1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘምና መድረክ

ዓርብ፣ መጋቢት 22 2009

በኢትዮጵያ ላለፉት ስድስት ወራት በመላው ሀገሪቱ ጸንቶ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገዢው ኢህአዴግ እና ተባባሪዎቹ ሙሉ ለሙሉ በተቆጣጠሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚራዘም የተጠበቀ መኾኑን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙዎች አስተያየት ሰጥተዉበታል።

https://p.dw.com/p/2aNJa
Äthiopien Unruhen
ምስል Getty Images/AFP/Z. Abubeker

የማህበራዊ መገናና ዘዴዎች ቅኝት

በኢትዮጵያ ላለፉት ስድስት ወራት በመላው ሀገሪቱ ጸንቶ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ አራት ወራት መራዘሙ የተነገረው ትናንት ነበር። ገዢው ኢህአዴግ እና ተባባሪዎቹ ሙሉ ለሙሉ የተቆጣጠሩት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔውን እንደሚያሳልፉት የተጠበቀ መኾኑን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙዎች አስተያየት ሰጥተዉበታል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመራዘሙ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ደግሞ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የተሰኘው የተቃዋሚ ፓርቲ ከኢህአዴግ እና ከሌሎች ተቃዋሚ ፓቲዎች ጋር ሲያከናውን የነበረውን ቅድመ ድርድር ውይይት ማቋረጡን ገልጧል። ፓርቲው ካቀረባቸው ቅድመ ኹኔታዎች መካከል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስር ኾኖ ከአባላቱ እና ከደጋፊዎቹ ጋር መወያየት ስለማይቻል አዋጁ ይነሳ የሚል ነበር። ከማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በኢትዮጵያ ለሚቀጥሉት አራት ተጨማሪ ወራት መራዘሙ ይፋ ሲደረግ በበርካታ የማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ዘንድ ብዙም ያልተጠበቀ ኾኖ አልታየም። ወርቄ፦ መርፌ ቁልፍ በሚል የትዊተር አድራሻ የቀረበ ጽሑፍ ይህን ያመላክታል። "አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተራዘመ ብላቹ ስለምን ታለቃቅሳላቹ… ለ26 ዓመት ኖራችሁበትም የለምን?" አለ ስሙን የረሳሁት ፈላስፋ»  ይላል የመርፌ ቊልፍ ጽሑፍ። 

ሲሞን አለባቸውም ከመርፌ ቊልፍ ጋር ተመሳሳይነት ያለው በእንግሊዝኛ የቀረበ ጽሑፍ በትዊተር አስነብቧል። «እንግዲህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለአራት ወራት ተራዝሟል፤ እናስ መንግሥት ለዚህም ማሳመኛ አግኝቶለት ይኾን? 25 ዓመት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ» የሲሞን መልእክት ነው። 
ሊያና ተፈሪ ደግሞ «በዚህም አለ በዚያ ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች መብት የላቸውም። አምባገነኖቹ  ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊትም ያሻቸውን ሲያደርጉ ነበር፤ ከዚያም በኋላ ቢሆን ተመሳሳይ ነው፤ አራት ነጥብ» ብላለች።  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአደጋ ጊዜ የሚደነገግ ጊዜያዊ አዋጅ መኾኑን በማጣቀስም፦ «ካድሬዎቹ የገባቸው አልመሰለኝም» በማለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የእንግሊዝኛ ትርጓሜን ከትዊተር ጽሑፏ ጋር አያይዛለች።

