1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአንድ ዓመቱ የለዉጥ ጉዞ በፖለቲካ ፓርቲዎች ዕይታ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 24 2011

በኢትዮጵያ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የዘለቀዉን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ዶክተር ዐቢይ አህመድ የጠቅላይ ሚንስትርነቱን ሥልጣን ከጨበጡ ድፍን አንድ ዓመት ተቆጠረ። በዚህ ጊዜ ዉስጥ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት መንግሥት የወሰዳቸዉ አወንታዊ ርምጃዎች ቢኖሩም ይህ ርምጃ ወደ ታች ባለመዉረዱ የተፈለገዉን ያህል በነፃነት መንቀሳቀስ አልቻልንም

https://p.dw.com/p/3G7Ec
Dr Abiy Ahmed
ምስል DW/Y.Geberegziabeher

«የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ረገድ አንፃራዊ ለዉጥ ተገኝቷል»


ሲሉ አንዳንድ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለፀዋል። ገዢው ፓርቲ ኢህአዴግ በበኩሉ ችግሮቹን  ለመፍታት እየሠራሁ ነው ብሏል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ  የዛሬ አንድ ዓመት  መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ/ም ነበር ቃለመሃላ ፈፅመዉ ወደ ስልጣን የመጡት። ጠቅላይ ሚንስትሩ የፍትህ የእኩል ተጠቃሚነት፣ የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር እጦት የወለደዉ ህዝባዊ ተቃዉሞ ባየለበት ፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አመራርና አባላት እንዲሁም በፖለቲካ ተሳትፏቸዉ በርካታ ዜጎች ለእስር በተዳረጉበት ወቅት ወደ ስልጣን የመጡ በመሆናቸዉ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋትና የተቃዋሚ ፓርቲዎችን እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ተፎካካሪ ማየት የሚለዉ ሀሳብ በመጀመሪያ ቀን ንግግራቸዉ ትኩረት ሰጥተዉ ካነሷቸዉ ጉዳዮች መካከል  አንዱ ነበር።«ከኢህአዴግ ዉጭ ያሉ ፓርቲዎች የምናይበት መነፅር እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን እንደተፎካካሪ እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ ወንድም አማራጭ ሀሳብ አለኝ ብሎ እንደመጣ ሀገሩን እንደሚወድ የዜጋ ስብስብ ነዉ።»

Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed
ምስል Office Of The Prime Minister

«ከኢህአዴግ ዉጭ ያሉ ፓርቲዎች የምናይበት መነፅር እንደ ተቃዋሚ ሳይሆን እንደተፎካካሪ 
ይህንን ተከትሎም  በውጭ ሀገር  በትጥቅና በሰላማዊ መንገድ መንግሥትን ይቃወሙ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ወደ ሀገር ቤት ገብተዋል። በሀገር ዉስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችም በነፃነት ሃሳባቸዉን ማራመድ ጀምረዋል።
DW ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ እንደሚሉት ከኢህአዴግ የ27 ዓመት የአገዛዝ ባህሪ በመነሳት ፓርቲው ራሱ የፈጠረዉን ችግር ራሱ ብቻዉን ሊቀርፈዉ አይችልም በሚል በድርጅቱ የተጀመረዉን ለዉጥ በጥርጣሬ ይመለከቱት ነበር። ለዉጡ በቀና መንፈስ ካልተካሄደ ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚል ስጋትም ነበራቸዉ። ያም ሆኖ ግን በዚህ አንድ ዓመት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ከወሰዷቸዉ አወንታዊ ርምጃዎች በመነሳት አንፃራዊ ለዉጥ ተገኝቷል ብለዉ ያምናሉ።

