1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መዘዝ

ሰኞ፣ የካቲት 26 2010

እንደወታደር ተዋግተዉ፤ እንደ ምርኮኛ ታሥረዋል።እንደ ታጋይ ተፋልመዉ የፖለቲካ ፓርቲ መሥረተዋል።እንደ ጄኔራል የታንክ-መድፍ ርቀትን በሚሊ ሜትር እየቀመረ ከመልካዓ ምድር አቀማመጥ ጋር እያመጣጠነ-የሚተኩሰዉን ጦር መርተዋል።የኢትዮጵያን ትልቅ ክልል እንደ ርዕሰ መስተዳድር መርተዋል።ባለፈዉ አርብም እንደ አፈ-ጉባኤ ቁጥር ጠሩ።አስጨበጨቡም።

https://p.dw.com/p/2tjMG
Äthiopien - Parlament
ምስል DW/Y. Gebregziabher

ማሕደረ ዜና፤ የተቃዉሞ-ግጭት ግድያ ዑደት

የኢትዮጵያ መንግሥት ዋና ተባባሪ ደጓሚ፤ደጋፊ  መንግሥታት ተቃዉመዉታል።የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት ይዞታ የሚከታተሉ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች «ሕገ-መንግሥቱን የሚጥስ» ብለዉታል። የሕግ አዋቂዎች ተችተዉታል። አፈ-ጉባዉ ቁጥር አዛብተዉበታል። ግን ፀደቀ ተባለ። ሁለተኛዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ። ሕዝባዊ ተቃዉሞዉም ቀጠለ።አዋጅ እንቆጥራለን።አድማ፤ ተቃዉሞ ግጭት እንዘረዝራለን።አስከሬን-ቁስለኛ እናሰላለን።ቀን-ሳምንት-ወር እያልን ዘመን እንቀምራለን። ሶስተኛ ዓመት። ኢትዮጵያ፤ የመቶ ሚሊዮኖች ሐገር። የተቃዉሞ-ግጭት ግድያ ዑደት ምድር። እስከመቼ? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።

እንደወታደር ተዋግተዉ፤ እንደ ምርኮኛ ታሥረዋል።እንደ ታጋይ ተፋልመዉ የፖለቲካ ፓርቲ መሥረተዋል። እንደ ጄኔራል የታንክ-መድፍ ርቀትን በሚሊ ሜትር እየቀመረ ከመልካዓ ምድር አቀማመጥ ጋር እያመጣጠነ-የሚተኩሰዉን ጦር መርተዋል። ተለዋጭ ስማቸዉም ለጦር መሪነት የሰጠ ነዉ። አባ ዱላ። የኢትዮጵያን ትልቅ ክልል እንደ ርዕሰ መስተዳድር መርተዋል።የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ከሰባት ዓመት በላይ መርተዋል።ባለፈዉ አርብም እንደ አፈ-ጉባኤ ቁጥር ጠሩ። አስጨበጨቡም። አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳ።

Äthiopien - Parlament
ምስል DW/Y. Gebregziabher

የቀድሞዉ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዝደንት አቶ መለስ ዜናዊ በ1986 ዋሽግተንን በጎበኙበት ወቅት ካነጋገሯቸዉ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት አንዷ የአሜሪካ የተፈጥሮ ጥበቃ ድርጅት ኃላፊ ነበሩ።ወይዘሮዋ ከፕሬዝደንቱ ጋር ያደረጉትን ዉይይት እንዳበቁ «ለግራር ዛፍ የሚስማማዉን አፈር እና ዓየር ሳይቀር ጥቃቅን ነገሮችን የሚያስረዳ መሪ አጋጥሞኝ አያዉቅም» እያሉ አወድሰዋቸዉ ነበር።

ለጥቃቅን ነገሮችን ሳይቀር ጥንቃቄ የሚያደርጉት መሪ አንዴ ጄኔራል፤ ሌላ ጊዜ ሚንስትር፤ ደግሞ ሌላ ጊዜ ርዕሰ-መስተዳድር፤ እንደገና ሌላ ጊዜ አፈ-ጉባኤ እያሉ የሾሙ የሸለሟቸዉ ፖለቲከኛ ትልቁን አዋጅ ያፀደቀዉን ምክር ቤት አባላት ቁጥር እና ድምር አሳሳቱ።

