1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዉሮጳ የአሸባሪዎች መከላከያ መስሪያ ቤት

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 3 2003

በቅርቡ ደ ፈሪስን የተኩት የቤልጂጉ ተወላጅ ጊለስ ደ ኬርሾቨ ግን የቢን ላደን መገደልም ሆነ የሽብር ጥቃቱን የማክሸፉ ዉጤት የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይፈጠር በየጊዜዉ ያስጠነቅቃሉ

https://p.dw.com/p/RcB1
ደ ፍሪስምስል AP

የፀረ-ሽብር ዘመቻዉ የአዉሮጳ ሕብረትን የፀጥታ ጥበቃና ቁጥጥር ትብብርን አጠናክሮታል።የዚያኑ ያክል በሕብረቱ አባል ሐገራት ዜጎች ላይ የሚደረገዉን ፍተሻና ቁጥጥርም አባብሶታል።ትብብሩን በበላይነት የሚመሩ ባለሥልጣን ተመድበዋልም።

---------------------------------------

የአዉሮጳ ሐገራት አሸባሪነትን በጋራ የመዋጋቱን አስፈላጊነት የተቀበሉትና ትብብራቸዉን ያጠናከሩት በመስከረም 1: 1994 ጥቃት ማግሥት ነዉ።ይሁንና የአዉሮጳ ሕብረትን የፀረ-ሽብር ዘመቻ በበላይነት የሚመሩት የኔዘርላንዱ ተወላጅ ጊየስ ደ ፈሪስ እንዳሚያስታዉሱት እ.ጎ.አ 2004 የስጳኝዋ ርዕሠ-ከተማ ማድሪድ በአሸባሪዎች ተመታለች።በጥቃቱ ሁለት መቶ ሰዎች ተገድለዋል።ከዚያ አደጋ በሕዋላ የሕብረቱ የፀረ-ሽብር ዘመቻ ማስተባበሪያና ማቀናበሪያ ይበልጥ ተጠናከረ።

ደ ፈሪስ «የመረጃ ልዉዉጥ በጣም አስፈላጊ ነዉ» ይላሉ። «በዩሮፖል (EUROPOL) አማካይነት ፖሊሶች መረጃ እንዲለዋወጡ እናዳርጋለን።አቃቢያነ ሕጎቻችን ደግሞ በአዉሮጳ የፍትሕ መስሪያቤቶች ትብብር (በዩሮጀስት (EUROJUST) አማካይነት መረጃ መለዋወጥ ይችላሉ።አሸባሪዎች የገንዘብ ድጋፍ እንዳይደረግላቸዉ በሕግ እናግዳለን።» ቀጠሉ ሐላፊዉ «ይሕን ለማድረግ ግን ዓለም አቀፍ ትብርም ያስፈልጋል።» ብለዉ።

የቢን ላደን መሞት ብዙ የሚለዉጠዉ የለም

የጋራ ትብብሩና ጥብቅ ቁጥጥሩ ቢጠናከርም ቢያንስ አንድ ትልቅ የሽብር ጥቃትን መከላከል ግን አልተቻለም።የለንደኑን ሽብር። በለንደኑ የምድር ዉስጥ የመንገደኞች ባቡር ላይ እ.ጎ.አ በ2005 በተጣለዉ አደጋ ከሐምሳ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።ከዚያ ጊዜ በሕዋላ ግን አዉሮጳ ሠላም ናት።ፖሊስና የስለላ ባለሙያዎች በርካታ የሽብር ጥቃቶችን ማክሸፋቸዉን ይናገራሉ።

በቅርቡ ደ ፈሪስን የተኩት የቤልጂጉ ተወላጅ ጊለስ ደ ኬርሾቨ ግን የቢን ላደን መገደልም ሆነ የሽብር ጥቃቱን የማክሸፉ ዉጤት የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይፈጠር በየጊዜዉ ያስጠነቅቃሉ።«የዓል-ቃኢዳ ማዕከል ተፅዕኖ የማሳረፍ አቅሙ በአመት ሒደት ተዳክሟል።አሁን ደግሞ ይበልጥ ደቅቋል።ኦስማ ቢ ላደን ከእንግዲሕ ድርጅቱን ባይመራም (የመሪ) ናሙና (ምሳሌ) ነዉ።ይሕ ናሙና ደግሞ ባንድ በምሽት አይጠፋም።» ባይ ናቸዉ።

EU-Koordinator für Terrorismusbekämpfung Gilles de Kerchove
ኬርሾቨምስል picture-alliance / dpa

የፀረ-ሽብር ቁጥጥሩ ዜጎችን በሙሉ ለቁጥጥርና ክትትል ያገለጠ ይሆን?

