1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሸባሪዎች ጥቃትና ፀረ-ሽብር ዘመቻ

ሰኞ፣ ሰኔ 22 2007

አል-ቃኢዳ የተፈለፈለ፤የተመሠረተ፤ የተሠራጨዉ በ እና ከመንግሥት አልባዋ አፍቃኒስታን ነበር።የISIS የተመሠረተ፤ የተጠናከረ፤ የተሠራጨዉም ጠንካራ መንግሥት አልባዋ ኢራቅ ነዉ።ፈጥኖ የተዛመዉ ወደምትወድመዉ ሶሪያ እና ወደ ፈራረሰችዉ ሊቢያ ነዉ።መንግሥት አልባዋ የመን እያሰለሰች ነዉ

https://p.dw.com/p/1Fpl5
ምስል Reuters/Z. Bensemra

የአሸባሪዎች ጥቃትና ፀረ-ሽብር ዘመቻ

አንድ ቀን-አርብ። አንድ ድርጅት-ISIS ዳዓሽ። ሰወስት ሰዓት። ከአምስት እስከ ስምንት። ሰወስት ክፍለ-ዓለማት-አዉሮጳ፤ አፊሪቃ፤እስያ። ወይም ሰወስት ሐገራት ፈረንሳይ፤ ቱኒዚያ፤ ኩዌይት። ሰወስት ወጣቶች። ሰወስት ሽብር። የከሥልሳ በላይ ሰዎች ሞት። የሽብሩ እንዴትነት፤ የፀረ-ሽብሩ ዉጊያ እስከየትነት ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ። አብራችሁኝ ቆዩ።

ጊዜዉ አጭር ነዉ። በዚያ ላይ ይሮጣል። እሱም ተጣድፏል 35 ዓመቱ ነዉ። ፈረንሳዊዉ ሾፌር። የጭነት መኪናዉን እያሮጠ ከጋስ ፋብሪካዉ እጥር ግቢ ደረሰ። ሳይንት-ኳንቲን። ዘቦቹ ሥለሚያዉቁት ምንም-ሳያንገራግሩ ወደ ዉስጥ እንዲዘልቅ ፈቀዱለት። የአሜሪካኖቹ ፋብሪካ ጋስ ማምረቻ ነዉ። በቀለሉ ተቀጣጣይ ። ሰወዬዉ አጥፍቶ-ለመጥፋት ሥሥ ኢላማ መርጧል።

«3 ሰዓት ከ35 የመጀመሪያዉ ፍንዳታ ተሰማ።» ይላል የአሜሪካዉ ቴሌቪዥን ጣቢያ። ኤቢሲ። በአካባቢዉ የነበሩት የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች በቅፅበት ደረሱ። ከጋየዉ መኪና አጠገብ በካራ-የታረደ የአንድ ሰዉ ጭንቅላትና በአረብኛ የተፃፉ ሐይማኖታዊ ጥቅሶች አገኙ። ገልመጥ ሲሉ ሰዉዬዉ ጠርሙስ ለመክፈት ሲታገል አዩ። እሱ ነዉ። አለቃዉን በካራ አርዶ-ገድሏል። የኬሚካሉን ፋብሪካ በኬሚካል ሊያጋይ ኬሜካል የተሞላበትን ጠርሙስ ለመክፈት ይታገላል።

የእሳት አደጋ ተከላካዮቹ እሳቱን ከምንጩ የሚያጠፉበትን ብልሐት ለማወቅ-ማሰብ ማሰላሰል አላስፈለጋቸዉም። ጊዜዉም የለም። ሰዉዬዉ ላይ ተከመሩበት። ከቀኑ አራት ሰዓት፤- ሁሉም ተጠናቀቀ። የብራስልስ ጉባኤያቸዉን አቋርጠዉ ወደ ፓሪስ የተመለሱት የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ፍራንሷ ኦላንድ እንዳሉት የእስት አደጋ ሠራተኞቹ አሸባሪዉን ባይዙት ኖሮ ከሻርሊ ኤብዶዉ ጥቃት በቅጡ ያልተፅናናችዉ ፈረንሳይ ሌላ ከባድ ጥፋት ይደርስባት ነበር። ጀርመናዊቷ የፖለቲካ አጥኚ ክሌር ደመስማይ ከባድ ጥፋት ሊደርስ ይችል እንደነበር አልተከራከሩም። የጀርመንና የፈረንሳይን ግንኙነት የሚያጠኑት ደመስሜይ ሙከራዉን ራሱን አስገራሚ ይሉታል። በጣም ያስገረማቸዉ ግን ባለፈዉ ጥር ሻርሊ ኤብዶ ከተጠቃ በኋላ የፀጥታ አስከባሪዎች ክትትል፤ ቁጥጥርና ጥንቃቄ ሳይላላ ሌላ ጥቃት መቃጣቱ ነዉ።

