1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በጀርመን

ሐሙስ፣ የካቲት 15 2010

በጀርመን ሐገር ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ሲሰጥ ዘንድሮ 99 ዓመቱን ይዞአል። በጀርመን ሐገር ከሂዮብ ሉዶልፍ እና ከአባ ጎርጎሪዮስ ጊዜ ጀምሮ የመጀመርያዉ ሰዋሰዉ እንደ አዉሮጳዉያን አቆጣጠር በ 1698 ዓ.ም ታትሟል። በመቀጠልም በጋራ የአማርኛ መዝገበ ቃላት አሳትመዋል።

https://p.dw.com/p/2sNBX
99 Jahre Amharisch Unterricht in Hamburg
ምስል Universität Hamburg

ቋንቋዉ በከፍተኛ ተቋም ሲሰጥ 99 ዓመት ሞላዉ።

በሐንቡርግ ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌቲ ገላዬ ከተናገሩት የተወሰደ ነዉ። ባለፈዉ ሳምንት መገባደጃ ላይ በሰሜናዊ ጀርመን የወደ  ከተማ በሆነችዉ ሐምቡርግ ከተማ በሚገኘዉ ዩኒቨርስቲ በእስያ አፍሪቃ ተቋም ወስጥ “የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት አሰጣጥ በጀርመን አገር“ በሚል ርዕስ የሁለት ቀናት ዓዉደ ጥናት ተካሂዶአል። በከፍተኛ ተቋም ደረጃ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት አሰጣጥና የማስተማር ሂደትን በተመለከተ የዘርፉ ባለሞያዎች የተሳተፉበት ዓዉደ ጥናት ሲካሄድ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ እንደሆነም ታዉቋል ። በዓዉደ ጥናቱ ተካፋይ የነበሩ የአማርኛ ቋንቋ ምሁራንን ስለ ዓዉደ ጥናቱ በተለይም ደግሞ በጀርመን ከፍተኛ ተቋማት ስለሚታየዉ የአማርኛ ቋንቋ አሰጣት መረሐ-ግብርና ታሪክ እንቃኛለን።

99 Jahre Amharisch Unterricht in Hamburg
ምስል Universität Hamburg

በጀርመን ሐገር በተለያዩ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት ሲሰጥ ዘንድሮ 99 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ባለፈዉ ሳምንት በሰሚናዊትዋ  የጀርመን ወደብ ከተማ ሐምቡርግ የሚገኘዉ ዩኒቨርስቲ “የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት አሰጣጥ በጀርመን አገር“ በሚል ለሁለት ቀናት ያካሄደዉ ዓዉደ ጥናት ግን ለመጀመርያ ጊዜ እንደነበር  ታዉቋል። ዓዉደ ጥናቱ የአማርኛ ቋንቋ በጀርመን ሐገር በዩኒቨርስቲ ደረጃ በትምህርትነት፤ በምርምር ቋንቋነት፤ በማስተማርያነት መሠጠት ጀመረ፣ የቋንቋዉ ትምህርት አሰጣጡ ያለበት ሁኔታ እንዴት ነዉ? ይህ  ዓዉደ ጥናት በጀርመን ሐገር የመካሄዱ ምክንያት፤ እንዲሁም  ለምንስ አስፈለገ በሚሉ ነጥቦች ላይ አማርኛ ቋንቋ መምህራን እና የሥነ- ልሳን ባለሞያዎች የጥናት ጽሑፎቻቸዉን በማቅረብ መወያየታቸዉን የዓዉደ ጥናቱ አዘጋጅና በሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌቲ ገላዬ ተናግረዋል።

« በዓዉደ ጥናቱ መጀመርያ ሐሙስ ዕለት በቅድምያ ፕሮፊሰር አሌሳንድሮ ባዉሲ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር አድርገዋል። በአሁኑ ጊዜ በአዉሮጳ ደረጃ በጀርመን ደረጃ የአማርኛ እና የግዕዝ ቋንቋ ትምህርትና ጥናት አስፈላጊነት በምርምር በማስተማርም እየጎላ መምጣቱን በደንብ አጠንክረዉ ተናግረዋል። በዚህም መሰረት ከአንጋፋም ከወጣትም ምሁራን ጋርም አብረን በትብብር መነጋገር መወያየት ፤ ምርምር ማድረግ የማስተማር ዘዴና አላማችንን መለዋወጥ የሚል ነበር የተናገሩት። ለምሳሌ ፕሮፌሰር ሉድቪግ ጌርሃርድት የተባሉት የአማርኛ ቋንቋ አሰጣጥ በሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ 99 ዓመት እንደሞላዉ ተናግረዉ፤ ከተጀመረበት ጊዜ  እስከዛሬ ያለዉን ታሪክ ዘርዝረዉ አስረድተዋል። ፕሮፊሰሩ አማርኛ ጠንቅቀዉ ይናገራሉ፤ የሥነ- ልሳን ምሁርም ናቸዉ»

በዚህ ዓዉደ ጥናት ላይ በተለይ ሥነ-ግጥምና ዘፈን ለአማርኛ ቋንቋ አሰጣጥ ግብአት እንደሚሆን የጥናት ጽሑፍ ማቅረቦ ይታወቃል። ስለዚህ አጠር አድርገዉ የሚነግሩን ይኖራል?