የአዉሮጳ የፀረ-ሽብር ቁጥጥር ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አሠራሩ ትችት ተለይቶት አያዉቅም። በየሕዝብ መሰብሰቢያዉ በርካታ ካሜራዎች መተከላቸዉ፥ በየአዉሮፕላን ጣቢያዉ የሚደረገዉ ልዩ ፍተሻ እና ቁጥጥር፥ ከሁሉም በላይ የባንክ ሒሳብ እና የመገናኛ ልዉዉጥ (መረጃዎችን) መቆጣጠሩንና ለቁጥጥር ሲባል ሳይሰረዙ ለረጅም ጊዜ መቀመጣቸዉን ብዙ ሰዎች ከልክ ያለፈ እና የግለሰቦችን ነፃነት ክፉኛ የሚጎዳ በማለት ይተቹታል።

ያን-ፊሊፕ አልብሬሽት በአዉሮጳ ምክር ቤት የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ እንደራሴ ናቸዉ።«አጠቃላይ ራዕይ መኖር አለበት» ይላሉ።«የአዉሮጳ ሕብረት የፀረ-ሽብር እርምጃዎችን ዉጤታማነት ማረጋገጥ አለብን።ምናልባት ሁኔታዉ በተጋጋመበት ወቅት ባንድ ወይም በሌላ መልኩ የተወሰዱ ወይም በጣም በጥድፊያ የተከናወኑ እርምጃዎች፥ ለምሳሌ የሥልክ ንግግሮችን (ልዉዉጦችን) መቅረፅና ለረጅም ጊዜ ማስቀመጥ የመሳሰሉትን እርምጃዎች ማስተካከል ወይም ጨርሶ መሠረዝ አለብን።»

ብዙ መረጃዎች መሠብሰብና የግለሰብ ሚስጥርን በቅጡ መጠበቅ

የክርክሩ አብይ ጭብጥ ደሕንነትን በማስከበርና የግለሰቦችን ግላዊ ሚስጥር በመጠበቅ መሐል የሚያጠነጥን ነዉ።ሁለቱ፥ ደ ኬርሾቨ እንደሚያምኑት አይቃረኑም።«ምክንያቱም ሥጋቱ መልኩን ሥለቀየረ ብዙ መረጃዎችን መሠብሰብ አለብን።» ችግሩ ተጠርጣሪዎች በፖሊስና በሥለላ ባልደረቦች አለመታወቃቸዉ ነዉ።በዚሕም ምክንያት አጠራጣሪ፥ጉዞዎችን፥ እንቅስቃሴዎችን፥ ክፍያዎችን፥ የሥልክ ንግግሮችን መከታተልና መመርመር አስፈላጊ ነዉ።

«ይሁንና ከዚሁ ጋር የግለሰቦችን የግል ሚስጥር አጠባበቅን ይበልጥ ማሻሻል አለብን።ይሕ ማለት ሁለቱንም እኩል ማከናወን አለብን።» ይላሉ የአዉሮጳ ሕብረቱ የፀረ-ሽብብር ማስተባበሪያ ሐላፊ (አስተባባሪ)።አባባላቸዉ እንደከዚሕ ቀደሙ ሁሉ ልዩ ትክረት የሚሰጠዉ ብሔራዊ ደሕንነትንና ፀጥታን ማስከበር ነዉ።ግን መቀናጀት አለበት አይነት ነዉ።አስተባባሪዉ እንደሚሉት በሊዝበኑ ዉል መሠረት የተሰጣቸዉ ሐላፊነት በጊዜ ሒደት ወደ (ሕብረቱ) ኮሚሽን መሸጋገሩ አይቀርም።ያም ሆኖ አስተባባሪዉ እንደሚያምኑት ለወደፊቱም ማስተባበርን የሚሹ ብዙ ምግባሮች አሉ።

«እኔ ሐላፊነቱን ሥረከብ ግን ማስተባበሩ በቋሚነት ሥለመቀጠሉ የተናገረ ማንም የለም።» እና ጊለ ደ ከርሾቨ በቅርቡ ሥራ አጥ ይሆኑ ይሆን? እሳቸዉ አልሆንም ባይ ናቸዉ።

ክርስቶፍ ሀስልባኽ

ነጋሽ መሀመድ