«ፈረንሳይ ዉስጥ ዳግም ጥቃት መሠንዘሩን በማየቴ በጣም ነዉ የተገረምኩት። በሐገሪቱ ያለዉን ዉጥረት ለተመለከተ ግን እጅግ በጣም የሚያስገርመዉ ጥቃት መሰንዘሩ አይደለም።ፓሪስ ዉስጥ ብዙ ተቋማት በተለይ ምኩራቦች እና የአይሁድ ትምሕር ቤቶች በፖሊስ ሲጠበቁ ይታያሉ። የማስጠንቀቂያዉ ደረጃ አልቀነሰም። ይሕ ሁሉ ፈረንሳይ አሁንም በተጠንቀቅ መቆሟን ያመለክታል።»

ከማሊ-እስከ ኮትዲቯር፤ ከማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ እስከ ጀቡቲ፤ ከኢራቅ እስከ ሶሪያ ባሠፈረች ወይም ባዘመተችዉ ጦሯ «ጠላት» የምትላቸዉን ቡድናት ወይም ሐይላት የምትወጋዉ፤ የምታዋጋዉ ፈረንሳይ አፀፋ ጥቃት እንዳይደርስባት መጠንቀቅ በርግጥ አይበዛባታም። ጥበቃ፤ ጥንቃቄዉ ግን ከሌላ ጥቃት ያዉም ከራስዋ ከፈረንሳይ በቀል አጥቂዎች ሊያድናት አለመቻሉ እንጂ ዚቁ።

የአሜሪካዉን የኬሚካል ፋብሪካ ለማጋየት የሞከረዉ ግለሰብ ከዚሕ ቀደም ከፅንፈኞች ጋር ግንኙነት እንደነበረዉ የፈረንሳይ ባለሥልጣናት አስታዉቀዋል። ይሁንና ሰዉዬዉ እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ወይም ደዓሽ ብሎ የሚጠራዉ ድርጅት አባል ሥለመሆን አለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።

Tunesien Gedenkfeier für die Opfer des Anschlags
ምስል Reuters(Z. Bensemra

የፈረንሳዩ ጥቃት እንዴትነት፤ የደረሰዉ ጥፋት እስከምንነት፤ የአጥቂዉ ማንነት ገና በቅጡ ሳይተነትን ከቀድሞዋ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዢ ከቱኒዚያ ሌላ የሽብር ጥቃት ተሰማ። ባገሬዉ አቆጣጠር ከቀኑ ስድሰዓት ግድም ነዉ። በዉቧ የመዝናኛ ከተማ ሶሴ ባሕር ዳር የተንጣለለዉ ዘመናይ የቅንጦት ሆቴል በጥይት ሩምታ ተደበላለቀ።

ያዩ ይናገራሉ።«መዋኛዉ ሥፍራ ጋደም ብለን ነበር። ባንዴ ተኩስና ጫጫታ ሰማን። ወዲያዉ ባሕር ዳርቻ የነበሩ ሶዎች እየተሯሯጡ መጡ። ከተንጋለልኩበት ዘልዬ የሚሮጡትን ተቀላቀልኩ።በጣም ነዉ የፈራነዉ።ከዚያ በኋላ (ከሆቴሌ) ምድር ቤት ዉስጥ ተሸሸግን።ከዚያ አካባቢ መሔድ ነዉ የፈለግነዉ። መሔድ።

ሌለኛዋ አከሉበት።

«ወደ ሐገሬ መሔድ እፈልጋለሁ።እዚሕ መቆየት አልፈልግም።ይሕ ጥቃትና ያሁሉ የሞተዉ ሰዉ ቀልድ አይደለም።»

