1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአርከበ ዕቁባይ ተፎካካሪዎች እነማን ናቸው?

ረቡዕ፣ ግንቦት 25 2013

የኢትዮጵያው አርከበ ዕቁባይ፣ የጀርመኑ ጌርድ ሙለር እና የቦሊቪያው በርናርዶ ካልዛዲላ ሳርሚዬንቶ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ለመሆን ይወዳደራሉ። በሐምሌ ቀጣዩ ዳይሬክተር ጄኔራል በተ.መ. የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የቦርድ አባላት ይመረጣል። ውጤቱ በኅዳር በሚካሔደው ጠቅላላ ጉባኤ መጽደቅ ይኖርበታል

https://p.dw.com/p/3uMdv
Äthiopien Arkebe Oqubay
ምስል DW/T. Waldyes

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የተ.መ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትን ለመምራት የቀረቡ እጩዎች እነማን ናቸው?

የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (UNIDO) ዳይሬክተር ጄኔራል ለመሆን የሚወዳደሩት ሶስት እጩዎች ባለፈው ሳምንት በቪየና በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ቢመረጡ ገቢራዊ እናደርገዋለን ያሉትን እና ለተቋሙ ያላቸውን ርዕይ ለድርጅቱ አባላት አቅርበዋል። ከሶስቱ እጩዎች አንዱ በመጪው ሐምሌ በሚደረግ ምርጫ ካሸነፈ ላለፉት ስምንት አመታት የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትን በዳይሬክተር ጄኔራልነት የመሩትን ቻይናዊው ሊ ዮንግ ይተካል።

እጩነታቸውን ከወራት በፊት ይፋ ያደረጉት የኢትዮጵያው አርከበ ዕቁባይ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ሆነው ቢመረጡ ስለሚከተሉት አመራር እና ትኩረት ስለሚያደርጉባቸው ዘርፎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የአርከበ ርዕይ

ዶክተር አርከበ ዕቁባይ "የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትን በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ለኢንዱስትሪ ልማት መሪ ዓለም አቀፍ ተቋም አድርጎ ለማጠናከር እና ለመለወጥ ርዕይ አለኝ" ሲሉ ተደምጠዋል።

"የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካስከተለው ተጽዕኖ ተመልሰን መገንባት ስንጀምር የኢንዱስትሪ መስፋፋትን እንደገና ለመፈተሽ ልዩ ዕድል ተፈጥሯል። ይኸን የተቀናጀ ዓለም አቀፍ ጥረት ለማሳካት አጠቃላይ የልማት አጀንዳ እና ለአካባቢ ተስማሚነት፣ ለፆታ ዕኩልነት እንዲሁም ለተጨባጭ ለውጥ ቅድሚያ የሚሰጥ የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ለማበረታታት በማደግ ላይ የሚገኙ እና ያደጉ አገሮችን ማቀናጀት ያስፈልጋል። ዘላቂ የልማት ግቦችን በ2030 ለማሳካት ለተጣለበት ግዳጅ የሚጥር እና የታደሰ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ከምንጊዜውም በላይ ያስፈልገናል" ብለዋል።

Li Yong, Generaldirektor von UNIDO
ቻይናዊው ሊ ዮንግ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትን በዳይሬክተር ጄኔራልነት ለስምንት አመታት መርተዋልምስል picture-alliance/ZUMAPRESS.com/Agencia EL UNIVERSAL/B. Fregoso

"በአግባቡ የተነደፈ እና ተግባራዊ የተደረገ የኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ዕቅድ ሊያመጣ የሚችለውን ቀጥተኛ እና ተዘዋዋሪ ጥቅም እኔ ራሴ አይቻለሁ" ያሉት አርከበ የፖሊሲ እና የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ዝግጅት እና ትግበራን ጨምሮ ለሶስት አስርት አመታት ገደማ በመንግሥት ኃላፊነት ማገልገላቸውን ጠቅሰዋል። 

ባለፉት አመታት በሐዋሳ፣ በአዳማ እና በመቐለ ከተሞች የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሲመረቁ ባደረጓቸው ንግግሮች ኢትዮጵያ ዘርፉን ለማስፋፋት የመረጠችው መንገድ የወጪ ንግድን ለማበረታታት፣ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና ግፋ ሲልም ዳጎስ ያለ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ኹነኛው መንገድ መሆኑን አርከበ ጠቁመው ነበር።

ሶስት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ምኒስትሮችን ያገለገሉት አርከበ በመንግሥት ኃላፊነት በሰሩባቸው አመታት ያካበቱትን የሥራ ልምድ ጠቅሰው ለኃላፊነቱ ብቁ መሆናቸውን አስረድተዋል። "የሥራ ልምዴ በተለይ ውጤታማ መዋዕለ-ንዋይ ለማምጣት ሥኬታማ አመራር መስጠት እና ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ማድረግ፣ አካታች እድገትን ማበረታታት እንዲሁም ሥራ የሚፈጥሩ እና የሚሊዮኖችን ሕይወት የሚለውጡ ፖሊሲዎች ተግባራዊ ማድረግን ይጨምራል" ያሉት አርከበ "የአፍሪካ አገሮች የገጠሟቸውን መሠረታዊ ተግዳሮቶች ብቻ ሳይሆን በሌሎች በማደግ ላይ በሚገኙ ቀጠናዎች የሚገኙ አገሮች ያሉባቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች እረዳለሁ" ብለዋል።

