፊደሎችን መጨመሩ ትልቅ ስህተት ነዉና ሊጤንበት ይገባል ሲሉ ምሁራኑ በሰጡን አስተያየት የምንስማማ ይመስለናል። እንደ ስርጭት ክፍላችን የፊስ ቡክ ተከታታዮች አስተያየት ደግሞ «ዳይሪክቶሪት ዳይሬክተር» «ትራንስፎርሜሽን» የመተካካት «ፓሊሲ» አይመቹንም፤ ከአማርኛ ጋር ሲሰሙ ለጆሮ ይጎረብጣሉና እንግሊዘኛ ቃላቱ አቻ የአማርና ቃላት ይፈለግላቸዉ ሲሉ በሰጡን አስተያየት፤ ሰፊ ቃለ ምልልስ የሰጡንን የቋንቋ ምሁራንን በዶይቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉዉን መሰናዶ የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።


አዜብ ታደሰ


ኂሩት መለሰ