1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አስር ወራት የፀናዉ የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነሳ

ዓርብ፣ ሐምሌ 28 2009

ለአስር ወራት የዘለቀው የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነሳ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ የአገሪቱ ሰላም በመረጋጋቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ በሙሉ ድምፅ ወስኗል። የምክር ቤቱን እርምጃ ''አንድ እምርታ ነው'' የሚሉት ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በቂ እንዳልሆነ ግን ይናገራሉ። 

https://p.dw.com/p/2hilc
Äthiopien Protest
ምስል Reuters/T. Negeri

''አዋጁን ብቻ በማንሳት ሰላም ይመጣል ማለት አይደለም'' አቶ ሙላቱ ገመቹ

ድንገተኛው የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ለአስር ወራት የዘለቀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንስቷል።የምክር ቤቱ አባላት ውሳኔውን በሙሉ ድምፅ አፅድቀውታል። የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ ያወጀው ከደም አፋሳሽ ተቃውሞ በኋላ ባለፈው መስከረም ወር ነበር። በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሰላ ትችት የሚሰነዘርበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባለፈው በመጋቢት ለአራት ወራት ተራዝሞ ነበር። በኢትዮጵያ ተወካዮች ምክር ቤት ፅ/ቤት የመረጃ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ናምሴ አልቃ እንደሚሉት "ህግና ሥርዓትን ማስከበር" በመቻሉ ያለምንም ተቃውሞ የአስኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ ሆኗል። የኮማንድ ፖስቱ ዋና ተጠሪ የመከላከያ ሚኒሥትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ቀሪው ሥራ የክልሎች የጸጥታ ኃይሎች ሊከውኑት ይችላሉ ሲሉ ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።
"ኮማንድ ፖስቱ ቀሪ ሥራዎችን አስመልክቶ በየአካባቢው ያለው የፀጥታ ኃይል እና የመስተዳድር አካላት ሊፈጽሙት የሚችሉ እና ከእነሱ አቅም በላይ እንዳልሆነ ከየክልሉ የጸጥታ ኃይሎችም ሆነ የመሥተዳድር አካላት ጋር በመወያየት የጋራ መግባባት  ተፈጥሯል።"

የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ገቢራዊ ካደረገ በኋላ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ታስረዋል፤ተከሰዋልም። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀ-መንበር እና የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዶ/ር መረራ ጉዲናም የታሰሩት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚጥስ ተግባር ፈፅመዋል በሚል ተጠርጥረው ነበር። ከቀናት በኋላ የሚነሳው ይኸው አዋጅ መቀመጫቸውን በውጭ አገራት ያደረጉ መገናኛ ብዙኃንን መከታተልን ያግድ ነበር። የተቃውሞ ሰልፍ ማካሔድ፤የተቃውሞ ምልክት ማሳየትንም አግዶ ቆይቷል።

Infografik / Karte Protests and violence in Ethiopia,  2016

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ "ሰብዓዊ መብትን የሚያፍን" እንደነበር ይናገራሉ። አዋጁ ካልተነሳ በቀር ገዢው ግንባር ያቀረበውን የ"እንደራደር" ጥያቄ ፓርቲያቸው አልቀበልም ማለቱን የሚያስታውሱት አቶ ሙላቱ የዛሬውን የተወካዮች ምክር ቤት ውሳኔ "አንድ አምርታ" ይሉታል።

"ካሁን በፊት ከእኛ ፓርቲ ጋር ንግግር ለማድረግ እንደ ቅድመ-ሁኔታ አድርገን ያስቀመጥንው ይኼ አዋጅ እንዲነሳ ነው። ይኸ አዋጅ እያለ ንግግር ለማድረግ ሰውን ለመሰብሰብ ኃሳብ ለመለዋወጥ እንቅፋት ስለሆነ ሰላማዊ ንግግር ለማድረግ አያስችልምና ይኼ ቅድመ-ሁኔታ ይነሳ ብለን ጥያቄ አቅርበን መንግሥት አልተቀበለውም። አሁንም እንዲነሳ የእኛ ጥያቄ ነው። በመነሳቱ አንድ እምርታ ነው እንላለን።"