በማደግ ላይ ባሉ አገሮች የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ለማበረታታት እና ለመደገፍ ኅዳር 8 ቀን 1959 ዓ.ም የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ባስተላለፈው የውሳኔ ሐሳብ የተቋቋመው ይኸ ተቋም 170 ገደማ አባል አገራት አሉት። ድርጅቱን ከመሠረቱ አባል አገራት መካከል አሜሪካ እና ካናዳ ጥለው ወጥተዋል። ከአፍሪካ ኤርትራ እና ደቡብ ሱዳን ጭርሱን አባል አይደሉም። አርከበ እንዳሉት ቢመረጡ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት አባል ያልሆኑ አገሮችን ተቋሙን እንዲቀላቀሉ፤ የቀድሞ አባላቱ እንዲመለሱም መሥራት ቅድሚያ ከሚሰጧቸው ጉዳዮች መካከል ናቸው። 

Äthiopien Der Industriepark Adama
ኢትዮጵያ አዳማ፣ ሐዋሳ እና መቐለን በመሳሰሉ ከተሞች የኢንዱስትሪ ፓርኮች ስትገነባ አርከበ ዕቁባይ ከፍ ያለ ሚና ተጫውተዋል። ምስል Eshete Bekele Tekle/DW

"የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ወደ ፊት ለሚገጥሙት ችግሮች የተዘጋጀ ተቋም አድርጎ ለመለወጥ ቃል ገብቼ እሱን ለማሳካት እሰራለሁ። ይኸ መግባባት መፍጠር፣ ጥምረት ማበጀት፣ ከአባል አገራት ጋር በቅርበት መሥራት፣ ከግሉ ዘርፍ ጋር የሚደረገውን ውይይት መምራት እና ዓለም አቀፍ ትብብርን ማበረታታትን ይጠይቃል። በእኔ አመራር ድርጅቱን የትጉ አገሮች እውነተኛ አጋር እና የአረንጓዴ ዕድገት አቀጣጣይ በማድረግ እንለውጠዋለን። የኢንዱስትሪ ልማት፣ ውጤታማ የሥራ ዕድሎች ፈጠራ፣ የኤኮኖሚ ዕድገት፣ ዘላቂ ልማት እና የፆታ ዕኩልነትን የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ተልዕኮ ቁልፍ ግቦች አደርጋለሁ" በማለት እንዲመረጡ ወትውተዋል።

በኢትዮጵያ መንግሥት በእጩነት የተጠቆሙት አርከበ ከጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከአፍሪካ ኅብረት ድጋፍ አግኝተዋል። የአፍሪካ ኅብረት ሥራ አስፈፃሚ ምክር ቤት ባለፈው ጥር 2013 ዓ.ም. ዶክተር አርከበ  ብቸኛው የአፍሪካ እጩ ሆነው እንዲቀርቡ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።  

አርከበ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባነትን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊነቶች ሰርተዋል። በከፍተኛ ኃላፊነቶች የሾማቸው የቀድሞው ኢሕአዴግ ፈርሶ መሥራቾቹ በተለያየ መንገድ ሲጓዙ የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ልዩ አማካሪ ሆነው መስራታቸውን እንደቀጠሉ ናቸው።

መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ "ኃላፊነታችሁን በማቆም ወደ ድርጅታችሁ ሪፓርት እንድታደርጉ" የሚል ትዕዛዝ በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከተሰጣቸው በፌድራል መንግሥቱ ውስጥ የነበሩ 13 ተሿሚዎች እና 27 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መካከል አንዱ ዶክተር አርከበ ነበሩ። ህወሓት ይመራው የነበረው የትግራይ መስተዳደር ከፌድራል መንግሥቱ ያለው ግንኙነት ሻክሮ ውጊያ ከተቀሰቀሰ በኋላ በአደባባይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው የሚታዩት አርከበ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትን ኃላፊነት ለመረከብ ሁለት ተፎካካሪዎች አሉባቸው።

የአርከበ ዕቁባይ ተፎካካሪዎች እነማን ናቸው?

የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ለምርጫው ከኢትዮጵያ፣ ከጀርመን እና ከቦሊቪያ ሶስት እጩዎች መቀበሉን ይፋ ያደረገው ባለፈው ግንቦት 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር። 

ላለፉት ስምንት አመታት ገደማ የጀርመን የኤኮኖሚ ትብብር እና ልማት ፌድራል ምኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ጌርድ ሙለር የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትን ለመምራት ከአርከበ ከሚወዳደሩ ሶስት እጩዎች አንዱ ናቸው። አሁን የያዙትን ኃላፊነት ከመረከባቸው በፊት የጀርመን የምግብ፣ የግብርና እና የሸማቾች ደህንነት ምክትል ምኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

"በአሁኑ ወቅት በሁላችንም ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ዓለም አቀፍ ፈተናዎች ተጋርጠውብናል" ያሉት ጌርድ ሙለር እኩልነትን ለማስፈን፣ የተሻለ መልሶ ለመገንባት እና የተፈጥሮ ሐብት እንዲያገግም ለማስቻል የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ቁልፍ ሚና ሊጫወት እንደሚችል ተናግረዋል።

"የከባቢ አየር ለውጥን እንዴት ማቆም እንዳለብን፤ እያንዳንዱ ሰው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት ማግኘት እንዳለበት፤ ረሐብ በሌለበት ዓለም መኖር እንደሚገባን፤ በሕይወታቸው የተሻለ ዕድሎች ለሚመኙ ወጣቶች ጥሩ የሥራ ዕድሎች መፍጠር እንዳለብን እናውቃለን። ለዚህ መልሱ አካታች እና ዘላቂ የኢንዱስትሪ መስፋፋት ነው" ያሉት ሙለር ያስፈልጋሉ ካሏቸው መካከል "ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት" ይገኝበታል።

"በእኔ ፕሮግራም የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የ2025 ዕቅድ ዳይሬክተር ጄኔራል ሊ ዮንግ ስኬታማ ሥራ ላይ የሚገነባ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ለቴክኖሎጂ፣ ለእውቀት እና ለዲጂታላይዜሽን ሽግግር፤ ለዘላቂ የልማት ግቦች ስኬት የሚሆን መድረክ በመፍጠር ድርጅቱን አጠናክረዋለሁ። እንዲህ አይነት መድረክ ክህሎት እና ቴክኖሎጂን ማሳደግ፣ የታዳሽ ኃይሎችን አጠቃቀም ማስፋፋት እና በዓለም ገበያ እና የምርት ሰንሰለት ፍትሐዊ ዕድልን መክፈት ይኖርበታል" ሲሉ ጌርድ ሙለር ተናግረዋል።

Gerd Müller Bundesentwicklungsminister
የጀርመን የኤኮኖሚ ትብብር እና ልማት ፌድራል ምኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ጌርድ ሙለር ድርጅቱን ለመምራት ከቀረቡ እጩዎች አንዱ ናቸውምስል Michael Kappeler/dpa/picture-alliance

ሶስተኛው እጩ በአሁኑ ወቅት የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት የዲጂታላይዜሽን፣ ቴክኖሎጂ እና የግብርና ንግድ ዘርፍን በዳይሬክተርነት የሚመሩት የቦሊቪያው በርናርዶ ካልዛዲላ ሳርሚዬንቶ ናቸው። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በማወክ በአነስተኛ እና ጥቃቅን ተቋማት ላይ ብርቱ ጫና ማሳደሩን የጠቀሱት ሳርሚዬንቶ በተለይ ተጋላጭ በሆኑ ማህበረሰቦች ላይ መበርታቱን ተናግረዋል። ኃላፊው "በዚህ ፈታኝ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት አስፈላጊነት እንደገና ተረጋግጧል" ብለዋል። 

ዓለም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካሳደረው ተፅዕኖ ሲያገግም በአነስተኛ እና ጥቃቅን ተቋማት ላይ ማተኮር እንደሚያሻ እምነታቸውን የገለጹት ሳርሚዬንቶ ተቋሙ በግብርና ንግድ፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳ፣ ታዳሽ ኃይሎች እና የተሽከርካሪ ማምረቻዎች ዘርፍ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው ሞግተዋል።

"ለወቅታዊው ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት እና ለወደፊቱም ለመዘጋጀት ጤና ተኮር የኢንዱስትሪ ዘርፎችን ማጠናከር ይገባናል" ሲሉ የተደመጡት ሳርሚዬንቶ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ብሎክቼን እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) በመሳሰሉ የቴክኖሎጂ ዘርፎች አባላት አገራቱን እንዲያግዝም ሐሳብ አቅርበዋል።

"የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅትን አውቀዋለሁ። ከዚህ የተሻለ መሥራት እንደሚኖርበት እና እንደሚችልም እረዳለሁ። የኢንዱስትሪ መስፋፋት ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት፣ በመላው ዓለም ለወጣቶች ጥሩ ሥራ፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴ እና የተሻለ ሕይወት ለመፍጠር ጥቅም ላይ መዋል አለበት የሚል ቁርጠኛ አቋም አለኝ" ሲሉም ተደምጠዋል።  

በመጪው ሐምሌ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ቦርድ አባላት ድምጽ ሰጥተው ቀጣዩ ዳይሬክተር ጄኔራል ይመረጣል። ውጤቱ ኅዳር 2014 ዓ.ም. በሚካሔደው የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ መጽደቅ ይኖርበታል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