የአካባቢ ተፈጥሮ በካዩ ፕላስቲክ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:06
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
12:06 ደቂቃ
05.09.2017

ማንኛዉም የፕላስቲክ ዕቃ አወጋገዱ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል

ካለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2016 አጋማሽ አንስቶ በርካታ ሃገራት ፕላስቲክ የዕቃ መያዣን መጠቀም በየበኩላቸዉ የተለያዩ ርምጃዎችን መዉሰድ ጀምረዋል። አንዳንዶች ሙሉ በሙሉ ሌሎች ደግሞ አይነቱን እየመረጡ የላስቲክና ፌስታል አጠቃቀም ላይ እገዳን ጥለዋል። በቅርቡም ጎረቤት ኬንያ ተመሳሳይ ርምጃ በመዉሰድ የብዙዎችን ትኩረት ስባለች።  

ኢትዮጵያ ዉስጥ የፕላስቲክ ዕቃ መያዣዎች በሀገራችን ሥራ ላይ ከመዋላቸዉ በፊት የተክሎች ዉጤቶች በሆኑት በዘንቢል እና ቅርጫት መጠቀሙ የተለመደ እንደነበር ይታወስ ይሆናል። ዛሬ ዛሬ እዚህ አዉሮጳ ዉስጥ እነቅርጫት እና ዘንቢል ዋጋቸዉ በሀገራችን መጠነኛ የጉዞ ሻንጣ የሚያስገዛ ሆኗል። ያንን መጠቀሙም የዘመናዊነት እና የንቃት መግለጫ ነዉ። ሱቆችም ከዓመታት በፊት ለየተገዛዉ ዕቃ የፕላስቲክ መያዣ እንዳልሰጡ ሁሉ ከአንድ ዓመት ወዲህ መያዣ ለሚጠይቃቸዉ ቀላል የማይባል ሳንቲም መጠየቅ መጀመራቸዉ፤ ተገልጋዩ ኅብረተሰብ ሳንቲም ለመቆጠብ ሲል መያዣዉን አስቀድሞ እንዲያስብበት እያደረጉት ነዉ።

ኬንያ ካለፈዉ ሰኞ ዕለት ጀምራ ነዉ በይፋ ፕላስቲክ የዕቃ መያዣን መጠቀም፤ ማምረትም ሆነ ወደሀገር ዉስጥ ማስገባት በገንዘብ አለያም በእስራት እንደሚያስቀጣ ያሳወቀችዉ። ይህን እገዳ  የተላለፈም እስከ 38 ሺህ ዶላር መቀጮ ወይም የአራት ዓመት እስራት ይጠብቀዋል። ያመረተ ወይም በማዕከላዊ ኬንያ የኪያምቡ ግዛት የእንስሳት ሀኪም ባለስልጣን ሙቡቲ ኪኒያንጁ ላስቲኮቹ ከአካባቢ አልፈዉ በእንስሳት ጤና ላይ ያስከተሉትን ችግር ዘርዝረዋል። 

«ዘግይተን እንዳስተዋልነዉ ከእንስሳቱ ዉስጥ እያደር የበዛ ፕላስቲክ ማዉጣታችንን ተመልክተናል። ከእንስሳቱ ሆድ ማለት ነዉ። እናም ይህ እያደገ የሄደ ስጋት መሆኑን መግለጽ ይኖርብኛል። ይህ እያደር እየጨመረ የመጣ ችግር ነዉ፤ ከዛሬ 10 ዓመታት በፊት እንዲህ ያለ ነገር አጋጥሞን አያዉቅም ነበር፤ አሁን ግን በየዕለቱ የሚታይ ነዉ ማለት ይቻላል።»

