1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአረብ አብዮትና ትምሕርት

ዓርብ፣ ሰኔ 15 2004

የአረብ መንግሥታት ባሁኑ ወቅት ዉጤታማ የሆነ የትምሕርት መርሕ ያስፈልጋቸዋል።በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፥ መገናኛ ዘዴዎችን፥ የሠራተኛ ማሕበራትን የመሳሰሉ ተቋማትን ለመመሥረት፥ ዳግም ለማዋቀርና ለመምራት የሚችሉ አዋቂዎች በጣም አስፈላጊዎች ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/15Jc1
Die Azhar-Universität (arabisch ‏جامعة الأزهر‎ dschamiʿat al-azhar, „die Blühende“) in Kairo ist eine der angesehensten Bildungsinstitutionen der islamischen Welt Deutsch: Al-Azhar-Universität, Kairo Datum August 2006(2006-08) Quelle English: German Wikipedia Deutsch: Deutsche Wikipedia
አንጋፋዉ የ አል-አዝሐር ዩኒቨርስቲ

በዓረቡ ዓለም በተደረገዉ ሕዝባዊ አብዮት የየሐገሩ ወጣቶች ግንባር ቀደም ተሳታፊዎች ናቸዉ።ወጣቶቹ ለዚሕ በቂ ምክንያት አላቸዉ።ከወላጆቻቸዉ ይበልጥ የተማሩና በሙያ የሠለጠኑ ቢሆኑም የሥራ ዕድል ግን የላቸዉም።

የቱኒዚያና የግብፅ ሕዝባዊ አብዮት በጋመበት ሰሞን ከቱኒዝና ከካይሮ በመላዉ አለም የናኙት ፎቶ ግራፎች ሁሉንም ይሉታል።አንድ እጁን ቡጢ ጨብጦ ሽቅብ ያጓነ፥ በሌላ እጁ ዲግሪ ወይም ዲፕሎማ የያዘ ወጣት ፎቶግራፍ።የአረብ ወጣቶች ከወላጆቻቸዉ በጣም የተሻለ የትምሕርትና የሙያ ሥልጠና አግኝተዋል።ለመማርና ለመሰልጠን ያለዉን ዕድል ሁሉ ተጠቅመዉበታል።ያም ሆኖ ብዙዎቹ ወጣት ምሑራን ሥራ የላቸዉም።

ወጣቱ ትዉልድ ሥራ በማጣቱ የሚደርስበት ችግር ለግል ሕይወቱ የሚያስፈልገዉን ገንዘብ ማጣት ብቻ አይደለም።በወግ አጥባቂዉ የአረብ ማሕበረሰብ ቋሚ ገቢ ሳይኖር ፍቅረኛ ማግኘት ወይም ቤተሰብ መመሥረት የማይቻል ያሕል ከባድ ነዉ። ወጣት ምሑራኑ በየተቃዉሞ ሠልፉ ቁጣቸዉን ቢገልፁ አያስደንቅም።ለችግራቸዉ ተጠያቂ የሚያደርጉት የየመንግሥታቸዉን የትምሕርትና የምጣኔ ሐብት መርሕ (ፖሊሲ)ን ነዉና።

የሥራ ዕድል የማይፈጥር የምጣኔ ሐብት ዕድገት

Muslim Brotherhood students hold a copy of the Quran during a protest at the al-Azhar university in Cairo, Egypt, Wednesday, April 16, 2008. Thousands of Muslim Brotherhood students in two Egyptian universities demonstrated Wednesday against the jailing of 25 members of the group for membership of an outlawed organization and anti-government activities. (AP Photo/Hossam Ali)
ወጣት ተቃዉሞ ሠልፈኞችምስል AP

ብዙዎቹ የአረብ መንግሥታት ባለፉት ተከታታይ አመታት ትምሕርትን ለማስፋፋት በርካታ ገንዘብ አዉጥተዋል።የዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች ቁጥር በእጅጉ ጨምሯል።የምጣኔ ሐብቱም ባለፉት አስር አመታት በከፍተኛ ሁኔታ አድጓል።ይሁንና መንግሥታቱ የኢንዱስትሪና የኢንቨስትመንት መርሐቸዉን ከከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት ለመተረቁ ምሑራን የሥራ ዕድልን ከመፍጠር ጋር አላጣጣሙትም።

