1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዋሽግተን-ሞስኮ እሰጥ አገባ

ሰኞ፣ ጥር 27 2011

የተለያዩ መንግሥታት የስምምነቱን መፍረስ ተቃዉመዉታል።የፖለቲካ ተንታኞችም መጪዉ ጊዜ የኑክሌር ጦር መሳሪያ  ስጋት የሚንርበት ይሆናል ባዮች ናቸዉ።ቅዳሜ የፈረሰዉ ስምምነት ታዛቢዎች እንደሚሉት የዓለምን ሠላም ለማስከበር ከመጥቀሙ እኩል ለቻይና ልዩ እድል ነበር የፈጠረላት።

https://p.dw.com/p/3ChmL
Sowjetunion 1988 US-Präsident Ronald Reagan & Präsident Michail Gorbatschow
ምስል picture-alliance/dpa/AFP

የአስጊዉ ጦር መሳሪያ አዲስ ሥጋት

የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ የጎርጎሪያኑ 2007 በባተ ማግሥት፣«ለሚወዷት» አዉሮጳ ያበረከቱት የዐዲስ ዓመት ስጦታ፣ ፖላንድና ቼክ  ዉስጥ የሚሳዬል መከላከያ ሚሳዬል የመትከል ዉሳኔያቸዉን ነበር። የሩሲያዉ አቻቸዉ ቭላድሚር ፑቲን ለአፀፋ እንደማይሰንፉ ዛቱ።የካቲት 2007 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር)።የዋሽግተን-ሞስኮዎች ዕቅድና ዛቻ ዓለምን ዳግም ከኑክሌር ጦር መሳሪያ ሥጋት እንደሚዶላት ባለሙያዎች መክሩ፣አሳስቡም። የፖላንድና የቼክ ሕዝብ በይፋ ተቃወመዉ።የሰማ እንጂ የተቀበለ የለም።ዉሳኔ-ዛቻዉ ለ11 ዓመት የገዘገዘዉን የጎርቫቾቭ-ሬገንን ዉል ትራም-በጠሱት፣ ፑቲን ጣሉት።ቅዳሜ።ሠላም ለማታዉቀዉ ዓለም ተጨማሪ የኑክሌር ስጋት።ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።

ጀርመኖች አስተከሉት።ጀርመኖች አደጋ አዩት።ጀርመኖች ተቃወሙት-አስነቀሉትም።ነገሩ እንዲሕ ነዉ፣-መጋቢት 1976 ሶቭየት ሕብረት SS-20 የተባለዉን ኑክሌር አወንጫፊ ሚሳዬል ለምዕራብ አዉሮጳ እሚቀርበዉ ግዛትዋ ዉስጥ አጠመደች።

ኑክሌር ተሸክሞ 5000 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ኢላማዉን የሚመታዉ ሚሳዬል መተከሉ ዩናይትድ ስቴትስን ማሳሰቡ አልቀረም።ይሁንና የያኔዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት የጂሚ ካርተር መስተዳድር በፍጥነት የማይንቀሳቀሰዉን የሶቬቶች የሚሳዬል ጣቢያ ስልታዊ በተባለዉ የኑክሌር ቦምብና ቦምቡን መጣል በሚችሉት ፈጣን አዉሮፕላኖች ማጋየት «አይገድም» በሚል አፀፋ እርምጃ ለመዉሰድ አልፈለገም ነበር።

Pershing II Raketen US Mittelstreckenrakete
ምስል Frank Trevino/US Department of Defense

የያኔዉ የምዕራብ ጀርመን  መራሔ መንግስት ሔልሙት ሽሚት በ1977 ባደረጉት ንግግር ግን የሶቭየቶች ሚሳዬል ምዕራብ አዉሮጳን እንደሚያሰጋ አስታዉቀዉ ዩናይትድ ስቴትስ አፀፋ እርምጃ እንድትወሰድ አሳሰቡ።

