1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካኖች ምርጫ ዉዝግብና ሩሲያ

ነጋሽ መሐመድ
ሰኞ፣ ጥር 1 2009

ቀዝቃዛዉ ጦርነት ባበቃበት ወቅት ክሬምሊንና ዋይት ሐዉስን ይቆጣጠሩ የነበሩት ቦሪስ የልትሲንና ቢል ክሊን ጥብቅ ባይባል እንኳ የሚግባቡ ወዳጆች ይመስሉ ነበር።የየልሲን ወራሽ ፑቲንና እና የባለቤታቸዉን መንበር የሚመኙት ወይዘሮ ሒላሪ ክሊንተን ግን ለመጠፋፋት የሚፈላለጉ ጠላቶች ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/2VXFB
Wladimir Putin und Barack Obama am Telefon
ምስል picture-alliance/dpa

የአሜሪካኖች ምርጫ ዉዝግብና ሩሲያ

በትችት-ዉዝግብ ተጀምሮ፤ በበስድብ-ንትርክ ንሮ፤ ባልተጠበቀ አሳዛኝ ዉጤት የተጠናቀቀዉ የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ አሜሪካኖችን ዛሬም እሁለት ገምሶ እያወዛገበ፤ እያወቃቀሰ፤ እያነታረከም ነዉ።የአወቃቃሽ-አነታራኪዉ ምርጫ መዘዝ ሞስኮ ተሻግሮ የሞስኮ-ዋሽግተኖችን ሥር የሰደደ ጠብ ማጋጋሚያ ሰበብም ሆኗል።እሁለት ከተገመሱት የአሜሪካ ፖለቲከኞች ተሰናባቾቹ-ሞስኮን ወንጃይ-አዉጋዥ-ቀጪ፤ መጪ ወይም ሥልጣን ተረካቢዎቹ ዉንጀላ-ዉግዘት-ቅጣቱን ተቃዋሚ ናቸዉ።የፖለቲከኞቹ ሰፊ ልዩነት እራስዋን የዴሞክራሲ ቀንዲል፤የሰብአዊ መብት አርአያ፤የፍትሕ-እክሊል የዓለም መሪ-አስተባባሪ እድርጋ የምትቆጥረዉን ታላቅ ሐገርን ታላቅነት-ከወጥ መርሕ እጥረት ጋር እያላተመዉ ነዉ።ሰበብ-ምክንያት ላፍታ እንቃኛለን።
                            
ከተራዉ ነብስ ወከፍ ጠመንጃ እስከ ጅምላ ጨራሹ ኑክሌር ቦምብ፤ ከባሕር-እስከ ሕዋ መተላለቂያ ጦር መሳሪያ በማምረት-ሌሎችን በማስታጠቅ አቻ የላቸዉም።«ቀዝቃዛ ጦርነት» ባሉት የጠብ፤ዉዝግብ የፍጥጫ ዘመናቸዉ በድፍን ዓለም ሚሊዮኖች ያለቁባቸዉን ግጭት-ዉጊያ፤ ጦርነቶችን በቀጥታም በተዘዋዋሪም ዘዉረዋል።አንድም ጊዜ፤ አንድም ሥፍራ አንዳቸዉ ሌላቸዉን ወግተዉ ግን አያዉቁም። ሞስኮና ዋሽግተን።
ቀዝዛዉ ጦርነት ማብቃቱን ሲያዉጁ የቆየ ጠብ-ዉዝግብ ፍጥጫቸዉ የመፈፀሙ ምልክት መስሎ ነበር።ከዓመታት «እረፍት» በኋላ ዳግም ሲሻኮቱ፤ ከሰርቢያ እስከ ኮሪያ፤ ከዩክሬን እስከ ሶሪያ ሐገር፤ ሕይወት፤ ንብረት የሚጠፋዉን ግጭት ጦርነት እያጋጋሙ ነዉ።አንድም ቀን አንዳቸዉ በሌላቸዉ ላይ ቃታ ስበዉ ግን አያዉቁም።ዋሽግተንና ሞስኮ።

Symbolbild Kalter Krieg Stimmung Nato und Russland Ukraine Konflikt
ምስል picture alliance/AP Photo/Mindaugas Kulbis

ሌሎችን ከማስታጠቅ፤ ማጋጨት-ማጋደል ባለፍ ቀጥታ የማይታኮሶት ኃያላን አንዱ የሌላዉን እዉቀት፤ምርት፤ሥራ እና ሥልት ለመግልበጥ፤ለማጋለጥ፤ ለማክሸፍ ወይም ለማጨናጋፍ በስላላ ዲፕሎሎሚሲዉ እንደተጠላለፉ ነዉ።የስለላ ጥልፍልፉ ርቀት ሳይበርን ፈጥሮ ሳይበርን መሳሪያዉ ካደረገ በትንሽ ግምት ሁለት አስርት አስቆጥሯል።«Hacking» ይሉታል እነሱ።የዓለም ትላልቅ መገናኛ ዘዴዎች የሰሞኑ ቋንቋም ትላልቁ ሐገራት እና ጠለፋዉ ነዉ።Hacking። 
                              