ቱኒዚያ ለዚሕ ጥሩ ምሳሌ ናት።የቱኒዚያ ምጣኔ ሐብት ባለፉት ዓመታት ከአማካይ በላይ አድጓል።እድገቱ ግን በአብዛኛዉ ወደ አዉሮጳ በሚላክ የጨርቃ ጨርቅ ምርትና ሐገር በማስጎብኘት (ቱሪዝም) ላይ የተመሠረተ ነዉ።ከከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት የተመረቁ ብዙዎቹ ወጣት ምሑራን ከሠለጠኑበት የሙያ መስክ ጋር የሚጣጣም ሥራ በጨርቃጨርቁም ሆነ በቱሪዝሙ መስክ  አያገኙም።የመንግሥት ምጣኔ ሐብታዊ መርሕ ያስከተለዉ የቢሮ ዉጣ ዉረድ (ቢሮክራሲ)፥ የተንሠራፋዉ ሙስናና የዘመድ-አዝማድ አሠራር ወጣቶቹ በግሉ ክፍለ-ኢኮኖሚ እንኳን ሥራ እንዳያገኙ እንቅፋት ሆኗል።

የተዛባ የትምሕርት ፅንሠ-ሐሳብ

መንግሥታት ባለፉት ዓመታት የከፍተኛ ትምሕርት ተቋማትንና ትምሕርት ቤቶችን ለማስፋፋት ጠቀም ያለ ገንዘብ ቢመድቡም ዉጤት ግን አልታየም።የሥርዓተ-ትምሕርት ባለሙያዋ ሳባሕ ሳፊ የተዛባዉን የትምሕርት ሥርዓትና እያሽቆለቆለ የመጣዉን የትምሕርት ጥራት የአረቡን ዓለም የሚያሽመደምድ የ«ዕዉቀት ክፍተት» በማለት ያስጠነቀቁት ከዓመታት በፊት ነበር።ጂዳ በሚገኘዉ የንጉስ አብዱል አዚዝ ዩኒቨርስቲ ለሃያ-አምስት አመታት ያስተማሩት ሳባሕ ሳፊ በአረቡ ዓለም የትምሕርት ጥራትን ዝቅጠት የሚያቀርቡት ማስረጃ የእዉቅና ማረጋገጪያ ያገኙ ተቋማት ቁጥር ማነስን ነዉ።

«በዓረቡ ዓለም የጥራት እዉቅና ማረጋገጪያ የተሰጣቸዉ ተቋማት ቁጥር፥ ከዓለም አቀፍ ደረጃ ጋር ሲነፃፀር በአስደንጋጭ ሁኔታ ዝቅተኛ ነዉ።» ይላሉ።ባለፉት ዓመታት አንዲት ደቡብ ኮሪያ ብቻ ለ16 ሺሕ ተቋማቷ የጥራት ማረጋገጪያ አግኝታለች።በተመሳሳይ ጊዜ ከመላዉ የአረብ ሐገራት እዉቅና ያገኙት ግን ከአንድ ሺሕ ያነሱ ናቸዉ።

ያረጃ የትምሕርት አሠጣጥና የሥራ ተኮር ትምሕርት እጥረት

ሳፊ እንደሚያምኑት ከቀዉሱ መሠረታዊ ምክያቶች ቀዳሚዉ ያረጀና እራሱን የሚደግም የትምሕርት ሥርዓት ነዉ።በመንግሥት ትምሕር ቤቶች የሚሠሩ መምሕራን በቅጡ የሠለጠኑ አይደሉም።በቂ ደሞዝ አይከፈላቸዉምም።እነዚሕ መምሕራን የሚያዉቁትና እንደ ባሕል የተያዘዉ «የተነገረ ወይም የተፃፈልሕን መልሰሕ ትፋ» አይነት የማስተማር ዘዴ የተማሪዎችን ንቁ ተሳትፎ፥ አዳዲስ ሐሳቦችንና ፈጠራዎችን፥ ያግዳሉ።ሽምደዳን መሠረት ያደረገ የማስተማር ዘዴ «የአረብ ዩኒቨርስቲ ተመራቂዎች ዓለም አቀፍ (የሥራ) ዉድድሮች) ተቀባይነት ለማጣታቸዉ ዋናዉ ምክንያት ነዉ» ይላሉ ሳፊ።

