1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚ

  የአዉሮጳ ኢንቨስትመንት ባንክ ብድር ለኢትዮጵያ 

ሰኞ፣ መስከረም 16 2009

የምጣኔ ሐብት አዋቂዎች እንደሚሉት ካለፈዉ ሕዳር ጀምሮ ኢትዮጵያ ዉስጥ የተቀጣጠለዉ ተቃዉሞና ግጭት ሐገሪቱን ለመዋዕለ ነዋይ ፍሰት የማትመች አድርጓታል።የመብት ተሟጋቾች ደግሞ የኢትዮጵያን መንግሥት በመብት ረጋጭነት እየወቀሱት ነዉ።የአዉሮጳ ባንክ በዚሕ ወቅት በጨቋኝነት ከሚወቀሰዉ የኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መዋዋሉን ተገቢ አይደለም የሚሉ አሉ።

https://p.dw.com/p/2Qaay
Europäische Investitionsbank (EIB)
ምስል picture-alliance/ dpa

የአዉሮጳ ኢንቨስትመንት ባንክ ብድር ለኢትዮጵያ 

 

የአዉሮጳ ኢንቨስትመንት ባንክ ኢትዮጵያ ለምታሰራቸዉ ሁለት የኢንዱስትሪ መንደሮች ግንባታ የሚዉል 200 ሚሊዮን ዶላር ብድር ሊሰጥ ነዉ።ባንኩ ብድሩን የሚሰጠዉ የኢንዱስትሪ መንደሮቹ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለተጠለሉ ለ30 ሺሕ የዉጪ ስደተኞች የሥራ ዕድል ሥለሚፈጥር ነዉ።የኢንዱስትሪ መንደሮቹን ለመገንባት አምስት መቶ ሚሊዮን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን ቀሪዉን 300  ሚሊዮን ዶላር የዓለም ባንክ፤ ብሪታንያና የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት ይሰጣሉ ተብሏል።

Europäische Investitionsbank (EIB)
ምስል picture-alliance/ dpa

 

ዉል፤ ፊርማዉ የአፈፃፀሙ እንዴትነት አይታወቅም።የብድሩ መጠን እና ዓላማዉ ግን የባንኩ የአፍሪቃ ጉዳይ የሕዝብ ግንኙነት ተጠሪ ሪቻርድ ዊሊስ እንደሚሉት ግልፅ ነዉ።ፕሮጄክቱም አዲስ። 
                                
«የአዉሮጳ ኢንቨስትመንት ባንክ ፕሬዝደንት ከኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ጋር ኒዮርክ ዉስጥ ከተነጋገሩ በኋላ ያወጁት ነዉ።ይሕ ለኛ ባሁኑ ወቅት የምንከታተለዉ አዲስ ፕሮጄክት ነዉ።ዝርዝሩን በመጪዎቹ ወራት እናረጋግጣለን ብለን እንጠብቃለን።»
ባንኩ ባለፉት አምስት ዓመታት ለአፍሪቃ የ13 ቢሊዮን ዶላር የወረት ብድር ሰጥቷል።ያሁኑ ግን ዊሊስ እንዳሉት አዲስ ነዉ።አዲስ የሚያደርገዉ ብድሩ የተሰጠዉ ኢትዮጵያ በገንዘቡ የምታሰራዉ ተቋም ለዉጪ ሐገር ስደተኞች ሥራ-እንዲያስገኝ ያለመ በመሆኑ ነዉ።
በሌላ አባባል የአዉሮጳ ሕብረት የአፍሪቃ ስደተኞች ወደ ግዛቱ እንዳይገቡ  ለማገድ ስደተኞቹ  ለሚነሱ ወይም ለሚተላለፉባቸዉ ሐገራት መንግሥታት ጠቀም ያለ ገንዘብ በመስጠት ስደተኞቹን በያሉበት  ለማስቆም የያዘዉ ዕቅድ አካል መሆኑ ነዉ።ዊሊስም በቀጥታ አላረጋገጡም።ግን  ሌላ አላሉም። 
                                  