የተባበረችዉ የሶቪየት ሶሻሊስት ሪፕብሊክ (SSSR)ን ሌኒን ወይም ስታሊን ፈጥረዋት ከነበሩ የዛሬዋን የሩሲያ ፌደሬሽንን  ዳግም የመሰረቱት  የልትሲንና አልጋ ወራሻቸዉ ናቸዉ።ቭላዲሚር ፑቲን።ሶቭየት ቭረት ከተፈረካከሰች በኋላ ምጣኔ ሐብቷ ዳሽቆ ከኃይልነት ማማ-ተሽቀንጥራ ለማኝነት ወለል ላይ የተነጠፈችዉን ሐገር ዛሬ ካለችበት ከፍታ ላይ ያደረሱት የቀድሞዉ እዉቅ ሰላይ ናቸዉ። ፑቲን።
ፑቲን በ2000 ዋዜማ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ከፕሬዝደንት ቦሪስ የልትሲን የወረሱትን ሥልጣን በምርጫ አፀድቀዉ በተቆጣጠሩ ማግስት የሐገራቸዉን ምጣኔ ሐብት ገዝግዞ የጣለዉን የቼችንያን ጦርነት አስቆሙ።ሙስና፤ ዋልጌነት፣ ስንፍናን ሙሉ በሙሉ ባያጠፉ ቀነሱት።

ፑቲን የተረጋጋ መንግሥት መስርተዉ፤ ጦርነቱን አስቁመዉ፤ ሙስና፤ ዋልጌነት እና ስንፍናን ቀንሰዉ የሩሲያ ምጣኔ ሐብትን ከአዘቅጥ አንስተዉ በድሕነት አረንቋ ይዳክር የነበረ አብዛኛ ሕዝባቸዉን የመካከለኛ ገቢ ባለቤት ያደረጉት በስምንት ዓመት ዉስጥ ነበር።
ከ2000 እስከ 2008 የቆየዉ ዘመነ-ሥልጣናቸዉ በ2008 ሲያበቃ፤ አራት ዓመት በጠቅላይ ሚንስትርነት አዝግመዉ ዳግም የፕሬዝደትነቱን ሥልጣን ለመጥቀለል አንድ-ሁለት ሲሉ ከዉስጥም ከዉጪም የገጠማቸዉ ተቃዉሞ ግን ቀላል አልነበረም። 
የያኔዉ ጠቅላይ  ዳግም ለፕሬዝደንት እንደሚወዳደሩ ካስታወቁ ከ2011 ጀምሮ እስከ 2013 የቀጠለዉ የአደባባይ ሰልፍ ተቃዉሞ ዛሬም ተዳፈነ እንጂ ሙሉ በሙሉ ጠፋ ማለት ያሳስታል።
                     
በተከታታይ በተደረገዉ  የአደባባይ ሰልፍ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች፤ የመብት ተሟጋቾች ኮሚንስቶች እና ግብረ-ሰዶማዉያን ተካፋዮች ነበሩ።አብዛኞቹ የሰልፉ አደራጅና መሪዎች ግን እኒያ ፑቲን በመጀመሪያ የፕሬዝደትነት ዘመናቸዉ ከድሕነት አንስተዉ የመካከለኛ ገቢ ባለቤት ያደረጓቸዉ ንዑስ-ከበርቴዎች ናቸዉ።
ያአያት አባቶቻቸዉን የብሔረተኝነ፤ ሐገር የመዉደድ ስሜትን ችላ እያሉ የምዕራቡን ትምሕርት፤አስተሳሰብ፤ አኗኗርና ፖለቲካዊ ይትበሐል ለሚያቀነቅኑት ንዑስ ከበርቴዎች ከመገናኛ ዘዴዎች ሽፋን እስከ ሥለላ መረጃ፤ ከተቃዉሞ ሥልት እስከ ገንዘብ፤ ከዲፕሎማሲ እስከ ዓለም አቀፍ  ዕዉቅና የሚደርስ ድጋፍ የምትሰጠዉ ደግሞ ዩናይትድ ነበረች።ነችም።
ቀዝቃዛዉ ጦርነት ባበቃበት ወቅት ክሬምሊንና ዋይት ሐዉስን ይቆጣጠሩ የነበሩት ቦሪስ የልትሲንና ቢል ክሊን ጥብቅ ባይባል እንኳ የሚግባቡ ወዳጆች ይመስሉ ነበር።የየልሲን ወራሽ ፑቲንና እና የባለቤታቸዉን መንበር የሚመኙት ወይዘሮ ሒላሪ ክሊንተን ግን ለመጠፋፋት የሚፈላለጉ ጠላቶች ናቸዉ።
ብዙ ታዛቢዎች እንደሚስማሙበት የወይዘሮ ክሊንተንና የፑቲን ጠብ ዋና ምክንያት ፑቲንን በመቃወም ይደረግ የነበረዉን የአደባባይ ሰልፍ ክሊንተን በግልፅ ከመደገፍ አልፈዉ ለሰልፉ አስተባባሪዎች ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ መስጠታቸዉ እና ዓለም አቀፍ እዉቅና እንዲያገኙ መጣራቸዉ ነዉ።
የሁለቱን ጠብ የሚያዉቁት ዶናልድ ትራምፕ የዲፕሎማሲዉን ወግ ባያዉቁትም በምረጡኝ ዘመቻቸዉ ወቅት የሩሲኖችን ርዳታ በግልፅ ጠይቀዉ ነበር። 
                                  