Symbolbild Soziale Netze
ምስል picture-alliance/dpa/Heimken

ዳዊት እንየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም በንግድ፤ በሀገር ጉብኝት እና በመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ላይ መዘዙ ብርቱ መኾኑን ጽፏል። 
ዘካሪያስ ኃይሉ በትዊተር ገጹ ላይ ፖል ሼም የተባለ ሰው ያቀረበውን የትዊተር መልእክት በማያያዝ «የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኢትዮጵያ አዲስ የተለመደ ነገር ኾኗል» ሲል አስነብቧል። የፖል ሼም ትዊተር «ሁሉም ነገር በጣም ጥሩ ከኾነ ታዲያ፤ ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማስረዘሟ ስለምን?» ሲል ይጠይቃል። ከፖል ትዊተር ጋር የዩናይትድ ስቴትሱ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ መልእክት አብሮ ተያይዟል። ጋዜጣው በጽሑፍ ያወጣው ርእስ፦ «ምንም እንኳን ከውጭ ጸጥታ መስፈኑ ቢታይም ኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አራዘመች» ይላል።  

ቀደም ሲል ጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የገዢዉ ፓርቲ አባላት ብቻ በሚገኙበት ምክር ቤት ቀርበው ባሰሙት ንግግር፦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስለመነሳት አለመነሳቱ በተደረገ ጥናት 82 በመቶ የሚሆነው የጥናቱ ተሳታፊዎች አዋጁ በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ እንዲቀጥል ምላሽ»  ሰጥተው ነበር ብለዋል። እሸቱ ሆማ ቄኖ በፌስቡክ ገጹ፦«በጥናት በተረጋገጠው መሠረት ተራዘመ አይደል?!?! ድሮውንም የእነአባይ ፀሃዬ "ጥናት" መሬት ጠብ አትልምኮ» ሲል አጠር ያለ መልእክት አስፍሯል። 
በዶይቸ ቬለ የፌስቡክ ገጽ ላይ ከቀረቡ አስተያየቶች መካከል የተወሰኑትን እንመልከት።  ዓይንዓለም ኪዳኔ፦ «አይደለም 6 ወር ለምን 10 አመት አይሆንም ለሰላም እስከሆነ ድረስ የናንተ ርእዮተ አለም ወደ ነበረችበት አዘቅት ማስመለስ ነው። ህዝባችን ነቅተዋል የሸወዳቹት ይበቃል አውሮጳ ተቀምጠህ መለፍለፍ ናና አካፋና ሞዶሻ ይዘህ አገርህ አልማ» ብላለች። 

ራስ መስፍን ደግሞ፦ «ኢትዬጵያ ላይ በስውር ከታወጅ 25 ዓመት ሞልቶታል በገሐድ ከታወጀ 6 ወር፤» ሲል አጠር ያለ አስተያየት ጽፏል። አብዱረስ ቀዊሲያት «አዋጁ ምንም ዓይነት አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ የለውም፤» ባይ ነው። «ከአዋጁ በፊትም ሆነ በኋላ ይገላሉ፣ የስራሉ፣ ይደበድባሉ፣ ያፍናሉ ... ወዘተ፣ ሁሉንም ኢሰብዓዊ ድርጊት ይፈፅማሉ። ምኑንም ከምንም ማነፃፀር አይቻልም ሁሉም ያው ነው። ለማስመሰል ያህል በውጪ ዜጎች ላይ ልዩነት ሊኖረው ይችላል፤» የሚል አስተያየትም አክሏል። 

የአስቸኳይ አዋጁ መራዘምን በተመለከተ «ምን ጥያቄ አለው መቀጠለ አለበት፤ ሠላም አግኝተናል» ያለው ደግሞ ጌታ ጉልበቴ የተባለ የፌስቡክ ተከታታይ ነው።
«አዋጁን በክፉም ሆነ በደጉ ለማስተንተን እኮ መጀመሪያ ነፃነት ሊኖረን ይገባ ነበር። የደላው ሙቅ ያኝካል» በቃልኪዳን አምባዬ የተሰጠ አጭር አስተያየት ነው።
አቡቸርዖሜጋ፥ «ነጻነት እንሻለን!» ብሏል።

Ethiopia State of Emergency Merkel (picture alliance / AP Photo)
ምስል picture-alliance/AP Photo