«ፖለቲከኞች ወደ ሀገር ገብተዉ በፈለጉት አደረጃጀት ተደራጅተዉ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ እድል ተሰጥቷል።በሚዲያ የመጠቀም መብታቸዉ የተወሰነ ክፍት ተደርጓልና ጠላት የሚለዉንም ወደ ተፎካካሪ ፓርቲ ተቀይሯል።በምርጫ ቦርድ አወቃቀር በጋራ እየተነጋገሩ  ፓርቲዎች የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ እንዲፈራረሙ ተደርጓልና አወንታዊ ነዉ።»

Äthiopien Oromo Federalist Congress
ምስል DW/Y.G. Egziabhare

የአረና ትግራይ ለሉዓላዊነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምዶም ገብረ ሥላሴ በበኩላቸዉ የዶክተር ዐቢይ መንግሥት በአንድ ዓመት የለዉጥ ጉዞ የፖለቲካ ምህዳሩን ከማስፋት አንፃር አወንታዊ ለዉጦች መኖራቸዉን ያስረዳሉ።

ያም ሆኖ ግን በፌደራል ደረጃ የሚታየዉ ለዉጥ እንዲሁም መንግሥት የሚያወጣቸዉ መመሪያዎች በታችኛዉ የአመራር እርከን በተገቢዉ ሁኔታ እየተተገበሩ ባለመሆናቸዉና ወደ ታች ባለመዉረዳቸዉ የፓርቲዎቻቸዉን ተሳትፎ የሚገድቡ ችግሮች እያጋጠሙን ነዉ ሲሉ ፓርቲዎቹ ይተቻሉ። በዚህ የተነሳ በአንዳንድ አካባቢዎች አባላት ይታሰራሉ ቢሮዎችም ይሰበራሉ ይላሉ አቶ ሙላቱ ገመቹ።እናም በፌደራል ደረጃ የሚታየዉ የፖለቲካ ለዉጥ በክልሎች አለመታየቱ እንደ አቶ አንዶም ገብረስላሴ ሊስተካከል የሚገባዉ ድክመት ነዉ ።
«አረና የፖለቲካ እስረኞቹ አልተፈቱም በሌላዉ የኢትዮጵያ ክፍል ተፈተዋል።የተሻለ ምህዳር ስላለ።በትግራይ ግን የአረናና የደምሂት እስረኞች አልተፈቱም« በማለት የለዉጡ ደካማ ጎን ያሉትን ጠቅሰዋል። 

የኢህአዴግ ምክርቤት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱአለም በበኩላቸዉ በዚህ የአንድ ዓመት የለዉጥ ጉዞ ድርጅታቸ የኢህአዴግ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የነበረዉ ግንኙነት ዲሞክራሲያዊ  ነበር ይላሉ።በዚህም ኢህአዴግ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ መስራት ጀምሯል።

Äthiopien  - Ministerpräsident Äthiopiens in einer Gesprächsrunde
ምስል Daniel Getachew

«በሀገር ቤትም የነበሩ በዉጭም የነበሩ ሁሉም ጥሩ እንቅስቃሴ ነዉ ያለዉ።ይህ ብቻ ሳይሆን ከገዥዉ ፓርቲ ኢህአዴግ ጋርም  የጋራ መድረኮች አሉን። እንወያያለን ።እንነጋገራለን።» ብለዋል።

በፓርቲዎቹ የሚነሱ ቅሬታዎችም በጋራ በዉይይትና በመነጋገር እንደሚፈቱ ሀላፊዉ አመልክተዋል። 

በፓርቲዎች መካከል የመነጋገር ባህል ማሳደግ ፣ በአሁኑ ጊዜ የሚታየዉ በርካታ የፓርቲዎች ቁጥር ወደዉህደትና ቅንጅት በመምጣት ጠንካራ ፓርቲ በመመስረት በዲሞክሲ ስርዓት ግንባታዉ የበኩላቸዉን ሚና መጫወት እንዳለባቸዉ ሦስቱም ፓርቲዎች አሳስበዋል።

 

ፀሐይ ጫኔ

ሽዋዬ ለገሠ