«ያቀረብኩት ጥናት በተለይ ምዕራባዉያንን ጀርመናዉያንን አማርኛ ስናስተምር ደረቅ ሰዋሰዉ ብቻ ከማስተማር ፤ ሥነ-ጥበቡንም፤ ዜማዉንም፤ ግጥሙንም ፤ አጫጭር ፊልሞችንም ጨምረን  ብናስተምር ተማሪዎች በደስታና በተመስጦ ጥሩ አድርገዉ ጥሩ ይማሩልናል። ወደ ኢትዮጵያም ሄደዉ የሐገሪቱን ባህል ትዉፊቱን የግጥሙን እና የዜማዉን ባህል የሙዚቃ መሳሪያዉን ጭምር  አዉቀዉ  ራሳቸዉም እያዜሙ በቀላሉ በደስታ ቋንቋዉን ይማሩታል  በሚል ሃሳብ ነዉ።»            

99 Jahre Amharisch Unterricht in Hamburg
ምስል Universität Hamburg

የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ከመግባቱ በፊት የሁለት ዓመት የሲቪል አገልግሎት ግዴታ ለመወጣት ሥራ ላይ ሳለ ነዉ በጎርጎረሳዊዉ  አቆጣጠር አስራ ዘጠኝ ዘጠናዎቹ መጀመርያ ላይ አፍሪቃን ብሎም ደግሞ ኢትዮጵያን እንደተዋወቃት የገለጸልን የሴማዊ ቋንቋዎች ተመራማሪና አማረኛን አቀላጥፎ የሚናገረዉ ጀርመናዊዉ ዶክተር አንድርያስ  ቬተር አማርኛ ቋንቋን ለረጅም ጊዜ በበርሊን ዩኒቨርስቲ አስተምሮአል። በኢትዮጵያም በተለይ በአርጎባ ቋንቋ ላይ ጥናትን አካሂዶአል።  የሐምቡርጉ ዓዉደ ጥናት ጥሩ እንደነበር የሚገልፀዉ ዶክተር አንድርያስ በጀርመን ሐገር ከፍተኛ ተቋማት የሚሰጠዉ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት እየቀነሰ መምጣቱን ሳይገልፁ አላለፈም።   
«ዓዉደ ጥናቱ ጥሩ ነበር። ለመጀመርያ ጊዜ ስለተዘጋጀም ብዙ ሠዎች ተሰባስበዉ መጥተዉ ነበር። በዓዉደ ጥናቱ ላይ ከተነሱት ኃሳቦች መካከል፤ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በአሁኑ ጊዜ ጀርመን ዉስጥ አንድ ቦታ በሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ ዉስጥ ብቻ መሰጠቱ ነዉ። ሌላዉ  ቋንቋዉን በቀላል የማስተማርያ ዘዴዎች ምን ምን ናቸዉ የሚለዉ ነጥቦችም ነበሩ» 

በጀርመን ሐገር በየት በየት ዩኒቨርስቲዎች ነበር የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የሚሰጠዉ?
«ከሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ ሌላ ከዚህ ቀደም በበርሊን ፍሪ ዩኒቨርስቲ፤ በማይንዝ ዩኒቨርስቲም ለአስር ዓመት ያህል ይኸዉ ቋንቋ ይሰጥ ነበር። ግን በማይንዝ ለዚህ ቋንቋ የተያዘዉ ፕሮጀክት ሲያልቅ በዚህ ዩኒቨርስቲ የማስተማሩን ሂደት መቀጠል አልቻልንም። በበርሊን ዩኒቨርስቲ ፕሮፊሰር ፎግት የሚባሉ የአማርኛ ቋንቋ ባለሞያ እና የሥነ-ልሳን ባለሞያ ነበሩ፤ በአማርኛ ቋንቋ ጥናት በጣም ትኩረት ሰጥተዉ ይሰሩ ነበር። ነገርግን ጡረታ ወጡና የማስተማርያዉ ክፍል ተዘጋ። »     
የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት መረሐ-ግብር የቀነሰበት ምክንያት ምንድን ነዉ ግን?  
«አንደኛ በርሊን የነበሩት ፕሮፊሰር የሴማዊ ቋንቋ ባለሞያ ሆነዉ በአማርኛ ቋንቋ ላይ ነበር ትኩረታቸዉን ያደረጉት። ከሳቸዉ በኋላ የመጡት ግን በሌላ ቋንቋዎች ላይ ትኩረት በመስጠታቸዉ ነዉ የአማርኛዉ ቋንቋ ትምህርት ሊቀር የቻለዉ። ቦታዉ ላይ ያለዉ ሰዉ ስራ ቀይሮ ከሄደ ወይም በጡረታ ምክንያት ቦታዉን ከለቀቀ ሌላ ምሁር ከሌላ ትኩረት ጋር