«ሩሲያ ከሰማችሁኝ የጠፋዉን ሰላሳ ሺሕ ኢሜየል እንደምታገኙት ተስፋ አደርጋለሁ።»
ትራምፕ የጠቀሱት ኢሜል ወይዘሮ ክሊንተን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በነበሩበት ወቅት የግልና የመንግሥትን ኢሜል አሳክረዋል የተባለዉን ነዉ።የትራምፕ መልዕክት መስከረም ላይ ከመሰማቱ ከወራት በፊት ግን ዊኪሊክስ የተባለዉ ሚስጥር አጋላጭ አምደ መረብ የክሊተንን የምርጫ ዘመቻ ከሚያስተባብረዉ የዲሞክራቲክ  ፓርቲ ብሔራዊ ኮሚቴ (DNC)የጮለጉ ኢሜይሎችን ለዓለም ዘርግፎት ነበር።
ጁሊንያ አሳጅ የሚመሩት ዊኪሊክስ ሐምሌ 22 2016 ክፍል-አንድ ብሎ 17 ሺሕ 252 ኢሜሎች እና 8,034 ተያያዥ መልዕክቶች ናቸዉ።ኤሜሎችና ተያያዥ መልዕክቶቹ ከጥር 2015 እስከ ግንቦት 2016 በነበሩት ጊዚያት የክሊተን የምርጫ ዘመቻ አስተባባሪዎች የተለዋወጧቸዉን የሚያካትት ነዉ።
የፕሬዝደንት ኦባማ መስተዳድር እና የክሊንተን ደጋፊዎች እንደሚሉት ዊኪሊክስ በተከታታይ ያሰተማቸዉ መልዕክቶች  የወይዘሮ ክሊንተንን የምርጫ ዘመቻ ሚስጥር በማጋለጡ ለክሊንተን ሽንፈት- ወይም በተቃራኒዉ ለትራምፕ ድል ምክንያት ሆኗል።
አስራ-ሰባቱ የዩናይትድ ስቴትስ  የስለላ ድርጅቶችና ተቋማት በጋራ ባወጡት የጥናት ዉጤት እንዳሉት ደግሞ ኢሜሎቹን ጠልፈዉ ለዊኪሊክስ አሳልፈዉ የሰጡት በፕሬዝደንት ፑቲን በቀጥታ የታዘዙ የሩሲያ የኮምፒተር ሰላይ ወይም ጠላፊዎች (ሐከርስ) ናቸዉ።ጉዳዩን እንዲያጠራ የተሰየመዉ የምክር ቤት ኮሚቴ ሊቀመንበር ሴናተር ጆን መኬይም ይሕንኑ ደግመወታል።
«የስለላ ማሕበረሰባችን ይሕንን የሩሲያዎች እንቅስቃሴ የሚመለከት ተጨማሪ መረጃዎችን ካወጣና ለጠለፋ የዋለዉን መሳሪያ እና መዋቅርን ያካተተ ዘገባ ይፋ ካደረገ ወዲሕ የሩሲያ የሲቢልና ወታደራዊ የስለላ ድርጅቶች አሜሪካን ማጥቃታቸዉ ግልፅ ሆኗል።ሩሲያ በሐገራችን ላይ ሥለፈፀመችዉ ጥቃት ማንኛዉም አሜሪካዊ  ሊረዳዉ ይገባል።ለዩናይትድ ስቴትስ የዉጪ ሐይል ጣልቃ የማይገባባት ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ከማስተናገድ የበለጠ ብሔራዊ ጥቅም የለም።»

