1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካን የበጀት ውዝግብና መዘዙ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 7 2006

የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የሃገሪቱን የበጀት ጣሪያ ከፍ ለማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ትናንት ማታ ካፀደቀ በኋላ ለ16 ቀናት የተዘጉት የተወሰኑ የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዛሬ ሥራ ጀምረዋል ። የሃገሪቱ የበጀት ጣሪያ ከፍ እንዳይል ሲሟገቱ የቆዩት ወግ አጥባቂ ሪፐብሊካኖች ውሳኔውን ሊያስቀሩት ባለመቻላቸው ሽንፈታቸውን አምነዋል ።

https://p.dw.com/p/1A1lb
US Capitol © kuosumo #4526957
US Capitol Hillምስል kuosumo/Fotolia

የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የሃገሪቱን የበጀት ጣሪያ ከፍ ለማድረግ የሚያስችለውን ስምምነት ትናንት ማታ ካፀደቀ በኋላ ለ16 ቀናት በከፊል ተዘግተው የቆዩት የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዛሬ ሥራ ጀምረዋል ። የትናንቱ ውሳኔ በቅርቡ ስራ ላይ ይውላል ተብሎ የሚጠቀበው አዲሱ የጤና ዋስትና ደንብ መሰረታዊ ለውጥ እንዲደረግበት አጥብቀው ይሟገቱ ለነበሩት ወግ አጥባቂ የሪፐብሊካን ፓርቲ እንደራሴዎች እንደ ሽንፈት ተቆጥሯል ። ሂሩት መለሰ
የዩናይትድ ስቴትስ የህግ መወሰኛ ምክር ቤት መጀመሪያ 81 የድጋፍና 18 የተቃውሞ ድምፅ ከሰጠበት በኋላ ሪፐብሊካኖች ወደ ሚያመዝኑበት የህግ መምሪያ ምክር ቤት የተመራው ረቂቅ ውሳኔ እሮብ ማታ በ285 ድጋፍና 144 ተቃውሞ ነው ሊያልፍ የቻለው ። የሃገሪቱን የበጀት ጣሪያ ከፍ ለማድረግ ውሳኔ እንዲሰጥበት የተቀመጠው የጊዜ ገደብ እኩለ ለሊት ከመድረሱ አስቀድሞም የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በፊርማቸው አፅድቀውታል ። የሃገሪቱ የበጀት ጣሪያ ከፍ እንዳይል ሲሟገቱ የቆዩት ወግ አጥባቂ ሪፐብሊካኖች ውሳኔው እንዲዘገይ ቢያደርጉም ከማለፍ ግን ሊያስቀሩት ባለመቻላቸው ሽንፈታቸውን አምነዋል ።
« ጥሩ ትግል አካሂደናል ። ግን አላሸነፍንም »
ሪፐብሊካኑ የህግ መምሪያ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጆን ቦህነር ይህን ሲሉ በህግ መወሰኛ ምክር ቤት የብዙሃኑ ዲሞክራቶች መሪ ሃሪ ሬድ ደግሞ የዓለምን ትኩረት የሳበው የዚህ ውዝግብ ድል አድራጊው ዲሞክራሲ ነው ብለዋል ።


« ዛሬ የመንግስት መሥሪያ ቤቶች እንዲከፈቱና የሃገሪቱም የበጀት ቀውስ እንዲስተካከል ለማድረግ በአሜሪካን ምክር ቤት ሁለቱ ፓርቲዎች የደረሱበትን ታሪካዊ ስምምነት ሁሉም ተመልክቷል ።»
ከፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ የሆነው የበጀት ጉዳዮችን የሚያጠናው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ኮሚቴ አባልና የምጣኔ ሃብት ምሁር ማርክ ጎልድዌይን ግን ሁለቱም ባሉት አይስማሙም ።
« በዚህ ጉዳይ አሸናፊ የለም በርካታ ተሸናፊዎች ግን አሉ ። እግዚአብሔር ይመሰገን የበጀት ቀውሱን በማስቀረት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚከፈቱበትን መንገድ አግኝተናል ። ይህ በእርግጠኝነት የኤኮኖሚው እድገት እንዲሻሻል ያደርጋል ።»
ትናንት ማታ የፀደቀው ህግ በውዝግቡ ምክንያት ተዘግተው የነበሩ የፌደራል መንግሥት መስሪያ ቤቶች እንደ ጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር እስከ ጥር 15 2014 ድረስ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ያስችላል ። መንግሥትም በህጉ መሰረት እስከ የካቲት 7 2014 ድረስ ወይም ከዚያም አንድ ወር ለበለጠ ጊዜ ልትበደር ትችላለች ። ያ ማለት ግን ውዝግቡ ዘላቂ መፍትሄ አገኘ ማለት አይደለም ከዚህ ወሳኝ ግን ጊዜያዊ ውሳኔ በኋላ ተጨማሪ እርምጃዎች መወሰድ ይኖርባቸዋል ። የዲሞክራትና የሪፐብሊካን ፓርቲዎች ተወካዮች የሚገኙበት ኮሚሽን የሃገሪቱን እዳ መቀነስ ያስችላሉ ተብለው በቀረቡ ሃሳቦች ላይ መክሮ በታህሳስ አጋማሽ ውጤቱን ይዞ መቅረብ ይጠበቅበታል ። ጎድዊን እንደሚሉት መፍትሄ ያልተገኘላቸው በርካታ የረዥም ና የአጭር ጊዜ ችግሮች አሉ ።