ስለሚመጣ ነዉ ይህ የአማርኛ ቋንቋ ምርምር ቦታዉን ያጣዉ። ለምሳሌ የሐምቡርግን ብናይ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ቦታዉ ላይ ያለ አንድ የአማርኛ ቋንቋ ምሁር በመኖሩ ቦታዉ ሳይዘጋ ወይም ሳይቀየር ቀርቶአል። በአሁኑ ወቅት ዶክተር ጌቲ ገላዬ ይገኛል። በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የአማርኛ ቋንቋ ጥናት፤ የአፍሪቃ ጥናት በጣም በጣም ጠባብ ቦታ ነዉ ያለዉ። የአሁኖቹ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንቶች በጥናቱ ላይ እንብዛም ትኩረት አይሰጡም» 

 

HafenCity Universität Hamburg 2015
ምስል DW/Zaripova

የአማርኛ ቋንቋን በቀላል ዘዴ ለማስተማር የተለያዩ ነጥቦችን አንስተን ተወያይተናል ሲሉ የገለፁት ዶክተር ጌቲ ገላዬ በበኩላቸዉ በጀርመን ሐገር የአማርኛ ቋንቋ ጥናትና ትምህርት ከጥንት ጊዜ ጀምሮ እንደነበር አስረድተዋል።

« ጀርመን ሐገር ከሂዮብ ሉዶልፍ እና ከአባ ጎርጎሪዮስ ጊዜ ጀምሮ የመጀመርያዉ ሰዋሰዉ እንደ አዉሮጳዉያን አቆጣጠር በ 1698 ዓ.ም ታትመዋል። በመቀጠልም በጋራ የአማርኛ መዝገበ ቃላት አሳትመዋል። ሂዮብ ሉዶልፍ ከእዉቁ የግዕዝና አማርኛ ሊቅ ከአባ ጎርጎርዮስ ነዉ ቋንቋዉን የተማረዉ። ሂዮብ ሉዶልፍ  ከዝያን ጊዜ ጀምሮ ስላሳተመዉ ፤ ሌሎቹ ጀርመኖች እስከ አዉሮጳዉያኑ 1905 ዓ.ም ድረስ በአማርኛ በግዕዝ ቋንቋ ጽሕፈት በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ  ምርምር ያደርጉ ነበር። በአፂ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት በ1905 ዓ,ም እስከ 1907 ዓ.ም ድረስ በዝያን ጊዜ የነበሩት ጀርመናዊዉ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ ቪልሄልም በጠየቁት መሰረት አማርኛ እና ግዕዝ ቋንቋን አለቃ ታየ ገብረማርያም በበርሊን ዩኒቨርስቲ አስተምረዋል። በሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ  የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት አሰጣጥ ቆይቶ ነዉ የተጀመረዉ ። ይኸዉም እንደ አዉሮጳዉያን አቆጣጠር በ 1919 / 20 ዓ.ም የመጀመርያዉ መምህር ወልደማርያም ደስታ የሚባሉ ከአንኮበር የመጡ የአማርኛና የግዕዝ ባለሞያኛቸዉ እስከ 1925 ዓ.ም አማርኛ በዋናነት አልፎ አልፎ ግዕዝም ኦሮምኛንም አስተምረዋል። በሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ ከዝያን ጊዜ ጀምሮ እኔ እስካለሁበት እስካሁን ድረስ ወደ 15 የሚጠጉ ኢትዮጵያን አማርኛን፤ የአማርኛን ሥነ-ጽሑፍ ፤ የአማርኛ ቋንቋን ባሕርያት፤ ባህል ለማስተማር ሞክረዋል። »       

የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በከፍተኛ ተቋም ደረጃ ሲሰጥ ከአዉሮጳዉያን ሐገራት መካከል በጀርመን ከፍተኛ ተቋም የመጀመርያ ነዉ ይባላል፤ እንደዉም በኢትዮጵያ በከፍተኛ ተቋም ደረጃ እንኳ አይሰጥም ነበር፤ የጀርመኑ ከፍተኛ ተቋም ይቀድማል ይባላል።ይህ ምን ያህል እዉነት ነዉ?