በርግጥ ቀልድ አልነበረም።ሰላሳ-ሰምንት ሰዎች ተገድለዋል።በርካታ ቆስለዋል።ከተገደሉት ከግማሽ የሚበልጡት የብሪታንያ ዜጎች ናቸዉ።የቱኒዚያ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት የቤልጂግ፤የጀርመን፤ የአየር ላንድና የፖርቱጋል አንዳድ ዜጎችም ተገድለዋል።ሐገር ጎብኚዎቹን በጥይትና በእጅ ቦምብ የገደለዉ ወጣትም በፀጥታ አስከባሪዎች ተገድሏል።

ገድሎ-ተገዳዩ የሃያ-አራት ዓመት ወጣት ነዉ።የመቀጠር፤ በግሉ የመሥራት፤ በትምሕርቱ የመቀጠል ሠፊ እድል የነበረዉ አዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቅ።ፖሊስ እንዳለዉ የወጣቱ ተንቀሳቃሽ ስልክ ሜድትራኒያን ባሕር ዉስጥ ተገኝቷል።ለመጨረሻ ጊዜ የደወለዉ ለአባቱ ነበር።ፖሊስ አባትዬዉን በጥርጣሬ አስሯቸዋል። «ልጄን ወዲዚሕ የመራዉን ፈጣሪ ይወቀዉ።»ይላሉ ቅጥ ባጣ ሐዘን የተቆራመዱት አባት።«ልጄን፤ ሰዉ ግደል ብዬ አላሳደግሁትም።» አከሉ።

አሸባሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አይ ሲ ስ ሐላፊነቱን ወስዷል።ቱኒዚያ በ2011 (እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር) የተቀጣጠለዉ የአረብ ሕዝባዊ አብዮት ያለ ብዙ ደም መፋፈስ ሕዝባዊ ለዉጥ ያመጣባት፤ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የጣለባት ብቸኛዋ ሐገር ናት።ግን የሊቢያ ጎረቤት።ሕዝባዊዉ አብዮት ብልጭ ባለበት ቅፅበት ወደ እርስ በርስ ግጭት የተለወጠባት፤ የርስ በርስ ግጭት ገና ከመጀመሩ የምዕራባዉያን መንግሥታት ጦር የያኔዎቹን አማፂያንን በመደገፍ ጣልቃ ገብቶ የደበደባት ሊቢያ የሐገር መንግሥትነቱ ሥርዓት ከጠፋባት እነሆ አራተኛ ዓመቷን አገባደደች።

Frankreich Paris Saint Quentin Fallavier Anschlag Gasfabrik
ምስል picture-alliance/dpa/M. Becker

በዚሕ አራት አመት ዉጥስ ከሚተራመሱባት ታጣቂዎች ወይም አሸባሪዎች አንዱ እራሱን እስላማዊ መንግሥት የሚለዉ ቡድን ነዉ።ቡድኑ በየሥፍራዉ የሚወጉትን መንግሥታት ዜጎች ወይም ተባባሪዎቻቸን ለመጥፋት ከሊቢያ ሻገር እያለ ቱኒዚያን ኢላማዉ ማድረግ ብዙም አልከበደዉም።ቡድኑ ባለፈዉ መጋቢት እዚያዉ ቱኒዚያ ዉስጥ በሐገር ጎብኚዎች ላይ በጣለዉ ተመሳሳይ ጥቃት ሃያ-አንድ ሰዎች ገድሎ ነበር።

የቱኒዚያ መንግሥት ከመጋቢቱ ጥቃት በኋላ የአክራሪዉ ቡድን አባላት ወይም ደጋፊዎች ብሎ የጠረጠራቸዉን በርካታ ሰዎች አስሯል።ፅንፈኝነት ይሰበክባቸዋል ያላቸዉን ሰማንያ መሳጂዶችን ዘግቷልም።የአርቡን ጥቃት ማቆም ግን አልቻለም።የሶሴዉን ግድያ ካዩት አንዱ፤ ሽብርን ለማስቆም አብነቱ መተባበርን ነዉ ይላሉ።

«እንደ አንድ ማሕበረሰብ አሸባሪነትን ለመዋጋት በጋራ መቆም አለብን።በአብዮቱ ወቅት የነበረንን በጋራ የመቆም ስሜት ዳግም ማሰብ አለብን።ለነፃነታችንና ለሠብአዊ መብት መከበር በአንድነት በአደባባይ እንደታገልን ሁሉ፤ በአንድነት ከቆምን አሸባሪነትን ድል ማድረግ እንችላለን።»

