1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንበጣ መንጋ፤ ርሃብና ድርቅ በምዕራብ አፍሪካ

ሐሙስ፣ ሐምሌ 21 1997

የአዉሮፓ ህብረት በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ኒጀር ለተከሰተዉ የርሃብ አደጋ እርዳታ ለመለገስ በአገሪቱ የተመቻቸ የግብረ ሰናይ ወኪል አለመኖር እንቅፋት እንደሆነበት አስታወቀ። በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ በአንበጣ መንጋና በድርቅ በተመታችዉ ኒጀር የሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ቁጥር ዉሱንነት ለመርዳት የተዘጋጁ ወገኖች እርዳታዉን በትክክል ለህዝቡ ያቀርባል ብለዉ የሚያምኑት አካል በማጣጣቸዉ መጓተቱ ነዉ የሚነገረዉ።

https://p.dw.com/p/E0jg

በምዕራብ አፍሪካ ከኒጀር ሌላ በአጎራባች የሚገኙ አገሮችም የርሃብና የድርቁ እንዲሁም የአንበጣ መንጋዉ ወረርሽኝ ችግር ተጋሪዎች ናቸዉ። ችግሩ አገራችንን ጨምሮ ሌሎች የአህጉሪቱን አገራትም እንደሚነካ ስጋት አለ።
የአዉሮፓ ህብረት ዋና ፀሃፊ እንደገለፁት በኒጀር ከተከሰተዉ የምግብ እጥረት፣የድርቅና የአንበጣ ወረርሽኝ በተጨማሪ ለጋሾችን ያዳገታቸዉ በአገሪቱ የመንገድ አለመኖርና እርዳታዉን ተረክቦ ማከፋፈል የሚችል አጋር የእርዳታ ድርጅት በአገሪቱ አለመኖሩ ነዉ።
የአዉሮፓ ህብረት ኮሚሽን ቃል አቀባይ አማዱ አልታፋጃ ታርዲኦ እንደሚሉት ከሆነ በአገሪቱ ከሚታዩ ዋነኛ ችግሮች አንዱ በኒጀር መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንደልብ አለመገኘት ነዉ።
አያይዘዉም ኒጀር በዓለም ካሉ አገሮች ሁለተኛዋ ድሃ አገር መሆኗን በመግለፅ አገሪቱ ካለባት ዘርፈ ብዙ የአስተዳደር ችግር በተጨማሪ አስቸጋሪ የአየር ጠባይ መኖሩም እንደጎዳት አስረድተዋል።
ይህ በሁሉም አቅጣጫ የደከመዉ የኒጀር ይዞታ ነዉ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሰራተኞች እንዲኖሩባት ያላበረታታዉ ይላሉ ታርዲኦ።
በዚያም ላይ በሚሊዮን የሚቆጠረዉን በርሃብ እየሞተ የሚገኝ የኒጀር ህዝብ ለመመገብ ገንዘብ ቢኖራቸዉም ያን ገንዘብ ተረክቦ በትክክል ለሚፈልጉት ወገኖች ማድረስ የሚችል አካል መኖሩን እርጠኞች አይደሉም።
በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በረጅም ጊዜ የስራ እቅድ የሚንቀሳቀሱ በመሆናቸዉ እንዲህ ያለ አደጋ በሚከሰት ጊዜ የገንዘብ መጠየቂያ መርሃ ግብር ይዞ ያለዉን በጀት በአግባቡ ስራ ላይ የሚያዉል ማግኘት ተቸግረናል ባይ ናቸዉ ቃል አቀባዩ።
12 ሚሊዮን ህዝብ ያላት የባህር በር አልባዋ ኒጀር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ 3.6ሚሊዮን ህዝብን ባሰጋዉ በምዕራብ አፍሪካ በተከሰተዉ የከፋ ረሃብ እየተጠቁ ከሚገኙ አገራት ግንባር ቀደሟ ሆናለች።
ኒጀር በሰሜን ከአልጀሪያና ሊቢያ፤ በምስራቅ ከቻድ፤ በደቡብ ከናይጀሪያና ቤኒን እንዲሁም ከቡርኪናፋሶና ማሊ ጋር በምዕራብ ትዋሰናለች።
የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ጉዳይ ሃላፊ ጆን ኤግላድ ባለፈዉ ሳምንት እንደገለጹት የዓለም ህብረተሰብ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታን ችላ በማለቱ የአፍሪካ አገራት ህዝቦች በተለይም ህፃናት እየሞቱ ነዉ በማለት አሳስበዋል።
እንደ ኢግላድ ገለፃ በኒጀር 2.5ሚሊዮን ህዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚፈልግ ሲሆን 800,000ህፃናት ደግሞ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ህይወታቸዉ አደጋ ላይ ነዉ።
የመንግስታቱ ድርጅት በመጀመሪያ ባለፈዉ ዓመት ህዳር ወር ላይ ለኒጀር በቅድሚያ እርዳታ ለማሰባሰብ ጠይቆ ምላሽ አላገኘም ነበር።
በድጋሚ በመጋቢት ወር 13.2 ሚሊዮን ዩሮ ማለትም 16ሚሊዮን ዶላር ጠይቆ 0.83 ማለትም 1ሚሊዮን ዶላር ብቻ ማግኘቱን አስታዉቋል።
በቅርቡ እንደገና በግንቦት ወር 25ሚሊዮን ዩሮ ወይም 30ሚሊዮን ዶላር በጠየቀበት ወቅት ደግሞ ሲመነዘር 10ሚሊዮን ዶላር የሚሆን 8.3ሚሊዮን ዩሮ ቢያገኝም ኢግላድ እንደሚሉት በጣም ትንሽ ነዉ።
ምክንያቱንም ሲያብራሩ በኒጀር ይህ የድርቅ ችግር ይከሰታል ተብሎ የተገመተዉ ከስድስት ወር በፊት ሲሆን ርሃቡ እያደረሰ ከሚገኘዉ አደጋ አንጻር ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ያሰባሰቡት የእርዳታ ገንዘብ።
በሌላ በኩል ታርዲኦ ምንም እንኳን አስቸኳይ እርዳታ ለተራቡት ወገኖች ማስፈለጉ ባያጠያይቅም ለምግብ ችግር የረጅም ጊዜ መፍትሄ መፈለግ ይኖርበታል ይላሉ።
በተደጋጊ እንደምንለዉ አሉ ታሪዲኦ እርዳታ በቀጥታ ማዳረስ አስፈላጊ ነዉ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለችግር ጊዜ የሚዉል በቂ የእህል ክምችት መኖር ወሳኝ ነዉ።
ከዚህ በመነሳትም በየአካባቢዉ ምግብ የሚከማችበትን ሁኔታ እንዳመቻቹ በመጥቀስ ህዝቡ ለወደፊቱ በቀላሉ እንዲደርሰዉ የማድረግ ተግባር እያከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
በአሁኑ ጊዜ የአንበጣ መንጋና ድርቅ በምዕራብ አፍሪካ ከኒጀር በተጨማሪ ሞሪሺየስ፤ ማሊና ቡርኪናፋሶንም እያጠቃ መሆኑ ታዉቋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስቀድሞ እንዳስጠነቀቀዉም በኒጀር ጎረቤት በማሊ 1.1ሚሊዮን ህዝብ በያዝነዉ ዓመት የእርዳታ ምግብ ፈላጊ ነዉ።
በሰሜናዊ ቡርኪናፋሶም ወደ500,000 የሚደርሱ ሰዎች የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸዉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በርካቶች ምግብ ፍለጋ ከቤታቸዉ ተሰደዉ በመዉጣት ላይ ናቸዉ።
በዚህ ረገድ በአፍሪካ ሌላ ተጨማሪ ቀዉስ ኢትዮጵያ፤ ኬንያና ኤርትራን ጨምሮ በሌሎች አገራትም ላይ አንዣቧል።
የአዉሮፓዉ ህብረት ማክሰኞ ዕለት ኢትዮጵያና ኤርትራ የርሃብ አደጋዉን የሚከላከሉበት 8.5ሚሊዮን ዩሮ ወይም 10.3 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ መስጠቱን አይፒኤስ ዘግቧል።
እርዳታዉም በቀጥታ ለመድሃኒትና ለዉሃ አቅርቦት፤ እንዲሁም ለምግብና ለከብት እርባታ ድጋፍ እንደሚዉል ይጠበቃል።