1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሸባብ ጥቃትና የኬንያ የአፀፋ እርምጃ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 1 2007

ባለፈው ሃሙስ በኬንያው የጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በአሸባብ ጥቃት የተፈፀመውን የ148 ተማሪዎች ግድያ ለመበቀል የኬንያ መንግሥት በሶማሊያ ና በሶማሊያውያን ላይ የጀመረውን የአፀፋ እርምጃ ቀጥሏል ።

https://p.dw.com/p/1F5ZE
Kenia Attentat in Garissa
ምስል picture-alliance/AP Photo

የኬንያ አየር ኃይል ባለፈው ሰኞ በሶማሊያ የአየር ድብደባ ያካሄደ ሲሆን ዛሬ ደግሞ የኬንያ መንግሥት ለሶማሊያ ጠቃሚ የሆኑ የገንዘብ ማስተላለፊያ ድርጅቶችን አግዷል ።ስለ ሰኞው የአየር ድብደባ ና የገንዘብ አአስተላላፊ ድርጅቶች መታገዳቸው በሶማሊያውያን ላይ ስለ ሚያሳድረው ተፅእኖ በመቅዲሾ የዶቼቬለ ተባባሪ ዘጋቢን አነጋግራ ኂሩት መለሰ ተከታዩን ዘገባ አጠናቅራለች ።

ካለፈው ሐሙሱ የአሸባሪዎች ጥቃት በኋላ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ በጥቃት አድራሹ በአሸባብ ላይ መንግሥታቸው ከባድ የአፀፋ ጥቃት እንደሚፈፅም ካሳወቁ ወዲህ የኬንያ መንግሥት የተለያዩ የአፀፋ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ነው ። የኬንያ የአየር ኃይል ባለፈው ሰኞ በሶማሊያ የአየር ድብደባ አካሂዷል ። በማግስቱ ማክሰኞ በኬንያው የዳዳብ የስደተኞች መጠለያ የሚገኙ የሶማሊያ ስደተኞችን ወደ ሃገራቸው በአፋጣኝ እንዲመለሱ ለማድረግ መታቀዱን አስታውቋል ። ዛሬ ደግሞ የሶማሊያ የሃዋላ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶችን አግዷል ። ከዚህ ሌላ ኬንያ በሶማሊያ ተጨማሪ የአየር ጥቃቶች አካሂዳለች ሲሉ አንዳንድ የዜና ምንጮች ቢናገሩም በሶማሊያ የዶቼቬለ ዘጋቢ መሀመድ ዑመር ሁሴን ግን ከሰኞ ወዲህ የተካሄደ የአየር ድብደባ የለም ይላል ።

Kenia Garissa Universität Anschlag Trauer
ምስል picture-alliance/dpa/D.Irungu

« የአየር ጥቃቱ የተካሄደው ለአንድ ቀን ብቻ ነው። ይኽውም ከ3 ቀናት በፊት ነበር ይህም በኬንያ መንግሥት የተወሰደ የበቀል እርምጃ ነው ። ፕሬዝዳንት ኡኹሩ ኬንያታ ባለፈው ሐሙስ ኬንያ ውስጥ ለደረሰው የሽብር ጥቃት ከባድ አፀፋ ጥቃት እንደሚፈፀም አስታውቀው ነበር ። ፕሬዝዳንቱ ያሉት በተግባር ተፈፅሟል ። »

በሰኞ የአየር ጥቃት የኬንያ መንግሥት የደፈጣ ተዋጊውን የአሸባብን ጠንካራ ይዞታ ማጥቃቱን ነው የገለፀው ።ሆኖም መሀመድ እንደተናገረው በጥቃቱ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ሰላማዊ ሰዎችም መገደላቸውን ከአካባቢው ምንጮች ሰምቷል ።

