1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሸባብን የከዱ አባል ስለ ቡድኑ ሲናገሩ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 7 2007

ሀሳን አሊ ለበርካታ አመታት የአሸባብ አባል ሆነው ሰርተዋል። መፃፍ እና ማንበብ በመቻላቸውም በተለያዩ የቡድኑ ዘርፎች ተሰማርተው ነበር። ሀሳን አሊ የአሸባብ ቡድንን እንዴት እንደተቀላቀሉ እና በምን ምክንያት ቡድኑን እንደከዱ፤ ለዶይቸ ቬለ ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/1E5nS
Infografik Karte Al Shabaab in Kenia und Somalia ENG

ሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የአሸባብ አማፂ ቡድን ፤ አፍሪቃ ውስጥ ጠንካራ ከሚባሉት አክራሪ የሙስሊም ቡድናት ተርታ ይመደባል። ቡድኑ መሰረቱን ካደረገበት ሶማልያ ተነስቶ እስከ ጎረቤት ሀገር ኬንያ ጭምር በተደጋጋሚ ጥቃት ጥሏል። ሶማሊያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው የአሸባብ ቡድን አባል የነበሩት ሀሳን አሊ ዛሬ በስጋት ይኖራሉ። ቡድኑን ከከዱ አንስቶ በተደጋጋሚ ከአሸባብ ቡድን የግድያ ማስፈራሪያ የስልክ ጥሪ እንደሚደርሳቸው ይናገራሉ። የአማፂ ቡድን ተብሎ የተፈረጀውን ቡድን በወቅቱ ለመቀላቀል ምን እንዳነሳሳቸው እንደሚከተለው ይገልጻሉ።« አሸባብ ስለ ሀይማኖት በአጠቃላይ የሚናገረው እውነት ነው ብዬ አምን ነበር። በአሸባብ አቋም እተማመን ነበር። በዛ ላይ የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያን ተቆጣጥሮ ነበር።»

ሀሳን አሊ ቡድኑን የተቀላቀሉበት ዋንኛ ምክንያት ሐይማኖት ቢሆንም በርካታ ሶማላዊያን ቡድኑን የሚቀላቀሉት ለገንዘብ ብለው እንጂ የግድ ቡድኑ በሚያራምደው የሐይማኖት አቋም ተስማምተው እንዳልሆነ ሀሳን አሊ ይናገራሉ። በሀገሪቷ ያለው አለመረጋጋት እና የስራ አጥ ብዛት ለዚህ አንዱ ምክንያት ነው። ይሁንና እንደ ሀሳን አሊ ማንኛውም ሰው ሄዶ ቡድኑን በቀላሉ መቀላቀል አይችልም። ሀሳን አሊ ለምሳሌ አንድ ቡድኑ ውስጥ በነበረ ዘመዳቸው አማካኝነት ነው ቡድኑን እንዲቀላቀሉ የተጠየቁት። አሸባብን እንደተቀላቀሉም ቡድኑን ካላሰቡት ገፅታ ተመለከቱት፤ « ለሐይማኖት መስፋፋት እንደሚታገሉ ይናገራሉ። የሚያደርጉት ግን ተቃራኒውን ነው። ሰው በዘፈቀደ ይገድላሉ። የራሳቸውን ፍላጎት ብቻ ነው የሚያስቡት።»

ይሁንና ቡድኑ ልክ እንደ አንድ መንግሥት የተደራጀ ነው ይላሉ ሀሳን አሊ ። ሚኒስቴር ብለው ባይጠሩትም፤ የጤና፣ የመረጃ ፣ የአስተዳደር ቢሮ እየተባሉ የተሰየሙ ዘርፎች አሉ። ሀሳን አሊ በተወሰኑ ዘርፎች አገልግለዋል።« መጀመሪያ ላይ የተፋላሚው ዘርፍ ላይ ነበርኩ። በዚህ ዘርፍ ወደ ግንባር ለውጊያ ሄጃለሁ። ከዛ የጤና ጉዳይ አባል ሆንኩ። በመጨረሻ የሂሳብ ክፍል ውስጥ ለረዥም ጊዜ ሰራሁ። አሸባብ በአግባቡ ማንበብ እና መፃፍ የሚችሉ ሰዎች የሉትም። ስለሆነም ይህንን የቻለ ሰው በቶሎ የአስተዳደር ስራ ያገኛል።»

Neues aus Afrika
የዶይቸ ቬለ ጋዜጠኞች ሞቃዲሺ ከሚገኙ የሰላም አስከባሪዎች ጋርምስል DW/Kriesch/Scholz

ሀሳን አሊ ወታደር ሆነው የኢትዮጵያ ጦርን እንደተዋጉ ይገልፃሉ። እንደ ሀሳን አሊ የተቀናጀ ጥቃት የሚያደርሱት ሌሎች የቡድኑ አባላት ናቸው። አፍሪቃ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እንደ አንሳር ዲን፣ ቦኮ ሀራም፤ የማግሬብ የአልቃይዳ ተፋላሚዎች እና ሌሎችም ቡድናት ይገኛሉ። እንደ ሀሳን አሊ ቡድኖቹ ርዕስ በእርስ ግንኙነት አላቸው።« በመካከላቸው ግንኙነት አለ። በመጀመሪያ ነገር በጋራ የሚያምኑነት ነገር አለ። አንድ ምሳሌ ለመግለፅ ያህል አሁን የቦኮ ሀራም ቡድን መሪዎች የሆኑት የሰለጠኑት በሶማሊያ ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥ ነው። ከአሸባብ ደግሞ በተደጋጋሚ ተፋላሚዎች ለስልጠና ወደ የመን ይሄዳሉ። ከየመንም ወደዚህ ይመጣሉ። እንደዚህ አይነት ግንኙነቶች አሉ። »

ሀሳን አሊ የቡድኑ አባላት እንዴት ለስልጠና ከሀገር ሀገር እንደሚጓዙም ገልፀዋል።« የሚጓዙበት በርካታ መንገዶች አሉ። ወደ አውሮፓ የሚሄዱ ስደተኞች መስለው ከስደተኞች መሀል ይቀላቀላሉ። ከዛ እስከ ሊቢያ ያሉትን ሁሉንም ድንበሮች ያልፋሉ። ሊቢያ ሲደርሱ ወደ አውሮፓ መሄዱን ይተውና አቅጣጫቸውን ይቀይራሉ።»

ሀሳን አሊ ለሂሳብ ክፍል እንደመስራታቸው ቡድኑ በምን እንደሚተዳደር ያውቃሉ። እንደ ሀሳን አሊ አረብ ሀገራት የሚገኙ ሀብታም የቡድኑ ደጋፊዎች በባህር ሶማሊያ ውስጥ የሚሸጡ እቃዎች ይልካሉ። ጥሬ ገንዘብ ግን በቀጥታ አይልኩም። ቡድኑን የከዱት ሀሳን አሊ ዛሬ ለሶማሊያ የስለላ ድርጅት ያገለግላሉ።

ያን ፊሊፕ ሾልሽ / ልደት አበበ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