1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካዊዉ ወታደር የጥገኝነት ጥያቄ

ሐሙስ፣ የካቲት 19 2007

ዛሬ ያስቻለዉ የአዉሮጳ ሕብረት ፍርድ ቤት ግን የሺፕሐርድን የጥገኝነት ጥያቄ አልደገፈዉም።ጨርሶም ዉድቅ አላደረገዉም።በፍርድ ቤቱ ዉሳኔ መሠረት ሺፕሐርድ አልዘምትም ለማለቱ ወይም የነበረበትን የጦር ክፍል ለመክዳቱ ያቀረበዉን ምክንያት በመረጃ ማስደገፍ አለበት።

https://p.dw.com/p/1EiO9
ምስል picture-alliance/epa/N. Bouvy

ምክንያቱ በኢራቁ ጦርነት ሠላማዊ ሰዎች ተጨፍጭፈዋል የሚል ነዉ።

የአፍሪቃ፤የእስያ ወይም የደቡብ አሜሪካ ዜጎች የየሐገራቸዉ መንግሥት ሲያንገላታ፤ ሲያሰቃያቸዉ ወይም እንግልት ስቃይ ያደርስብናል ብለዉ ሲፈሩ ከቻሉ ወደ ሰሜን አሜሪካ፤ወይም ምዕራብ አዉሮጳ መሰደድ የተለመደ ነዉ።ይሕ ካልሆነ በየጎረቤቶቹ ሐገራት መሸሸግ።የምዕራብ አዉሮጳ፤ የሰሜን አሜሪካ በተለይ የዩናይትድ ስቴትስ ዜጎችስ ሲከፋቸዉ ወይም ሲያስፈራቸዉ መደበቂያቸዉ የት ይሆን?ለኤድዋርድ ስኖደን ሩሲያ ናት። ለአንድሬ ሽፕሐርድስ? ጀርመን እንበል ይሆን?

ወታደር አንድሬ ሽፕሐርድ እንደ ኤድዋርድ ስኖደን ሁሉ የልዕለ ሐያሊቱ ሐገር መንግሥት በደልና ግፍ አንገፍግፎኛል ዓይነት ባይ ነዉ።ሺፕሐርድ ባየር፤ ደቡብ ጀርመን የሠፈረዉ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ባልደረባ ነበር።ኢራቅ ዘምቶ ተመልሷል። በ2007 (እንደ ጎርጎሮሳዉያኔኑ አቆጣጠር) ዳግም ወደ ኢራቅ እንዲዘምት ይታዘዛል።እንቢኝ አለ።

ትዕዛዝ አለመቀበሉ ያለምንም ዉጣ ዉረድ አመት ከመንፈቅ ያሳስረዋል።እስራቱን ፍራቻ የጦር ሠፈሩን ጥሎ ጠፋ።«ከዳ-» በጦሩ ቋንቋ።(Absent without leave)። ዘንድሮ ሰላሳዎቹን ያጋመሰዉ ወታደር አስራዘጥኝ ወራት ከተሰወረ በሕዋላ ጀርመን ዉስጥ የፖለቲካ ጥገኝነት እንዲሰጠዉ አመለከተ።

የዴሞክራሲያዊዉ ሥርዓት «ቀንዲል»፤ የሰብአዊ መብት «አክባሪ-አስከባሪይቱ» ሐገር ዜጋ ያዉም ወታደር ባየር-ጀርመን ዉስጥ የፖለቲከኛ ጥገኝነት መጠየቁ ጀርመኖችን ያስገርም፤ አንዳዶቹን ያሰጋ ብዙዎችን ያነጋግር ገባ።ጦርነትና ብሔራዊ ዉትድርናንን የሚሸሹ ሰዎችን የሚያማክረዉ ኮኔክሽን የተሰኘዉ ግብረ-ሠናይ ድርጅት ሐላፊ ሩዲ ፍሪድሪሽ ግን አንድ ሰዉ የዴሞክራሲያዊት ሐገር ዜጋ እንኳን ቢሆን ክትትል የሚደረግበት ከሆነ ጥገኝነት መጠየቅ መብቱ ነዉ።