7. Bildergalerie Kenia Mülldeponie bei Nairobi

በዶቼ ቬለ የፌስ ቡክ ገጽ ላይ አስተያየታቸዉን ያስነበቡን ሳዴራ እየ ተሞክሮም ይህንን የሚያጠናክር ነዉ። እንስሳት እንዳገኙ ሊመገቡት እንደሚችሉ፤ ባህር ዉስጥም ቢሆን የሚጣለዉን የተለያየ ፕላስቲክ ነገር ዓሣዎችና ሌሎች የባህር ዉስጥ እንስሳት እየበሉ ራሳቸዉ መሞታቸዉ ሳያንስ እነሱን የሚመገቡ በተዘዋዋሪ ለፕላስቲኩ ብክለት እንዲጋለጡ ማድረጉም በየጊዜዉ የአካባቢ ጥበቃ ተቆርቋሪዎች የሚያቀርቡት አቤቱታ ነዉ። የፕላስቲክ ዕቃ መያዣዎች የኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢን ጎዳናዎች እንዳበላሹ፤ ቆሻሻ በሚጣልባቸዉ ስፍራዎችም ተከምረዉ እንደሚታዩ የአሶሺየትድ ፕረስ ዘገባ ያመለክታል። ኬንያ ፕላስቲክ ዕቃ መያዣዎቹን ስታግድ ከተማዎችን መበኩሉን አልፎ ተርፎም እንስሳትን መጉዳቱን ያስተዋሉ ቢደግፉትም በማምረትም ሆነ በመሸጥ የሚተዳደሩ አካላት ግን በቀላሉ አልተቀበሉትም። እኝህ ወይዘሮ ፉስታል ሻጭ ናቸዉ፤

«የእኔ ደንበኞች ሥጋ ቤትም ሆነ ሌላ መሸጫ ያላቸዉ ሲሆኑ የከብትም ሆነ የዶሮ ሥጋ የሚሸጡት በእነዚህ ላስቲኮች ጠቅልለዉ ነዉ። እንዲህ በመሆኑም ማቀዝቀዣ ዉስጥ ለማስቀመጥ ይጠቅማቸዋል። ስለዚህ አሁን ይህ ሕግ ሲደነገር እኔ ከወዲሁ ጉዳቱ ተሰምቶኛል ምን ሸጬ ልኖር ነዉ? ይህ የእኔን ንግድ የሚያጠፋ ነዉ። በእጄ ያሉትንስ ምን ላድርጋቸዉ? ማን ይከፍለኛል?»

በማለት ያማርራሉ። ሕጉን ያወጣዉ የኬንያ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ባለስልጣናት የፕላስቲኩ በየቦታዉ መጣል የሀገሪቱን የዉኃ አካላት እንዲሁም የከብቶችን ጤና መበከሉን፤ ያም ደግሞ ወደሰዉ ሰዉነት ዉስጥ በተለያየ መልኩ እየገባ መሆኑን በመዘርዘር የተጣለዉ ዕገዳ የመጀመሪያ ርምጃ መሆኑን አሳዉቀዋል። በነገራችን ላይ ኬንያ ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ነዉ ይህን መሰል እገዳ በፕላስቲክ ላይ ስትጥል። በተመድ የአካባቢ ጥበቃ መርሃ ግብር መረጃ መሠረት ኬንያ ዉስጥ በየዓመቱ 100 ሚሊየን የዕቃ መያዣ ፕላስቲክ በየገበያ አዳራሹ ሥራ ላይ ይዉላል። በየዓመቱም ከመላዉ ዓለም ባህር ዉስጥ ከሚገኘዉ ቆሻሻ 8 ሚሊየን ቶኑ ፕላስቲክ መሆኑን የተመድ መረጃ ያመልክታል።

4. Bildergalerie Kenia Mülldeponie bei Nairobi

 ከጎረቤት ኬንያ ወደ ኢትዮጵያ ስንሻገር የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ የተመለከተ ሕግ ካወጣች 10 ዓመት እንዳለፋት እንመለከታለን። በ1999ዓ,ም የካቲት ወር በነጋሪት ጋዜጣ የወጣዉ ይህን የተመለከተዉ አዋጅ ዉፍረቱ 0,03 ሚሊ ሜትር እና ከዚያም በታች ሆኖ በስብሶ ከአፍር ጋር የማይዋሃድ የፕላስቲክ ከረጢት ማምረት ወይም ወደ ሀገር የማስገባት ፈቃድ መስጠት ይከለክላል። አዋጁ ከወጣ ወዲህ ተግባራዊነቱ እንዴት ነበር በሚል በአካባቢ የደን እና የአየር ንብረት ለዉጥ ሚኒስቴር የደረቅ እና ደገኛ ቆሻሻ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ገመቹ ሕጉ ከተሞች እና የአስተዳደር መዋቅሮች ደረቅ ቆሻሻ የሚስከትለዉን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ የሚያስችሉ የየራሳቸዉን አወጋገድ ስልት እንዲያቅዱ አቅም እንደፈጠር በመዘርዘር በተጨባጭ ያለዉን አብራርተዋል። ሙሉ ቅንብሩን ከድምጽ ዘገባዉ ያድምጡ፤

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