ማሰሰቢያዉ  የምዕራብ አዉሮጳ መንግስታትን አሳድሞ፣አሜሪካኖችንና መላዉ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) አባል መንግስታትን አሳመነ።የድርጅቱ ሚንስትሮች በ1979 ባደረጉት ስብሰባ ባንድ በኩል፣ዩናይትድ ስቴትስ ከሶቬት ሕብረት ጋር እንድትደራደር በሌላ በኩል ደግሞ Pershing II የተባለዉ የዩናይትድ ስቴትስ ኑክሌር አወንጫፊ ሚሳዬል ምዕራብ ጀርመን፣ ቤልጂግ፣ኢጣሊያ፣ሆላንድና ብሪታንያ ዉስጥ እንዲጠመድ «መንታ-ጎዳና» የተባለዉን ዉሰኑ።

የጂሚ ካርተር መስተዳድር ሁለቱንም ዉሳኔዎች ገቢር ለማድረግ አንድ ሁለት ማለት እንደጀመረ ካርተር በ1980ዉን ምርጫ በወግአጥባቂዉ ፖለቲከኛ በሮናልድ ሬጋን ተሸንፈዉ ከስልጣን ወረዱ።

ሬጋን  በ1981 ማብቂያ «ዜሮ-ዜሮ» ባሉት መርሕ መሠረት እስከዚያ ጊዜ ድረስ ከተጠመዱት ሌላ ተጨማሪ የአሜሪካ ሚሳዬሎች አዉሮጳ ዉስጥ መጠመዳቸዉን አስቁመዉ፣ሊዮንድ ብሬዥኔቭ ከሚመሩት የሶቭየት ሕብረት መንግስት ጋር ይደራደሩ ገቡ።

ድርድሩ በዉዝግብ፣ፉክክር፣ ጥርጣሬ፣ ዳተኝነት፣ በሶቮየቶች መዳከምም እየተደነቃቀፈ ደንበር ገተር በሚልበት መሐል-ምዕራብ ጀርመኒቱ ከተማ ሐይልብሮን አጠገብ በሚገኘዉ የአሜሪካኖች የሚሳዬል ጣቢያ የሆነዉ-ሆነ።

Russland Pressekonferenz zur Vorstellung neuer Raketen
ምስል picture-alliance/Sputnik/V. Astapkovich

«አስደጋጭ» ይሉታል ያኔ የሚሳዬል ጣቢያዉን ይጠብቁ ከነበሩት የአሜሪካ ወታደሮች አንዱ ላሪ ኒኮላስ።«አስደንጋጭ ነበር።ማለቴ የምናወራዉ ሥለኑክሌር ተሸካሚ ነዉ፤ ሥለ ሚሳዬል ሞተር ነዉ።በዚያ የቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍጥጫ በናረበት ወቅት እንዲያ ዓይነት ነገር መሆኑ---መላዉ ዓለምን ነበር ያስጠነቀቀዉ።»

ሕዳር 11 1985።ለትልቂቱ የደቡብ ምዕራብ ጀርመን ከተማ ሐይልብሮን ነዋሪ ሕይወት ያዉ የወትሮዉ ነዉ።በረዶ-ቅዝቃዜ፣ሩጫ፣ የገና ዝግጅት፣ ሸመታና የወትሮዉ ጥድፊያ።ከተማይቱ የተንተራሰችዉ ሐይደ የተሰኘዉ ጫካም እስከዚያች ሰዓት ድረስ ያዉ እንደወትሮዉ ወዲያ ወዲሕ ከሚሉበት ጥቂት ወታደሮች በስተቀር በበረዶ ተሸፍኖ የከተማይቱን ጫጫታ፣ቱማታ፣ በዝምታዉ እየዋጠ፣ በፀጥታ ያንጎላንጃል።

የDW ጋዜጠኛ ፋቪያን ፎን ፎን ዴር ማርክ እንደዘገበዉ ያጫካ-ዛሬም ያኔ ግን ከዚያች ሰዓት በፊትና በኋላ ከነበረዉ ብዙም አልተለወጠ።ያቺ ሰዓት።አሜሪካኖች እዚያ ጫካ ዉስጥ በቆፈሩት ዋሻ ካከማቹት ሚሳዬል አንዱ ፈነዳ።