የአረብ መንግሥታት ማይምነትን ለማጥፋት ያደረጉት ጥረት ተሳክቶላቸዋል።ዉጤታማ ትምሕርትን እና ሥራ ተኮር እዉቀትን ለማስፋፋትና ከሥራ ገበያያዉ ጋር ማጣጣም ግን አልቻሉም።በዚሕም ሠበብ በብዙዎቹ የአረብ ሐገራት በተፈጥሮ ሳይንስ መስክ በተለይም ሐኪሞችና ኢንጂኖሮች ከሚፈለገዉ በላይ ሲኖሩ፥ የሠለጠኑ ወይም የተማሩ ጋዜጠኞች፥ የሥነ-ማሕበረሰብና የፖለቲካ ሳይንስ ባለሙያዎች ግን ከፍተኛ እጥረት አለ።

የአረብ አብዮት ትምሕርት ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች አልገባም

Thousands of Egyptian protesters gather in Tahrir Square, the focal point of Egyptian uprising, in Cairo, Egypt, Friday, July 29, 2011. Thousands of Egyptians rallied in Cairo's central Tahrir Square on Friday seeking to unify their demands despite rifts over key issues between liberal activists and Islamist groups. (Foto:Amr Nabil/AP/dapd)
ሕዝባዊዉ አብዮትምስል dapd

የአረብ መንግሥታት ታሪካዊ ለዉጥ በሚካሔድበት ባሁኑ ወቅት ዉጤታማ የሆነ የትምሕርት መርሕ ያስፈልጋቸዋል።በተለይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፥ መገናኛ ዘዴዎችን፥ የሠራተኛ ማሕበራትን የመሳሰሉ ተቋማትን ለመመሥረት፥ ዳግም ለማዋቀርና ለመምራት የሚችሉ የማሕበራዊ ሳይንስ አዋቂዎች በጣም አስፈላጊዎች ናቸዉ።

የአረቡ ዓለም ከጠባቂነትና ከተቀባይነት አስተሳሰብ እንዲላቀቅ በተማሪዎችና በትምሕርት ተቋማት ዲሞክራሲን፥ግልፅነትንና ተሳታፊነትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ይመክራሉ።ይሁንና በርሊን የሚገኘዉ የዘመናዊ የምሥራቅ ባሕል (ኦርየንታል) ጥናት ማዕከል ምክትል ሐላፊ ሶንያ ሔጋስይ እንደሚሉት የፋርስ ባሕረ-ሠላጤና የሰሜን አፍሪቃ ትምሕርት ቤቶችና ዩኒቨርስቲዎች በዚሕ አቅጣጫ የሚያደርጉት ጉዞ ሲበዛ አዝጋሚ ነዉ።ተቋማቱ የአረብ አብዮት አልዳሰሳቸዉም።«ይሕ ትልቅ ችግር ነዉ።በአረቡ ዓለም አሮጌዉ ሥርዓት በመደርመስ ላይ ቢሆንም የተማሪዎች ተሳትፎ በሁሉም መስክ ከፍተኛ እገዳ ይደረግበታል።» ይላሉ አጥኚዋ።ዋቢ የሚያደርጉት ደግሞ ካይሮ የሚገኘዉ የጀርመን ዩኒቨርስቲን ነዉ።«ዩኒቨርስቲዉ ለመደራጀት የፈለጉ ተማሪዎቹን እንደሚቀጣ (እንደሚያግድ) አስጠንቅቋል።» አከሉ ሔጋስይ።
ሎአይ ሙድሁን

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ
Negash Mohammed
Aryam Abraha