የፍልስፍና ፕሮፌሰር ዶክተር ዳኛቸዉ አሰፋ እንደሚሉት ግን ሥለቁጥር ስሕተት የሚነገረዉ የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ ኢሕአዲግ ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ መቼ ፈቅዶ ያዉቅና ነዉ ይላሉ። የአምቦ ዩኒቨርስቲ መምሕርና የአምደ መረብ ፀሐፊ አቶ ስዩም ተሾመ እንደሚሉት ደግሞ ቁጥሩ ሥሕተት ከሆነ መታረም የሚገባዉ በራሱ በምክር ቤቱ ጉባኤ መሆን ነበረበት።ምክር ቤቱ ዳግም ተሰብስቦ ድምፅ መስጠት ነበረበት- አቶ ስዩም እንደሚሉት።

ከሁለት ሳምንት በፊት የሚንስትሮች ምክር ቤት ያወጀዉ፤ ባለፈዉ አርብ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፀደቀዉ የተባለዉ አዋጅ መደንገጉ  አቶ አስዩም አክለዉ እንዳሉት የሐገሪቱን ሕገ መንግሥት የሚፃረር ነዉ። ዶክተር ዳኛቸዉ የማርሻል ሕግ ይሉታል።

የሆነዉ በርግጥ ሆነ።አዋጁ በፀደቀ ማግስት ቅዳሜ እና ዕሁድ ከምዕራብ ሸዋ እስከ ምሥራቅ ወለጋ የሆነዉን እሱ «ያስጠላል» ይለዋል። ይኸኛዉ «የማይገመት ነገር።» ዛሬ-ወሊሶ የነበረውን አቶ ስዩም ይገልጹታል። በአብዛኛዉ ኦሮሚያም ተመሳሳይ ሁኔታ ነበር።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በሚቃወሙ ወገኖች ላይ ፀጥታ አስከባሪዎች ካለፈዉ አርብ እስከ ትናንት በወሰዱት እርምጃ በትንሽ ግምት አምስት ሰዎች መገደላቸዉን የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ዘግበዋል።ዛሬ ደግሞ አዋጁን የሚቃወሙ ወገኖች በመላዉ ኦሮሚያ የጠሩት የሥራ ማቆም አድማ ግጭት ግድያዉን አብሶታል።አድማዉን የሚከታተሉት ታዛቢ እንደገለፁት ካለፈዉ አርብ ጀምሮ በየአካቢዉ የተገደሉት ሰዎች ቁጥር መገናኛ ዘዴዎች ከዘገቡት በላይ ነዉ።

Äthiopien Protesten der Oromo in Bishoftu
ምስል REUTERS/File Photo/T. Negeri

በርግጥ ኢትዮጵያ ወዴት እየተጓዝዘች ነዉ? ዶክተር ዳኛቸዉ ወደ ጥሩም ወደ መጥፎም ይላሉ። መምሕር እና የአምደ መረብ ፀኃፊ ስዩም ተሾመ ደግሞ የኢትዮጵያን ገዢ ፓርቲ ጉዞ ከመጨረሻዉ ምዕራፍ የደረሰ ይሉታል። ዶክተር ዳኛቸዉ መጥፎ ያሉት እንዳይሆን የሐይማኖት መሪዎች፤ የሐገር ሽማግሌዎች እና ምሁራን የሚያደርጉት ካለ ጠየቅኋቸዉ።መለሱ የፍልስና ፕሮፌሰሩ  አይመለከተኝም እያሉ።

የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሬክስ ቲለርሰን ሰሞኑን ከሚጎበኟቸዉ የአፍሪቃ ሐገራት ኢትዮጵያ አንዷ ናት። አንድ የመስሪያ ቤታቸዉ ከፍተኛ ባለሥልጣን ባለፈዉ  አርብ ሥለ ጉብኝቱ በሰጡት መግለጫ የቀድሞዉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ያሉትን ጠቀሱ። «ኢትዮጵያ ሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ቦይንግ አዉሮፕላኖች በመግዛትዋ 35 ሺሕ አሜሪካዉያን ሥራ አግኝተዋል ብለዉ ነበር ጠቅላይ ሚንስትሩ» አሉ አሜሪካዊዉ ባለስልጣን። «ኢትዮጵያን ለመርዳት እናንተ አሜሪካዉያን ምን ታደርጉልናላችሁ?» አክለዉ ጠየቁ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሠላም፤ ፍትሕና ዴሞክራሲ እንዲያገኝ ቲለርሰንን መጠበቅ ዳግም አሜሪካኖችን መጠየቅ ይኖርበት ይሆን? ነጋሽ መሐመድ ነኝ እስኪ ቸር ያሰማን እንበል።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