የመኪና-ባቡር-ፋብሪካ ኩርኩርታ፣ የሕዝብ፣ ሆይሆይታ ቱማታ ጫጫታን እየቀለበ የሚዉጠዉ ደን ለዓመታት የዋጠዉን ጩኸት የተፋ ያክል በረባሽ ድምፅ ተርገበገበ።ፍንዳታዉ ሰወስት ወታደሮች ገደለ።16 አቆሰለ።ከሁሉም በላይ የዚያን ጫካ ሚስጥር መጀመሪያ ለሐይልብሮን ነዋሪዎች፣ ቀጥሎ ለጀርመን አሰልሶ ለዓለም አጋለጠ።

  «አደጋዉ እዚሕ እላይ ያለዉ ነገር ምን ያሕል አደገኛ እንደሆነ አረጋገጠ።እንዲሕ ዓይነት አደጋ ይደርሳል ብዬ አላሰብኩም ነበር።ብቻ ማረጋገጪያ፣ ሕዝቡንም አነቃ።በአስር ሺሕ የምንቆጠር ሰዎች ፣ ለተቃዉሞ አደባባይ መዉጣት የጀመርነዉም ከዚያ ጊዜ በኋላ ነዉ።»

ወይዘሮ ሱዛነ ሁበር።እሳቸዉም ባለቤታቸዉም የኑክሌር ጦር መሳሪያን የሚቃወመዉ የሐይልብሮን የሠላም ምክር ቤት የተባለዉ ስብስብ አባላት ናቸዉ።የፈነዳዉ ሚሳዬል፣ እንጂ የኑክሌር ቦምብ አለመሆኑ ኋላ ተረጋግጧል።ተቃዉሞዉ ግን ቦን ላይ ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ካሰለፈ በኋላ በድፍን አዉሮጳ ከዚያም በዓለም ተዛምቶ ዓለም አቀፍ ንቅናቄ ሆኗል።

USA Elko  Trump Statement
ምስል Reuters/J. Ernst

ሕዝባዊዉ ግፊት፣ ሶቭየት ሕብረት ከተደረገዉ የመሪዎች ለዉጥ ጋር ተዳምሮ ፕሬዝደንት ሮናልድ ሬገንና ዋና ፀሐፊ ሚኻኤል ጎርቫቾቭ INF የተባለዉን ስምምነት እንዲፈራረሙ አስገድዷል።1987።

 «ይሕ ሥርዓትና የምንፈርመዉ ሥምምነት ለትዕግሥት ዉጤት እጅግ በጣም ጥሩ ምሳሌዎች ናቸዉ። ከስድት ዓመታት በፊት ሕዳር 1981 ነበር-ዜሮ አማራጭ የሚለዉን ሐሳብ ያቀረብኩት።ሐሳቡ ትጥቅን እንደማስፈታት ቀላል ነበር ማለት ይቻላል።ከዚሕ ቀደም እንደነበሩት ስምምነቶች የነበረዉን መቀነስ ወይም አዲስ የጦር መሳሪያዎችን ክምችት የሚገታ ብቻ አይደለም።የጦር መሳሪያ ሽቅድምድምን የሚያስቆምም ብቻ አይደለም።በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር የሚለዉ ቋንቋ የጦር መሳሪያ ቅነሳ በሚለዉ ተለዉጧል።በዚሕ (ዉል) መሠረት የሶቬየትና የዩኤስ የኑክሌር ሚሳዬልን ማጥፋት ነዉ።»