ኤሊያስ አያሌው፦ «ጦርነትም ተፈጥሯዊ አደጋም ሳይኖር ህዝብ ጥይቄ ስላነሳ እና ብጥብጥ ስለተከሰተ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ራሱ የስርአቱን ድክመት ወይንም ፀረ ዴሞክራሲ ለመሆን ሳይጠየቁ ቀጥቅጦ ለመግዛት ያለን ፍላጎት ያሳያል» ብሏል። አስተዋይ መሪ ቢኖር ባለፉት 6 ወራት ሁለት ነገሮች ሊወሰዱ ይችሉ ነበር ሲልም ያብራራል። «1ኛ በወቅቱ የተነሳውን ተቃውሞ እና ስርአት አልበኝነት ማስቆም:: 2ኛ በ6 ወራት ውስጥ ዘላቂ የመከላከል እርምጃዎችን ጎን ለጎን በመውሰድ ወደ ተለመደው ሰብአዊ መብቶችን ሳይሸራርፍ ማክበር ወደሚፈቅደው ሕገመንግስታዊ ስርአት መመለስ! ግን አሁን ያለን መንግስት ወይ አምባግገነንነት ተመችቶታል ወይም አቅመቢስ ሆኗል?» ሲል መልእክቱን አጠናቋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለአራት ወራት መራዘሙ ከመገለጡ አንድ ቀን ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ከኢህአዴግ እና ከተቃዋሚዎች ጋር የሚያደረገውን ቅድመ-ውይይት ድርድር ማቋረጡን አስታውቋል። ይኽን በተመለከተ በዋትስአፕ የደረሱንን የድምጽ መልእክቶች እናስከትል።

«ኢህአዴግ እና ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊያደርጉት ላቀዱት ድርድር የሦስተኛ ወገን አደራዳሪ አስፈላጊነት ላይ መሥማማት ተስኗቸዋል። ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው ድርድር ላለፉት 26 ዓመታት በኢህአዴግ ቁጥጥር ሥር በቆየው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ አንዳች ለውጥ የማምጣት አቅም ይኖረው ይሆን?» በሚል ላቀረብነው ጥያቄ ከተሰጡ አሰተያየቶች መካከል፥ ኢዮብ ብርሃነ ፤ «ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሉም አርዋሯጮች እንጂ! እውነተኛዎቹማ አስቸኳይ አዋጅ አውጆ ንጹሃን በግፍ ከሚገል ከሚያስር አውሬ ስርዓት ጋር ቁጭ ብለው አበል ለማግኘት አይኳትኑም ነበር! 100% አሸንፈናል ካሉ ለምን ውይይት ይጠራሉ?» ብሏል።

ዮሐና አብርሃም ደግሞ፦ «ተቃዋሚ ፓርቲ ብሎ የሰበሰባቸው አንዳችም ተጽዕኖ መፍጠር የማይችሉትን ነው። እንደማዘናጊያ ወይም ለዕድሜ ማራዘሚያ እየተጠቀመባቸው ነው።» ስትል፤ በረከት ዓማን፦ «ምንም ለውጥ አይመጣም መድረክ መውጣቱ ልክ ነው የቀሩትም ባይደራደሩ ይሻላል።» የሚል መልእክቱን አስፍሯል። 
እንዳለ ትዕዛዙ ደግሞ፦ «መከባበር ቢኖር ሁሉም ቀላል ነበር ግን ምን ያደርጋል ተቃዋሚዎች በነጮች ነው የሚያምኑት እድሜ ለኢህአዴግ ሁሉንም ላመጣው ግላዊ ሐሳብን ትታችሁ የሕዝብን ፋላጎት ተከተሉና ተወያዩ፤» ብሏል።

አቢይ አንጋ፦ «ድሮም ድርድሩ ለገዢው ፓርቲ ግዜ መግዣ እንጂ ትክክለኛ መፍትሔ ፍለጋ አይደለም» የሚል አስተያየት ሰጥቷል፡፡ ከመድረክ በተጨማሪ ሰማያዊ ፓርቲ ከትናንት በስትያ ከቅድመ ድርድሩ መውጣቱ ተዘግቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