እንዴት? ለመመለስ አይደለም ለመጠየቅም ጊዜ አልነበረም።ኩዌት ሌላ ሽብር አለ።የኩዌት ኤምሬት ባለሥልጣናት ኋላ እንዳስታወቁት ሳዑዲ አረቢያዊዉ ወጣት ከሳዑዲ አረቢያ በማናማ-ባሕሬን አድርጎ ኩዌት ሲቲ የገባዉ የዚያን ቀን ማለዳ ነዉ።አርብ።የዓለም መገናኛ ዘዴዎች የፈረንሳዩንና የቱኒዚያዉን ጥቃት እየተቀባበሉ በሚያራግቡበት መሐል ወጣቱን ያሳፈረዉ መኪና ኢማም ሳዲቅ መስጊድ ቅጥር ግቢ ገባ።

Sousse Tunesien Stadtansicht
ምስል picture-alliance/dpa/B. Schakow

የሃያ-ሰወስት ዓመቱ ወጣት ቦምቡን እንዳሸረጠ ወደ መስጊዱ ዘለቀ።ዙሁር ወይም ቀትር ነዉ።በዚያ ላይ የቅዱሱ ወር የረመዳን -ታላቅ ቀን።ጁምዓ።አርብ።የሺዓዎቹ መስጊድ ሁለት ሺሕ ያሕል ምዕመናን ተጨናንቀዉበታል።ፈጣሪን ሊማፀኑ።ስግደት፤ዱዓ፤ምልጃዉ በአስደንጋጭ ፍንዳታ ተጠቋረጠ።ሽብር።ሃያ ሰባቱ ሞቱ።መቶዎች ቆሰለ።

እራሱን የኢራቅና የሶሪያ እስላማዊ መንግሥት (ISIS) ብሎ የሚጠራዉ ቡድን ወጣቱን አጥፍቶ ጠፊ ማዝመቱን አረጋግጧል።ቡድኑ መናፍቅ የሚላቸዉን ወገኖች በተለይም ሺዓዎችን በቅርብ ቀን እንደሚገድል ከጥቂት ቀናት በፊት ዝቶ ነበር።

ኩዌትን ኢላማ ያደረገበት ምክንያት ግን በዉል አልተነገረም።እርግጥ ነዉ የሺዓዎች ሐራጥቃ ሐገር፤ ተቆርቃሪም ተደርጋ የምትቆጠረዉ ኢራን ሶሪያና ኢራቅ ዉስጥ አክራሪዉን ቡድን ትወጋለች።በቴሕራን የሚደገፉት የደማስቆና የባግዳድ መንግሥታትም አንድም ሺዓ አለያም ለሺዓ የሚቀርበዉ የአላዊት ሐራጥቃ ተከታዮች ናቸዉ።

Kuwait Anschlag Beerdigung
ምስል picture-alliance/dpa/R. Qutena

ከአይሲስ ጋር የሚደረገዉን ዉጊያ ወይም ፀረ-ሽብር የሚባለዉን ዘመቻ በግልፅ ቋንቋ መበየን አስቸጋሪ ነዉ።ብቻ ዩናይትድ ስቴት እና ኢራን ጠላት ናቸዉ።ዩናይትድ ስቴትስና ሳዑዲ አረቢያ ወዳጆች ናቸዉ።ሳዑዲ አረቢያ እና ኢራን ጠላት ናቸዉ።ሳዑዲ አረቢያ ኩዌትን ጨምሮ የፋርስ ባሕረ-ሠላጤ አካባቢ መንግሥታትን በበላይነት ትመራለች።ከግብፅ መዳከም በኋላማ የሪያድ ነገስታት መላዉን ዓረብ ከሆነላቸዉም መላዉን ሙስሊም ዓለም ለመምራት እየተንጠራሩ ነዉ።

ኢራንና ሶሪያ፤ ኢራንና ኢራቅ ወዳጆች ናቸዉ።ዩናይትድ ስቴትስ፤ የምዕራብም፤ የምሥራቅም ወዳጆችዋና ተባባሪዎችዋ በነሳዑዲ አረቢያ ከሚመሩት አረቦች ጋር ሆነዉ ባንድ በኩል የሶሪያን መንግሥት የሚወጉ ሐይላትን ያስታጥቃሉ።ኢራንና በኢራን የሚደገፈዉ የሊባኖሱ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሒዝቦላሕ የደማስቆ መንግሥትን ደግፈዉ በዩናይትድ ስቴትስ፤ በሳዑዲ አረቢያና በተባባሪዎቻቸዉ የሚደገፉ አማፂያንን ይወጋሉ።