«ኢትዮጵያም፤ የየአካባቢዉ ሕዝብም፤ ከጎረቤት ሐገራት የሚሰደዱ ሰዎችን በተቀበሉ ቁጥር ችግር ያጋጥማቸዋል።እዚሕ አዉሮጳም ስደተኞች የሜድትራኒያን ባሕርን ወይም በረሐ ሲያቋርጡ ሕይወታቸዉን ሲያጡ እናያለን።ይሕ ሁሉንም የሚያሳስብ ጉዳይ ነዉ።ለሰዎቹና ለቤተሰቦቻቸዉ ዘላቂ የሆነ የሥራ ዕድል እና  ሥልጠና እንዲያገኙ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠዉ መሠረታዊ ጉዳይ ነዉ።»
ሰዎች የሚሰደዱት ጭቆናን፤ ጦርነትን፤ ሽብርንና የምጣኔ ሐብት ችግርን ሽሽት ነዉ።የሥራ ዕድል ያዉም በተሰደዱበት ሐገር መፍጠር ችግሩን ቢያቃልል እንኳ ከብዙዎቹ ችግሮች ለአንዱ እንጂ ለሌሎቹ መፍትሔ አይሆንም።የመብት ተሟጋችም ስደተኞችን በየሐገራቸዉ ወይም በመተላለፊያ ሐገራት ለማገድ የሚወሰደዉን እርምጃ አጥብቀዉ ይቃወማሉ።
የአዉሮጳ ሕብረት፤ አባላቱና ተቋማቱ ግን ለእንቆቅልሹም፤ ለመብት ተሟጋቾች ተቃዉሞ ትችትም ሰሚ ጆሮ ያላቸዉ አይመስልም።
                                 
«ገንዘቡ፤ አፍሪቃ ዉስጥ ሰዎች የሚሰደዱበትም ሆነ አቋርጠዉ የሚያልፉበት ሐገራትን ለማሳደግና የሰዎቹን ኑሮ ለማሻሻል የሚረዳ ነዉ።ይሕ ብድርም ከአጎራባች ሐገራት ከሚሰደዱት ሰዎች እኩል ኢትዮጵያዉያንንም የሚጠቅም ነዉ።» 
የምጣኔ ሐብት አዋቂዎች እንደሚሉት ካለፈዉ ሕዳር ጀምሮ ኢትዮጵያ ዉስጥ የተቀጣጠለዉ ተቃዉሞና ግጭት ሐገሪቱን ለመዋዕለ ነዋይ ፍሰት የማትመች አድርጓታል።የመብት ተሟጋቾች ደግሞ የኢትዮጵያን መንግሥት በመብት ረጋጭነት እየወቀሱት ነዉ።የአዉሮጳ ባንክ በዚሕ ወቅት በጨቋኝነት ከሚወቀሰዉ የኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መዋዋሉን ተገቢ አይደለም የሚሉ አሉ።የባንኩ የሕዝብ ግንኙነት ተጠሪ ግን ፖለቲካ ዉስጥ አንገባም ባይ ናቸዉ።
                             
«ዞሮ ዞሮ በአንድ ሐገር ዉስጣዊ ፖለቲካዊ ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት የባንክ ሚና አይደለም።በግልፅ የሚታወቀዉ ግን በሰፊዉ ሲታይ ምጣኔ ሐብታዊ እና ፖለቲካዊ ዉጥረት ባለበት ፤ ይሕን በመሰለዉ ዓይነት መርሐ ግብር ድሕነትን ቅነሳ እና የሥራ ፈጠራን መርዳት መረጋጋት የሚሰፍንበትን መንገድ ማጠናከር እና ማሕበረሰቦች አብረዉ እንዲኖሩ መርዳት ነዉ።»
ኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞችን በማስተናገድ ከአፍሪቃ አንደኛ ናት።743 ሺሕ። 

Europäische Investitionsbank
ምስል PA/dpa
Philippe Maystadt Porträtfoto
ምስል AP

ነጋሽ መሀመድ

ሂሩት መለሰ