Boldkombo Hillary Clinton Donald Trump Emotionen
ምስል Getty Images/AFP/M. Ngan
Karikatur von unserem Karikaturisten Sergey Elkin
ምስል DW/S.Elkin

የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ መስተዳድርም የሐገሩን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ሰላሳ አምስት የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ከሐገሩ አባርሯል።በአራት የሩሲያ ባለሥልጣናት ላይም ማዕቀብ ጥሏል።የሞስኮ ዋሽግተኖች እስጥ አገባ በተለይም የዩናይትድ ስቴትስ ርምጃ ቀዝቃዛዉ ጦርነት «አበቃ» ከተባለበት ጊዜ ወዲሕ ከባዱ ቅጣት ነዉ።
                                
« ቀዝቃዛዉ ጦርነት ካበቃ ወዲሕ በሩሲያ ላይ ጠንካራ ቅጣት ሲጣል ያሁኑ እጅግ ከፍተኛዉ ነዉ።እርምጃዉ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን እንረዳለን።ይሁንና የሩሲያን ርምጃ ለመግታት ያሁኑ የመጀመሪያዉ እንጂ የመጨረሻዉ አይደለም።»
ይላሉ የኢንተርነት ደሕንነት ባለሙያ ጄምስ ሉዊስ።ሩሲያ የአሜሪካኖችን ዉንጀላ አጣጥላ ነቅፋዋለች።አሜሪካ ለወሰደችዉ እርምጃ አፀፋ እርምጃ መዉሰዷ እንደማይቀር አስጠንቅቃለችም።ይሁንና ፕሬዝደንት ፑቲን ሁለት ሳምንት በሟይሞላ ጊዜ ዉስጥ ዋይት ሐዉስን ከሚያስረክቡት ከፕሬዝደንት ኦባማ ጋር መነታረኩን አልፈለጉም።«ትራምፕ ሥልጣን እስከሚይዙ» በሚል ምክንያት አፀፋ እርምጃዉን ናቅ አድርገዉ ትተዉታል።
ተመራጭ ፕሬዝደንት  ዶናልድ ትራምፕም ኢሜሎቹን የጠለፉት የሩሲያ የስለላ ባለሙያዎች ናቸዉ የሚለዉን  የተቀናቃኞቻቸዉን ወቀሳ አልተቀበሉትም።
                      
«ይሕ ከንቱ ነገር ነዉ።አላምንበትም።እንደሚመስለኝ ዴሞክራቶች በጥሰዉ የቀጠሉት ነዉ።ምክንያቱም በዚች ሐገር የምርጫ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ሽንፈት ገጥሟቸዋል።»
ሩሲያ የጠለፈችዉ የዴሞክራቶቹን ብቻ ሳይሆን የሪፐብሊካኖቹንም የምርጫ ዘመቻ ሚስጥራዊ መልዕክቶች እንደሆነ የአሜሪካ የስለላ ድርጅቶች  አስታዉቀዋል።እስካሁን የታተመዉ ግን የዴሞክራቶቹ ብቻ ነዉ።ዶናልድ ትራምፕ ጠላፊዎቹ ቻይና ወይም ሌላ ወገን ላለመሆኑ ምን መረጃ አለ ይላሉ።የአሜሪካ የስለላ ድርጅቶች መረጃን ደግሞ የትራም የሽሽግር ቡድን አባላት «እነዚሕ ሳዳም ሁሴይን ጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያ ታጥቀዋል ብለዉ የነበሩት አይደሉም እንዴ? እያሉ ይጠይቃሉ።
የተጠለፉትን መልዕክቶች የሚያትመዉ የዊኪሊክስ መስራች ጁሊያን አሳጅም መልዕክቶቹ ከሩሲያ አልደረሱንም ባይ ናቸዉ።
                           
«ባለፉት ሁለት ወራት በተደጋጋሚ አስታዉቀናል።ምንጫችን የሩሲያ መንግስት አይደለም።መንግሥትም አይደለም።»
ከፉክክር ዘመቻዉ እስከ ዉጤቱ ተራ ስድድብ፤ ወቀሳ፤ መነቃቀፍ ያልተለዉ የአሜሪካኖች ምርጫ የሐገሪቱን ፖለቲከኞች እሁለት ገምሶ ማወዛገቡ እንደቀጠለ ነዉ።ሩሲያን በወንጀልና ባለመወንጀል የሰፋዉ ልዩነት ልዕለ ኃያሊቱን ሐገር ወዴት እንደሚያጉዛት ማጠያያቁም አልቀረም።መልሱን ግን ጊዜ ነዉ ሰጪዉ። ቸር ያሰማን።

USA TV-Duell Karikatur von Sergey Elkin

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