«የአየር ድብደባው የተካሄደው በሶማሊያና በኬንያ ድንበር ላይ ጌዶ በሚባል አካባቢ ነው ። የኬንያ መንግሥት በዚሁ ስፍራ የአሸባብን ተዋጊዎች ጠንካራ ይዞታ መደብደቡን አሰታውቋል ። ሆኖም ከአካባቢው የሚወጡ ዘገባዎች ግን ሰላማዊ ሰዎችም ላይ ጉዳት መድረሱን ያሳያሉ ። በርግጥ በጥቃቱ የተጎዱት ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ ግን ማወቅ አልቻልንም ።»

148 ተማሪዎች በተገደሉበት የጋሪሳ ዩኒቨርስቲ ፣ ጥቃቱ በተፈፀመበት እለት የኬንያ መንግሥት ልዩ ኃይል ፈጥኖ መድረስ አለመቻሉ መንግሥትን ክፉኛ እያስተቸው ነው ። ባለፈው ማክሰኞ ናይሮቢ ውስጭ ሟቾቹን ለማሰብ ሰልፍ የወጡ ተማሪዎች የመንግሥት ወታደሮችን ያኔ የት ነበራችሁ ሲሉ ጠይቀው ነበር ። ያለፈው ሳምንቱ የኬንያው የአሸባብ ጥቃት ከዚህ ቀደም ስለ ቡድኑ መዳከም ሲሰጡ የነበሩ አስተያየቶችን ጥያቄ ውስጥ አስገብቷል ። ተባባሪ ዘጋቢ መሀመድ በበኩሉ የቡድኑን መዳከም የሚያሳዩ ምልክቶች እንዳሉ ሁሉ ያለ መዳከሙም መገለጫዎች አሉ ይላል ።

Kenia Garissa Universität Anschlag Soldaten Militär
ምስል Getty Images/AFP/de Souza

«አዎ አሸባብ ተዳክሟል ። በሌላ በኩል ደግሞ አልተዳከመም ። ይህን የምልበት ምክንያት አሸባብ ከዋና ዋናዎቹ የሶማሊያ ከተሞች እንዲወጣ ተደርጓል ። ያም ሆኖ አሁንም ራቅ ብለው በሚገኙት የሶማሊያ አካባቢዎች ግን ግን በትጋት ይንቀሳቀሳል ። አሁንም ቢሆን በሶማሊያም ሆነ በጎረቤት አገሮች ከባድ ጉዳቶች ማድረስ ይችላል ። »

የሐሙስ ጥቃት ካስከተለው መዘዝ አንዱ ኬንያ የሚገኙ የሐዋላ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች መታገድ ነው ። የኬንያ መንግሥት ዛሬ እንዳስታወቀው ለሶማሊያ ጠቃሚ የሚባሉ የገንዘብ አስተላላፊ ተቋማትን አግዷል ። ይህም ከውጭ በሚላክ ገንዘብ ላይ ህይወታቸው ለተመሰረተው በርካታ ሶማሊያውያን ከባድ ጉዳት መሆኑ ግልጽ ነው ።መሀመድ እንደሚለው ግን እርምጃው የሚጎዳው ሶማሊያውያንን ብቻ አይደለም ።

«የነዚህ የሐዋላ ድርጅቶች ተገልጋዮች ሶማሌዎች ብቻ አይደሉም ። ኢትዮጵያውያንና ሱዳኖችና የረብ ሃገራት ዜጎችም ናቸው ። ሃዋላው ለበርካታ አፍሪቃውያን በጣም ጠቃሚ ነው ። በነርሱም ላይ ተፅእኖ እንደሚያደርግ እርግጠኛ ነኝ በፍጥነትና በቀላሉ ገንዘብ የሚልኩበትና የሚቀበሉበት መንገድ ነበር ። በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሃዋላ አገልግሎት ከሚሰጡ ሌሎች ተቋማት ገንዘብ ማግኘቱ ውስብስብ ነው የሚሆነው እናም ያለ አንዳች መጠራጠር ይጎዳቸዋል ።»

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