« በትምህርት ደረጃ በዩኒቨርስቲ በኢጣልያ ኔፕልስ ዉስጥ ነዉ ለመጀመርያ ጊዜ  ቋንቋዉ ትምህርት መልክ የተሰጠዉ። የመጀመርያዉ የአማርኛ ቋንቋ መምህር ደግሞ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ ይባላሉ። ፕሮፊስር ጋሊና ከሚባሉ ጋር  እዝያ አስተማሪ በነበሩበት ጊዜ ጦቢያ የሚባል ልብወለድ ታሪክ እንደ አዉሮጳዉያን አቆጣጠር በ 1908 ዓ.ም ያሳተሙት፤ በኢትዮጵያዉያን አቆጣጠር በ1900 ዓ.ም ነዉ። የአማርኛ ቋንቋ ትምህርትን በተመለከተ ፈረንሳዉያንም ከጀርመናዉያን ቀደም ብለዉ ነዉ የጀመሩት። በጀርመን በዩኒቨርስቲ  ደረጃ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት የተጀመረዉ መጀመርያ በበርሊን ከ 1905 እስከ 1907 በሐምቡርግ ደግሞ 1919 /20 ዓ.ምጀምሮ ያለምንም ማቋረጥ ትምህርቱ እስካሁን ይሰጣል።»

99 Jahre Amharisch Unterricht in Hamburg
ምስል Universität Hamburg

     
እንግዲህ እንደገለፁልኝ የአማርኛ ቋንቋ ትምህርት በሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ ረዥም ታሪክ ያለዉ ነዉ። ሐምቡርግ ዩኒቨርስቲ ሌላም ታሪክ እንዳለዉ ይነገራል።ይኸዉም  የአፋን ኦሮሞ ቁቤ በዚያዉ በዩኒቨርስቲዉ እንደተወለደ ነዉ የሚነገረዉ ይህንንስ ያዉቃሉ? ለሚለዉ ዶክተር ጌቲ ሰፊ ሰፋ ያለ መልስን ሰጥተዋል።  
እዚሁ ጣብያችን አቅራብያ በሚገኘዉ ኮለኝ ከተማ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት እና በጀርመን መከላከያ ሚኒስቴር የቋንቋዎች ቢሮ ዉስጥ የአማርኛ ቋንቋ ላይ የሚሠሩት እና አንዳንድ ትምህርትን የሚሰጡት አቶ ሰዒድ አሕመድ በዚሁ ዓዉደ ጥናት ላይ ተሳታፊ ነበሩ።  
በወልቂጤ ከተማ ወደ አምስት ዓመት በመኖራቸዉ ጉራጌኛ ቋንቋን የተማሩት እና በጉራጌ ማኅበረሰብ ባህል ቋንቋ ላይ ከፍተኛ ጥናትን ያካሄዱት ሌላዉ የአማርኛ ቋንቋ ተመራማሪ ጀርመናዊዉ ዶክተር ሮኒ ማየር፤ የሐምቡርጉ ዓዉደ ጥናት ተሳታፊ ነበሩ ። ዶክተር ሮኒ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከዶክተር አንድርያስ  ቬተር ጋር ለዓመታት ጥናት አካሂደዋል። በአሁኑ ወቅት በፓሪስ በሚገኘዉ ኢናልኮ ዩኒቨርስቲ የአማርኛ ቋንቋ አስተማሪና የሥነ- ልሳን ተመራማሪ  ናቸዉ።  
ቋንቋ የሠዉ ልጅ የማንነት መገለጫ ነዉ ያሉት የዓዉደ ጥናቱ ዋና አዘጋጅ ዶክተር ጌቲ ገላዬ ከጀርመን ብዙ ነገሮችን መዉሰድ ይገባናል ሲሉ ተናግረዋል።
የአስናቀች ወርቁ፤ የስለሺ ደምሴ ዘፈኖች በሐንቡርግ ዩኒቨርስቲ የአማርኛ ቋንቋ ተማሪዎች የቋንቋ እዉቀታቸዉን ከሚያጎለብቱባቸዉ የማስተማርያ መሳርያዎች  መካከል ዋናዎቹ እንደሆኑ ተመልክቶአል። 

 
ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ። 


አዜብ ታደሰ 
ኂሩት መለሰ