አንድ የተወካዮች ምክር ቤት አባል ግን "አሁንም አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይነሳ። የምናደርገውን እናደርጋለን" የሚሉ መኖራቸው አስግቷቸዋል። የሕዝብ ተወካዩ ለመከላከያ ሚኒሥትሩ ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ ግን "በአንድ አንድ ቦታዎች" አሉ ያሏቸውን እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መነሳት ይጠብቃሉ የተባሉትን ወገኖች ማንነት አልገለጡም። የመከላከያ ሚኒሥትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ "የብጥብጥ እና ኹከት ወሳኝ ኃይል" ያሏቸው በተለያየዩ አካባቢዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል ሲሉ ተናግረዋል። አሶሼትድ ፕሬስ በተቃውሞ ወቅት ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው የተጠረጠሩ 8,000 ሰዎች በእስር ላይ መሆናቸውን ዘግቧል።

"የተወሰኑ ጸረ-ሰላም ኃይሎች፤ጸረ-ልማት ኃይሎች ለመቀስቀስ ለመናገር ያስቡ ይሆናል። ነገር ግን ከሕዝቡ አምልጠው ወደ ዚህ አይነት ብጥብጥ ሊያስገቡ የሚችሉበት ሁኔታ የሌለ መሆኑን በሚገባ ማወቅ መረዳት ተገቢ ነው።ሁለተኛ ወሳኝ ኃይል የሚባለው ይኼ የብጥብጥ እና የኹከት ወሳኝ ኃይል የሚባለው ደግሞ በየአካባቢው በቁጥጥር ሥር ውሏል።"

Äthiopien Proteste Gebet
ምስል Reuters/T. Negeri

የመከላከያ ሚኒሥትሩ ተቃውሞ አይሎባቸው ከነበሩ አካባቢዎች መካከል በአማራ ክልል ከ143,000 በላይ ሚሊሻ አሰልጥናል ሲሉ ተናግረዋል። በኦሮሚያ፤አማራ እና የደቡብ ክልሎች የፖሊስ ሰራዊት አባላት ተጨማሪ ስልጠና መውሰዳቸውንም ገልጠዋል። አቶ ሙላቱ ገመቹ ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ይተቻሉ። 

"መንግሥት ውጥረቱን ለመፍታት ፤ ጊዜ ለመግዛት፤ ሕዝብን ዝም ለማሰኘት ጥያቄውን በወቅቱ ለመመለስ ባለመቻል {ተግባራዊ }የተደረገ አዋጅ ነው። አሁንም በእኛ በኩል አዋጁ በመነሳቱ የሕዝብ ችግር ተፈታ፤ ጥያቄ ሲቀርብበት፤ሕዝብ በአማራም በኦሮሞም በየቦታው ያለ ሁሉ ቅሬታውን ሲያሰማ የነበረው የመብት ጥሰት በመከሰቱ፤መልካም አስተዳደር በመጥፋቱ ፤ሰብዓዊ እና በህገ-መንግሥቱ የተሰጡት መብቶች በመታገዳቸው ፤ሰው ካለአግባብ በመታሰሩ፤ወታደር በየ ቦታው በመዝመቱ እና ሰላም በመጥፋቱ የተደረገ ነው። አሁንም አዋጁን ብቻ በማንሳት ሰላም ይመጣል ማለት አይደለም። ከዚህ ጋራ አብረው የሚሔዱ ነገሮች አሉ። ሕዝብ የጠየቃቸው መብቶች አሉ። እነዚያን ጥያቄዎች መመለስ ሕዝብን ያረጋጋዋል የሚል ግምት ነው ያለን።"

የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይጊ አዋጅ ያወጀው ከጎርጎሮሳዊው 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተቀሰቀሰ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ነበር። 


እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