USA Haushaltsstreit Einigung Kompromiss Harry Reid Senat
ባራክ ኦባማምስል Reuters


« በግብር ከምናገኘው ገቢ በላይ በፍጥነት በመጨመር ላይ ያሉ የጤናና የማህበራዊ ዋስትና መርሃ ግብሮች አሉን ። አንድ ቦታ ላይ ወይ የእነዚህን መርሃ ግብሮች ስፋት መቀነስ አለያም የግብር ገቢያችንን ማሳደግ ወይም ደግሞ ሁለቱም አቀናጅተን ማስኬድ መቻል ይኖርብናል ። »
ምንም እንኳን አሁን የተገኘው መፍትሄ ጊዜያዊ ቢሆንም ሁለቱ ወገኖች መግባባት ላይ መድረሳቸው ለዩናይትድ ስቴትስ ትልቅ እፎይታ ነው ። ሆኖም ውዝግቡ ይህን ያህል ጊዜ መጓተት አልነበረበትም የሚሉ የፖለቲካ ታዛቢዎችም አልጠፉም ። የበጀት ቀውስ ይከተላል የሚለው ለሳምንታት የቀጠለው ስጋት ሰዎች በዩናይትድ ስቴትስ ኤኮኖሚና የዓለም መገበያያ በሆነው በዶላር ዋጋ ላይ ያላቸው እምነት እንዲሸረሸር ማድረጉን CENTER FOR AMERICAN PROGRESS የተባለው የጥናት ተቋም ባልደረባ ማይክል ዌርዝ ተናግረዋል ።
« ይህን መሰሉ ሁኔታ አንዴ ብቻ ሲደርስ በይቅርታ ማለፍ ይቻል ይሆናል ። ሆኖም ወግ አጥባቂ ሪፐብሊካኖች እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሲከቱን በ24 ወራት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው ። ይህ ቀስ በቀስ እንደ ጥሩ አርአያ እየተወሰደ ነው ።

John Boehner
ጆን ቦህነርምስል Reuters

ይህ ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ እንደ ዓለም የፖለቲካ ና የምጣኔ ሃብት መሪነት የተጣለባትን አመኔታ ያናጋል ።»
ለ2 ሳምንት የተወሰኑ የፌደራል መንግስት መሥሪያ ቤቶች መዘጋታቸው አሜሪካንን ተዓማኒነትን ከማሳጣቱም በላይ የ24 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ተጨማሪ ወጪም እንዳስከተለባትም የምጣኔ ሃብt ባለሞያዎች ግምት ያስረዳል ። ይሁንና ዝርዝሩ በይፋ አልተገለፀም ። በዌርዝ አስተያየት ኦባማኬር በመባል የሚጠራው በተለይ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎችን ይጠቅማል የተባለው የጤና ዋስትና መርሃ ግብር ለውጥ ሳይደረግበት የብድር ጣሪያው ከፍ እንዲል መወሰኑ ለወግ አጥባቂዎቹ ሪፐብሊካኖች በተለይም ለ ቲ ፓርቲ አባላት ከባድ ሽንፈት ተደርጎ ተወስዷል ።

Senate Majority Leader Harry Reid of Nev. speaks during a news conference on Capitol Hill in Washington, Tuesday, May 15, 2012, following a political strategy meeting. (Foto:J. Scott Applewhite/AP/dapd)
ሃሪ ሪድምስል AP

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