በርግጥም በስምምነቱ መሠረት ዩናይትድ ስቴትስ 846፣ ሶቭየት ሕብረት ደግሞ 1ሺሕ 846 የአጭርና የመካከለኛ ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳዬሎቻቸዉን አጥፍተዋል።በጀርመኖች ግፊት ጀርመንን ጨምሮ በብዙ የአዉሮጳ ሐገራት የተጠመደዉ አደገኛ ጦር መሳሪያ ሐይልብሮን-ጀርመን ፈንድቶ፣ ጀርመኖች ጀምረዉት፣ ዓለምን ባዳረሰዉ ተቃዉሞና ግፊት ተነቀለ ወይም ወደመ።

እስከ 2007 መጀመሪያ ድረስም አዉሮጳ ሰወስተኛዉ የዓለም ወይም ምናልባትም የመጀመሪያዉ የኑክሌር ጦር ዉጊያ ይጫርባታል የሚለዉ ሥጋት ቀንሶ ነበር።በ2002 ኋይት ሐዉስን የተቆጣጠሩት የኒዮ-ሊብራል አክራሪ ፖለቲከኞች ግን የቀነሰዉ ሥጋት በነበረበት እንዲቀልጥል አልፈለጉም፣ ወይም የበላይነታቸዉን ከማረጋገጥ ባለፍ መዘዙን በቅጡ አላጤኑትም።

ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ኢራቅን ባጠፉ በአራተኛ ዓመቱ አዉሮጳ ላይ ፀረ-ሚሳዬል-ሚሳዬል ለመትከል መወሰናቸዉ በሬጋን-ጎርቫቾቭ ዉል የፀናዉን ሠላም አናግቶታል።የቡሽ መስተዳድር ሩሲያ ጥግ ፖላንድ ላይ ሊተክል ያቀደዉ ፀረ-ሚሳዬል-ሚሳዬልና ቼክ ሪፐብሊክ ላይ ሊያቋቁም ያሰበዉ ሬዳር ከኢራን የሚተኮስ ሚሳዬልን ለመከላከል የሚል መሸፋፈኛ ሊያቀርብለት ሞክሮ ነበር።

Deutschland Pershing-II Rakten - USA will INF-Vertrag aufkündigen
ምስል picture-alliance/dpa/H. Melchert

የሩሲያ ፌደሬሽን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ማርሻል ዩሪ ባሉየቭስኪይ የዋይት ሐዉስ ማማኸኛን ሩሲያን «እንደማጃጃል» ነበር የቆጠሩት።በርግጥም ከመካከለኛዉ ምሥራቅ ኢራን የሚተኮስ ሚሳዬልን ለመከላከል ምሥራቅ አዉሮጳ ላይ ሚሳዬል መትከል ለጦር አዋቂዎች አይደለም ለተራዉ ሰዉም  አመክንዮ አልባ ማማሐኛ ነበር።

የፕሬዝደንት ጆር ቡሽ ዉሳኔ እንደተሰማ ለአፀፋ የዛቱት የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በ2008 SSC-8 የተሰኘዉን ሚሳዬል አሰሩ።ሩሲያ በ2014ም ሌላ ሚሳዬል ሠራች።የጀርመኑ የፀጥታ ጉዳይ ተኝታኝ ማርኩስ ካይም እንደሚሉት ፕሬዝደንት ባራክ ኦቦማ የሩሲያን እርምጃ «ደበቅ» አድርገዉ፣ ጉዳዩን በድርድር ለመጨረስ ሞክረዉ ነበር።

የትራምፕ መርሕ ግን የተፈጥሮ ጥበቃ ይሁን-የንግድ ስምምነት፣ የኢራን ኑክሌር ይሁን-የየሩሳሌም ጉዳይ፣ የስደተኛ ይሁን-የጤና ሕግ ኦባማ የጀመሩ፤የፈረሙትን ዉል ማፍረስ ነዉ።አልካዱምም።«ሩሲያ ስምምነቱን ጥሳለች።ለብዙ ዓመታት ሲጥሱ ነበር።ፕሬዝደንት ኦባማ ለምን እንዳልተደራደሩ ወይም ከስምምነቱ እንዳልወጡ አላዉቅም።የኑክሌር ስምምነቱን ጥሰዉ እኛ መስራት የተከለከልነዉን መሳሪያ እንዲሰሩ አንፈቅድላቸዉም።እኛ ስምምነቱን አክብረናል።ሩሲያ ግን እንዳለመታደል ሆኖ አላከበረችም ሥለዚሕ ከስምምነቱ እንወጣለን።»

