1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአኗኗር ዘይቤ እና ጥንቃቄ የሚያሻው ጤናችን

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 1 2011

የሰዎች የአኗኗር ዘይቤ በጤናቸው ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የጤና እና የስነምግብ ምሁራን በየጊዜ ይናገራሉ። የአመጋገብ ልማድ እና እንቅስቃሴን የሚያካትተው የአኗኗር ዘይቤ መለወጥ ሰዎችን ለተለያዩ የጤና እክሎች መዳረጉን የሚያሳስቡት የዘርፉ ተመራማሪዎች የምንፈልገውን ብቻ ሳይሆን ለሰውነታችን የሚያስፈልጉትን መመገብ እንደሚያስፈልግ ይመክራሉ።

https://p.dw.com/p/3GWVy
Obst und Gemüse
ምስል Colourbox

«ጥንቃቄን የተከተለ አመጋገብ እና አካላዊ እንቅስቃሴ ይመከራል»

የትኛውም ያህል ዘመን መኖር ብንችል የየግል ጤናችንን ለመጠበቅ ቀዳሚው የሚሆነው የአኗኗር ስልታችን እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ። በተለይም ዛሬ ዛሬ በብዛት የሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ የሚታወቁት እንደካንሰር እና መሰል በሽታዎችን ለመከላከል የአመጋገብ ጥንቃቄን በአንድ በኩል በሌላው ወገን ደግሞ የሰውነት እንቅስቃሴን ማዘውተር ይመከራሉ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት በቅድሚ የሚበላው በተገኘ የሚል እና እንዲህ ያለውን የባለሙያ ምክርም የቅንጦት አድርጎ የሚመለከት አይጠፋም። እውነታው ግን ከቀድሞው ይልቅ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም ዛሬ ዛሬ የካንሰር ታማሚው መበርከት፤ የደም ግፊት እና የስኳር ብሎም የልብ ህመምተኛው ቁጥር መጨመር ዋናው መንስኤ ተብሎ ወደሚነገረው የአኗኗር ዘይቤ ፊታችንን እንድናዞር ግድ ይለናል። በግላቸው ከመጠን በላይ የሆነ የሰውነት ክብደትን ለመቀነስ ለሚሹ አስፈላጊውን ሙያዊ ምክር በመስጠት ተግባር የተሰማሩት የስነምግብ ባለሙያው አቶ አብነት ተክሌ ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት በትምህርት ቤት ደረጃ ይሰጡ የነበሩ እንደ የቤት ውስጥ ባልትና ሳይንስ ያሉ ትምህርቶች አለመኖር ኅብረተሰቡ በዚህ ወሳኝ ችግር ላይ ያለውን ግንዛቤ እንደገደበው ያምናሉ። የመረጃዎች በስፋት ኅብረተሰቡ ውስጥ አለመዳረስ ደግሞ ሰዎች ለአኗኗር ዘይቤያቸው ትኩረት እንዳይሰጡ ማድረጉንም ያመለክታሉ። በሀገራችን ከአቅም ችግር ጋር በተያያዘ የምግብ እጥረት ላይ ትኩረት መደረጉን ቢገልፁም ከመጠኑ ያለፈው አመጋገብ እጅግም ቦታ እንዳልተሰጠውም ያስረዳሉ ባለሙያው።

Enjera Äthiopien
ምስል DW/E. Bekele Tekele

የማጣት እና የመትረፍረፉ ጉዳይ እንዳለ ሆኖ ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ የሚባለው ሦስት መሠረታዊ ነገሮችም ማካተቱን የስነምግብ ባለሙያው  እንዲህ ይዘረዝራሉ፤

«ምንድነው ጤናማ የአኗኗር ዘይቤ ብለን ስንመለከት ሦስት መሠረታዊ ሃሳቦች አሉ። አንደኛው እና ዋናው አመጋገብ ነው። ሁለተኛው እንቅስቃሴ ነው፤ ሦስተኛው ደግሞ የስነአእምሯዊ ጉዳዮች ወይም ደግሞ የአስተሳሰብ ጤንነት የምንለው ነው።»

ለመሆኑ ጤናማ አመጋገብ እንዴት ያለ ነው? አሁንም አቶ አብነት፤ «ጤናማ አመጋገብ በኢትዮጵያም ከኢትዮጵያ ውጪም ባሉት የተሠራ ብዙ ጥናት የሚያሳየው ከተለያዩ ምግቦች አውጣጥቶ እነሱን ቀላቅሎ መመገብ ከሚለው ጋር ይሄዳል።»

የምንፈልገውን ሳይሆን ሰውነታችን የሚያስፈልገውን መመገብ እንደሚያስፈልግ የስነምግብ ባለሙያው ምሳሌ በመጥቀስም ያስረዳሉ፤ «ለምሳሌ አንዳንድ ሰው ኤኮኖሚው እያደገ ሲመጣ ፕሮቲን እና ቅባትን ብቻ አብዝቶ የመጠቀም ነገር ትመለከቻለሽ። ያ እንግዲህ ብዙ ጊዜ ከሥጋ ጋር ፣ ጮማ የመሳሰሉ፣ ስኳርነት የበዛባቸው ነገሮች፤ ይሄ በቀን ውስጥ የሚያስፈልገንን የምግብ ምጣኔ ያዛባል።»

የአመጋገብ አለመስተካከል ለተለያዩ የጤና ችግሮች እንደሚያጋልጥ የውስጥ ደዌ ከፍተኛ ሀኪም የሆኑት ዶክተር ቶሌራ ወልደየስም ያረጋግጣሉ። በሌላ በኩልም በቂ ምግብ ባለማግኘትና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትም የጤና ጠንቅ እንደሆነው የውስጥ ደዌ ከፍተኛ ሃኪሙ አንስተዋል።

ስለአኗኗር ዘይቤ ሲነሳ በጤና ላይ ችግር የሚከተለው በዋናነት ምግብን የሚመለከተው ቢሆንም በቂ የአካል እንቅስቃሴ እና በቂ እንቅልፍም ትልቅ ሚና እንዳላቸው መዘንጋት የለበትም። ባለሙያዎቹ ከዚህም ሌላ ስለአልክሆል መጠጥም የሚሉት አለ። ለዛሬ ጊዜ ገደብ ሳምንት የእናንተን አስተያየት አክለን እንመለስበታለን። 

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