1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዓመታዊ ዘገባ

ዓርብ፣ ግንቦት 21 2001

ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት፡ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘንድሮ ያወጣው ዓመታዊ ዘገባ ትኩረቱን ያሳረፈው በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኤኮኖሚ ቀውስ በሰብዓዊ መብት ይዞታ ላይ ባስከተለው አሉታዊ መዘዝ ላይ ነው።

https://p.dw.com/p/Hzo5
ምስል picture alliance/dpa

አራት መቶ ገጾች የያዘውና የ 157 ሀገሮችን ሰብዓዊ መብት ይዞታ የተመለከተው ዘገባ በኤኮኖሚው ቀውስ የተነሳ በብዙ የዓለም ሀገሮች ውስጥ ይበልጡን እየተስፋፋ የተገኘው ድህነት አለመረጋጋትንና ግዙፍ ሁከትን ሊያስከትል እንደሚችል ስጋቱን ገልጾዋል። በኤኮኖሚው ቀውስ ሰበብ የሰብዓዊ መብት የሚጣስበት ርምጃ ባፋጣኝ ገደብ ካላረፈበት በስተቀር ግዙፍ ማህበራዊ ቀውስ ሊያስነሳ እንደሚችልም ዘገባው አክሎ አስጠንቅቆዋል።

የኤኮኖሚው ቀውስ ለወትሮውም በብዙ ሀገሮች ውስጥ የሚታየውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይበልጡን እንዲከፋ ማድረጉን እአአ ከ ጥር እስከ 2008 ዓም ድረስ በነበረው ጊዜ ውስጥ የአምነስቲ ዘገባ አስታውቋል። ከአንድ መቶ ሀምሳ ሰባቱ ሀገሮች መካከል ከግማሽ የሚበልጡት መሰረታዊ የሰብዓዊ መብትን እንደሚጥሱ አመልክቶዋል። ብዙ የዓለም መንግስታት በሀገሮቻቸው የተስፋፋውን የድህነት፡ የእጦት፡ የአድልዎና ያለመረጋጋት ሁኔታን ህዝቦቻቸውን ለመጨቆኛ እንደመሳሪያ እንደሚጠቀሙበት ድርጅቱ አመልክቶዋል። የዓለም መሪዎች በወቅቱ በኤኮኖሚው ቀውስ ላይ ብቻ ማትኮራቸውን ትክክል አለመሆኑን ዘገባው በማስታወቅ፡ ለሰብዓዊ መብት ይዞታ ቅድሚያ በመስጠት ኢፍትሀዊ ሁኔታዎችን፡ አለመረጋጋትን፡ የእኩልነት መጓደልን እና ውርደትን በማስወገድ የሰብዓዊ መብት ይዞታቸውን እንዲያስተካክሉና ለቀጠሉ ውዝግቦች መፍትሄ እንዲያፈላልጉ አሳስቦዋል። የኤኮኖሚው ቀውስ ከ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ጋር ባንድነት በመሆን ወቅት እየጠበቀ የሚያመረቅዝ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማስከተሉን ነው አምነስቲ በዘንድሮው ዘገባው ለማጉላት የሞከረው። በአፍሪቃ በኤኮኖሚው ቀውስ ሰበብ በተባባሰው የድህነት ሁኔታና በሰብዓዊ መብት ጥሰት መካከል ግንኙነት መኖሩን በአምነስቲ የአፍሪቃ ፕሮግራም ዋና ስራ አስኪያጅ ኤርቪን ፋን ደር ቦርኽት ለዶይቸ ቬለ አስታውቀዋል።

ሱዳን፡ ሶማልያና ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ምስራቃዊ አካባቢን በመሳሰሉ አካባቢዎች የቀጠለው ውዝግብ እንዳሳሰበው ያስታወቀው የድርጅቱ ዘገባ፡ ለውዝግቡ መባባስ በተለይ ትንሾቹ የጦር መሳሪያዎች ዝውውር የተስፋፋበትን ድርጊት እንደ ዋነኛ ምክንያት ገልጾዋል።

የሰብዓዊ መብት ይዞታን በተመለከተ በኢትዮጵያ ያን ያህል የሚታይ ለውጥ አለመደረጉን ኤርቪን ፋን ደር ቦርኽት አስታውቀዋል።

« የመናገር እና የመደራጀት ነጻነት መጓደሉን አጉልተናል። ነጻው የመገናኛ ብዙኃንም ገደብ አርፎበታል። ተቃዋሚዎችም ታስረዋል። አምነስቲ ኢንተርናሽናል እነዚህን እስረኞች የህሊና እስረኞች አድርጎ ይመለከታቸዋል። በተለይ በአውሮጳውያኑ 2009 ዓም መጀመሪያ ላይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የሚመለከት አዲስ አዋጅ ከወጣ ወዲህ በሀገሪቱ ያሉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሁኔታ አሳስቦናል። አምነስቲ ህጉ የመናገር እና የመደራጀት ነጻነት ይጥሳል ብሎ ነው የሚያምነው። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማክበር ግዴታ የገባችውን የሰብዓዊ መብት ህግን ይጻረራል። »

ድርጅታቸው ወደኦጋዴን አካባቢ የመሄድ ዕድል እንዳላጋጠመው የገለጹት ፋን ደር ቦርኽት በዚያ የቀጥለው የጦር እንቅስቃሴ በሲቭሉ ህዝብ ላይ ብርቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ማስከተሉን

የሚያሳዩ መረጃዎች ማግኘቱን አስታውቀዋል። በሰብዓዊ ርዳታ ላይ ገደብ ያሳረፈው የጦሩ እንቅስቃሴ ባካባቢው በሚኖረው ሲቭል ህዝብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አስከትሎዋል። ፋን ደር ቦርኽት ድርጅታቸው ወደ ኤርትራ በመሄድ ሁኔታዎችን የመመልከት ዕድል ባያጋጥመውም ስለ ኤርትራ የሰብዓዊ መብት የሚያገኘው መረጃ በጠቅላላ እጅግ አስከፊ መሆኑን አመልክተዋል።

« በኤርትራ ያለው የሰብዓዊ መብት ይዞታ በአፍሪቃ ክፍለ ዓለም እጅግ መጥፎ ከሚባሉት አንዱ ነው። የሀይማኖት እና የመናገር ነጻነት የለም። ለሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም በሀገሪቱ ቦታ የለም። ህዝብ በመደዳ እንደሚታሰርና በወህኒ ቤቶችም ውስጥ እንደሚጉላሉ ተመልክተናል። ከዚህ በተጨማሪ ያያነውም ሸሽተው ወደ ሌሎች ሀገሮች ከሄዱ በኋላ ግብጽን፡ ሱዳንን፡ ጀርመንንና ብሪታንያን በመሳሰሉ ሀገሮች በግዳጅ ወደ ኤርትራ እንዲመለሱ የተደረጉ ኤርትራውያንም ችግር እንደሚደርስባቸው ነው። »

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የዘንድሮ ዘገባ አፍሪቃ መንግስታት የህዝቦቻቸውን መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት እንዲያከብሩ፡ የውኃ፡ የምግብ፡ የጤናና የመንሪያ ቤት ፍላጎትን እንዲያሟሉ አሳስቦዋል። በብዙ የዓለም ሀገሮች የተስፋፋው ድህነት ወደለየለት ማህበራዊ ቀውስ እንዳይለወጥም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለድሆቹ ሀገሮች የሚሰጠውን የልማት ርዳታ እንዲቀጥልበት ዘገባው ሀሳብ አቅርቦዋል።

አርያም ተክሌ/ተክሌ የኋላ