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራም ጥቅም 2018።ዝተዉ አልቀሩም-አርብ።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፒዮ-መንግስታቸዉ ከቅዳሜ ጀምሮ ከስምምነቱ መዉጣቱን አወጁ።«ሩሲያ፣ የዩናይትድ ስቴትስን የፀጥታ ጥቅም ጎድታለች።ከእንግዲሕ ሩሲያ ያለምንም ሐፍረት በምትጥሰዉ ስምምነት ልንዛ እንችልም።ሩሲያ ሊጣራና ሊረጋገጥ በሚችል መልኩ፣ በሚቀጥሉት ስድስት ወራት ዉስጥ፣ ስምምነቱን የሚጥሱ ሚሳዬሎቿን፣ ማስፈንጠሪያዎቿንና ተያያዥ መሳሪያዎችዋን በማጥፋት ስምምነቱን ካላከበረች፣ ስምምነቱ ሙሉ በሙሉ ይፈርሳል።»

የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲንም ሐገራቸዉ ከስምምነቱ መዉጣትዋን አዉጀዋል።«ዩናይትድ ስቴትስ ስምምነቱን ስታከብር እናከብራል።ስታፈርስ እናፈርሳለን» ይላሉ ፑቲን።ዉጪ ጉዳይ ሚንስትራቸዉ ሠርጌይ ላቭሮቭ ደግሞ የዩናይትድ ስቴትስን ዉሳኔ «ሥጋት» ብለዉታል።«የቀዝቃዛዉ ጦርነት መለያ እንደነበረዉ፣የጦር መሳሪያ ምርት እሽቅድምድም ዉስጥ አንገባም።ፕሬዝደንንቱ ፑቲን በግልፅ አስቀምጠዉታል።እርግጥ ነዉ፣ዩናይትድ ስቴትስ ከአጭርና ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ የኑክሌር ሚሳዬል ሥምምነት በመዉጣታዋ የፈጠረችዉን ሥጋት ለመቋቋም ወታደራዊና ቴክኒካዊ አቅምን መጠቀማችን አይቀርም።»

Russland Ausstieg INF-Abrüstungsvertrag
ምስል picture-alliance/dpa/A. Nikolsky

የተለያዩ መንግሥታት የስምምነቱን መፍረስ ተቃዉመዉታል።የፖለቲካ ተንታኞችም መጪዉ ጊዜ የኑክሌር ጦር መሳሪያ  ስጋት የሚንርበት ይሆናል ባዮች ናቸዉ።ቅዳሜ የፈረሰዉ ስምምነት ታዛቢዎች እንደሚሉት የዓለምን ሠላም ለማስከበር ከመጥቀሙ እኩል ለቻይና ልዩ እድል ነበር የፈጠረላት።

ሁለቱ ኃያላን መንግሥታት ስምምነቱን ሲፈራረሙ እንደስጋት ያላይዋት ቻይና ዛሬ የዘመናዊዉ የኑክሌር ሚሳዬል አምራች ሆናለች።የጦር መሳሪያ አዋቂዎች እንደሚሉት ቻይና በስምምነቱ ከታገደዉ ከ5000 ኪሎ ሜርትር ርቀት በላይ የሚወነጨፍ ሚሳዬል አምርታለች።

አሁን የስምምነቱ መፍረስ ዩናይትድ ስቴትስ የቻይናን አዳዲስ ሚሳዬሎች የሚገታ ሚሳዬል ለማምረትና እስያ ላይ ለመትከል ይረዳታል ባዮች አልጠፉም።ግን ከምዕራብ መጣ-ከምሥራቅ ኑኬሌር መሆኑ ነዉ-ክፋቱ።

ነጋሽ መሐመድ 

ኂሩት መለሰ