የሶሪያን መንግሥት ከሚወጉት አማፂያን አንዱ ISIS ነዉ።ብዙ ሥፍራ፤ በብዙ ጉዳይ በጠላትነት የሚፈላለጉት ከእስራኤል ፍልስጤም ግጭት እስከ ሊባኖስ፤ ከየመን እስከ ግብፅ በተዘዋዋሪ የሚዋጉት፤ ከኑክሌር ጥያቄ እስከባሕር መስመር የሚሻኮቱት መንግሥታት በሙሉ አይሲሲን ለመዉጋት ወዳጅ ናቸዉ።

ኢራን፤ ሶሪያ፤ ኢራቅ፤ ዩናይትድ ስቴትስ፤ ሳዑዲ አረቢያና ተባባሪዎቻዉ በቀጥታ ይዋጋሉ።ፈርተዉም፤ ጥቅም ከጅለዉም ከሐብታም ሐያላኑ ጋር ያበሩት የድፍን የዓለም መንግሥታትም በሙሉ በቀጥታም፤ በተዘዋዋሪም እያሉ እንደ ጥሩ ወዳጅ እየተደጋገፉ ያን አሸባሪ ድርጅት ይወጋሉ።

ዩናይትድ ስቴትስ ለምትመራዉና ለምታስተባበረዉ ዘመቻ ኢራቅና ሶሪያ ዉስጥ ብቻ እንዲት ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በቀን ወደ ዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር ትከሰክሳለች።የሌሎቹ መንግሥታት ድምር ወጪ ከዩናይትድ ስቴትስ ቢበልጥ እንጂ አያንስም።ዓመት ሊደፍን ጥቂት በቀረዉ ዉጊያ ከስልሳ ሺሕ በላይ ሰዉ ተገድሏል።ወደ አንድ ሚሊዮን ያሕል ተሰድዷል ወይም ተፈናቅሏል።እስከ አምና ድረስ ኢራቅና ሶሪያ ዉስ ብቻ ይታወቅ የነበረዉ አሸባሪ ድርጅት ድፍን ዓለም እየቀጠቀጠዉ፤ ሊቢያ፤ ግብፅ፤ የመን፤ቱኒዚያ፤ኩዌት ምናልባትም ፈረንሳይን ማሸበር የቻለበት ምክንያት በርግጥ አነጋጋሪ ነዉ።የኩዌቱ የምክር ቤት እንደራሴ አድናን አል-ሙተዋ እንዳሉማ ሠላማዊዉ ሰዉ መሸሸጊያ ነዉ ያጣዉ።

Kuwait Beerdigung von Opfern bei einem Anschlag auf Moschee
ምስል Reuters/J. Mohammed

«ሁሉም ሙስሊሞች በአሸባሪዎች ሲገደሉ እያየን ነዉ።ኢላማ ያደረጉት አንድ ሐራጥቃን ብቻ አይደለም መላዉን አረብና ሙስሊምን አንጂ።በሰላም የምንቀመጥበት ሥፍራ የለም።ቤቶቻችንም፤ መመሳጂዶቻችንም አስተማማኝ አይደሉም,።የባሕረ ሠላጤዉ ትብብብር ሐገራትና መላዉ ሙስሊም ሐገራት አሸባሪነትን እንዲዋጉ እንጠይቃለን።»

አል-ቃኢዳ የተፈለፈለ፤የተመሠረተ፤ የተሠራጨዉ በ እና ከመንግሥት አልባዋ አፍቃኒስታን ነበር።የISIS የተመሠረተ፤ የተጠናከረ፤ የተሠራጨዉም ጠንካራ መንግሥት አልባዋ ኢራቅ ነዉ።ፈጥኖ የተዛመዉ ወደምትወድመዉ ሶሪያ እና ወደ ፈራረሰችዉ ሊቢያ ነዉ።መንግሥት አልባዋ የመን እያሰለሰች ነዉ።አፍቃኒስታን፤ ኢራቅ፤ ሊቢያ፤ የመን ለምን እና እንዴት መንግሥት አልባ ሆኑ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