Luxemburg Europäischer Gerichtshof EuGH Schild
ምስል picture-alliance/dpa/T. Frey

«ጥያቄዉ አንድ ሰዉ ፖለቲካዊ ክትትል ይደረግበታል ወይ የሚለዉ መሆን አለበት።ይሕ በዲሞክራቲክ ሐገርም ሊፈፀም ይችላል።»ባይፈፀም ኖሮማ-ስኖደንስ ሞስኮ ሙጥኝ ማለት ለምን አስፈለገዉ።የወታደር ሺፕሐርድ ጉዳይ አልፎ አልፎም ቢሆን የበርሊንና የዋሽግተኝ ዲፕሎማሲያዊ መጎሻሸሚያ ሆኗል።ያም ሆኖ የጀርመን የሥደተኛና የጥገኝነት ጉዳይ መስሪያ ቤት የአሜሪካዊዉን ወታደር የጥገኝነት ጥያቄ አልተቀበለዉም።

የወታደሩ ጠበቃ ሙኒክ ለሚገኝዉ ፍርድ ቤት አቤት ብለዋል።ይሁንና አቤቱታዉ በጎም ሆነ መጥፎ ዉሳኔ የሚያገኘዉ ከአዉሮጳ ሕብረት የሠብአዊ መብት ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ከወሰነ በኋላ ነዉ።የፍርድ ሒደት አጥኚ ኤሎኖር ሻርፕስቶን እንደሚሉት ሉክሰምበርግ-የሚያስችለዉ የአዉሮጳ ሕብረት ፍርድ ቤት ለአሜሪካዊዉ ወታደር ጥያቄ ትክክለኛ ዉሳኔ ይሰጣል ብለዉ ያምናሉ።

ትክክለኛ ዉሳኔ ማለት ወታደሩ የጥገኝነት ጥያቄዉ ተቀባይነት ያገኛል ማለት ነዉ።ሩዲ ፍሪድሪሽም የአንድሬ ሽፕሐድር ጉዳይ በልዩ ሁኔታ መታየት አለበት ይላሉ።«አንድሬ ሺፕሐርድ ልዩ መመሪያ የተሰኘዉ የአዉሮጳ ሕብረትን አሰራር ያስፈልገዋል።ይሕ ማለት የአዉሮጳ ሕብረት መብትን የማስከበርን ሐላፊነት የሚመለከት ነዉ።የሱ ጉዳይ በርግጥም ልዩ ነዉ።ልዩ በመሆኑም ነዉ የሙኒኩ ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ዉሳኔ ከመስጠቱ በፊት የአዉሮጳ ሕብረት ልዩየመብት መመሪያ ገቢሪያዊ እንዲሆን የምንፈልገዉ።»

Europäischer Gerichtshof für Menschenrechte
ምስል picture alliance/JOKER

ዛሬ ያስቻለዉ የአዉሮጳ ሕብረት ፍርድ ቤት ግን የሺፕሐርድን የጥገኝነት ጥያቄ አልደገፈዉም።ጨርሶም ዉድቅ አላደረገዉም።በፍርድ ቤቱ ዉሳኔ መሠረት ሺፕሐርድ አልዘምትም ለማለቱ ወይም የነበረበትን የጦር ክፍል ለመክዳቱ ያቀረበዉን ምክንያት በመረጃ ማስደገፍ አለበት።ምክንያቱ በኢራቁ ጦርነት ሠላማዊ ሰዎች ተጨፍችፈዋል የሚል ነዉ።

በመጀመሪያዉ የኢራቅ ዘመቻዉ እሱ የነበረበት ጦር በርካታ ኢራቃዉን ሠላማዊ ሰዎችን በተለይ ፋሉጃሕ ዉስጥ ሲገድል አይቻለሁ ባይነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