1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአቶ በቀለ ዋስትና ታገደ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 23 2010

ከአቶ በቀለ ጠበቆች አንዱ አቶ አብዱልጃበር ሁሴን ገመዳ ለዶቼቬለ እንዳሉት የዋስትናውን ውሳኔ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ አጣሪ ችሎት ማገዱን ዛሬ ደንበኛቸው በታሰሩበት ማረሚያ ቤት በተገኙበት አጋጣሚ ተነግሯቸዋል። ልጃቸዉ ቦንቱ በቀለ ገርባ በዛሬዉ ዕለት አባቷ ጉዳያቸዉ ኅዳር 14 ቀን በፍርድ ቤት እንደሚታይ እንደገለጹላት ተናግራለች።

https://p.dw.com/p/2ms39
Äthiopien Politiker Bekele Gerba
ምስል Addis Standard Magazine

ከአቶ በቀለ ገርባ ጠበቃ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ለኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር ለአቶ በቀለ ገርባ የፈቀደው ዋስትና መታገዱ በቃል እንደተነገራቸው ጠበቆቻቸው አስታወቁ። ከአቶ በቀለ ጠበቆች አንዱ አቶ አብዱልጃበር ሁሴን ገመዳ ዛሬ ለዶቼቬለ እንዳሉት የዋስትናውን ውሳኔ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ አጣሪ ችሎት ማገዱን ዛሬ ደንበኛቸው በታሰሩበት ማረሚያ ቤት በተገኙበት አጋጣሚ ተነግሯቸዋል። ጠበቃው ደንበኛቸው በዋስትና እንዳይለቀቁ ትናንት በምክንያትነት የቀረበው ተሳስቷል የተባለ የመዝገብ ቁጥር እንዲስተካከል ለመጠየቅ ነበር ዛሬ ማረሚያ ቤት የሄዱት።

አቶ በቀለ ገርባ በዋስትና የመፈታታቸዉ ጉዳይ መታገዱን ቤተሰቦቻቸዉ የሰሙት ደግሞ ከራሳቸዉ ከአቶ በቀለ ነዉ። ልጃቸዉ ቦንቱ በቀለ ገርባ በዛሬዉ ዕለት ወደ ታሠሩበት ስፍራ ሄዳ እንዳገኘቻቸዉ ጉዳያቸዉም ኅዳር 14 ቀን 2010 ዓም በፍርድ ቤት እንደሚታይ እንደገለጹላት ለዶቼ ቬለ አስረድታለች። «ጠብቂ ይመጣል ተባልኩኝ። ቆሜ ብዙ ሰአት ጠበክኹት።  በመጨረሻም ሲመጣ  ቢሮ ተጠርቼ እያናገሩኝ ነበር እና 'ሰበር ሠሚ ችሎት ለኅዳር ዐሥራ አራት ቀጠሮ ያዘ፤ እንደገና ክርክር ይደረጋል እናም አቃቤ ሕጎች ለሠበር ሰሚ ችሎት አቤቱታ አቀረቡ ስለዚህ አትወጣም ተባልኩኝ' አለኝ።»

Äthiopien Journalisten Martin Schibbye und Johan Persson
ምስል AP

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቶ በቀለ በ30ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ የወሰነው ከትናንት በስተያ ነበር። አቶ በቀለ ገርባ ዛሬ ከእስር ቤት ይወጣሉ በሚል ጠበቆቻቸው ወደተለያዩ ቦታዎች ጉዳዩን ለማስፈጸም ሄደው ነበር። አቶ አምኃ መኮንን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቶ አብዱልጃባር ሁሴን ገመዳ ደግሞ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት። አቶ አብዱልጃባር ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በቃል የሰሙትን ለዶቼ ቬለ በዝርዝር ተናግረዋል። «መጀመሪያ ይሄ መዝገብ ዐሥራ ዘጠነኛ ወንጀል ችሎት የነበረ መዝገብ ነው። ጉዳዩ በጣም እየበዛ ሲሄድ ነው  ሁለት ችሎት የሆነው፤ እና ኋላ ላይ ወደ አራተኛ ችሎት የሄደው። አሁን ማረሚያ ቤቱ በዐሥራ ዘጠነኛ ወንጀል ችሎት ብሎ ነበር ደብዳቤውን የጻፈው እና ያንን ወደ አራተኛ ለማስቀየር ደብዳቤውን ይዘን ስንሄድ አያይ ጉዳዩን እኮ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሰበር ሰሚ ችሎት አግዶታል። ይሄ ደብዳቤ ቢቀየርም ባይቀየርም ምንም ጥቅም የለው የሚል መልስ ሰጡን  የእስረኞች ጉዳይ አስተዳደር ክፍል ማለት ነው።»

ጠበቃ አብዱልጃባር ከቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ታግዷል መባሉን በቃል ከመስማታቸው ውጪ «የእግዱን ወረቀት አላየንም» ብለዋል። ጉዳዩንም አቶ በቀለ ገርባ ጋር እንደደረሰ ተመካክረን «እንዴት እንደምንቀጥል እንወያያለን» ብለዋል።

ሙሉ ዘገባዎቹ ከታች ከሚገኘው የድምጽ ማዕቀፍ ማድመጥ ይቻላል። 

ኂሩት መለሰ

ሸዋዩ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