1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ምርጫ

ማክሰኞ፣ ግንቦት 20 2011

የኢማኑዌል ማክሮ ፓርቲ ላሪፐብሊክ ኦን ማርሽ በአሁኑ የአውሮጳ ምክር ቤት ምርጫ በተቀናቃኙ የማሪን ለፔን ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ተሸንፏል። በማቲዮ ሲልቪኒ የተመራው ሊጋ የተሰኘው የኢጣልያ ቀን ጽንፈኛ ፓርቲ ደግሞ 32 በመቶ ድምጽ ሰብስቧል። ምንም እንኳን ቀኝ ጽንፈኞች ከቀድሞው የበለጠ ድምጽ ቢያሸንፉም እንደፎከሩት አልተሳካላቸውም።

https://p.dw.com/p/3JLwe
Eurpawahl Die Grünen Jubel
ምስል Getty Images/AFP/T. Schwarz

የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ምርጫ

የዘንድሮው የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት አባላት ምርጫ ያልተጠበቁም የተጠበቁም  ክስተቶችን ያስተናገደ ነበር። ከአስገራሚዎቹ ክሰቶትች መካከል አንዱ  ከዛሬ 5 ዓመቱ በተለየ የመራጮች ቁጥር ዘንድሮ ከፍ ማለቱ ነው። ድምጽ መስጠት ከሚችለው 400 ሚሊዮን አውሮጳዊ ድምጹን ለመስጠት የወጣው ወደ 51 ከመቶ ይጠጋል። ይህም በዛሬ አምስት ዓመቱ ምርጫ ከተሳተፈው ጋር ሲነጻጸር የ8 በመቶ ብልጫ አሳይቷል። ለአራት ቀናት ተካሂዶ ባለፈው ሳምንት በተጠናቀቀው በዘንድሮው የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ምርጫ የተሳተፈው አውሮጳዊ ቁጥር የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤቱ ምርጫ መካሄድ ከጀመረበት ከጎርጎሮሳዊው 1979 ወዲህ ከፍተኛው ከፍተኛው መሆኑ ተነግሯል።በምህጻሩ EPP የተባለውን የአውሮጳ ህዝብ ፓርቲ ወክለው ለህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት የጀርመኑ የክርስቲያን ሶሻል ህብረት ፓርቲው የ46 ዓመቱ ማንፍሬድ ቬበር ለዶቼቬለ DW በሰጡት አስተያየት እንዳሉት የመራጩ ቁጥር ዘንድሮ መጨመሩ ከምርጫው ዜና እጅግ አስፈላጊው እና ትርጉምም ያለው ነው።

«ህዝቡ ድምጹን በመስጠት ተሳትፏል።የአውሮጳን መጻኤ እድል ለመወሰን  የመምረጥ መብታቸውን ተጠቅመዋል።ይህም የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤትን ይበልጥ ተዓማኒ ያደርጋል፤የክፍለ ዓለሙን እውቅናም ይበልጥ ያጠናክራል።»

Deutschland | Europawahlen | Reaktion CDU Mitglieder
ምስል Getty Images/AFP/O. Andersen

ለዚህም አስተዋጽኦ አድርገዋል ከሚባሉት ውስጥ የህብረቱ የአካባቢ ጥበቃ መርህ እንዲሻሻል በአስራዎቹ እድሜ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በየሀገራቸው በየሳምንቱ የሚያሰሙት ተቃውሞ፤እንዲሁም የአውሮጳ ህብረትን የሚተቹት እና የሚቃወሙት ቀኝ ጽንፈኛ ብሔረተኛ ፓርቲዎችን የመከላከል አጣዳፋነት ትኩረት ማግኘቱ መሆናቸው ይገለጻል። በዘንድሮ ምርጫ መምረጥ ከሚችለው ከግማሽ በላይ የሚሆነው አውሮጳዊ ድምጹን መስጠቱ ስጋቶችን ቀንሷል ይላሉ «ካናታር የአውሮጳ መጻኤ እድል ምርምር እና ትንታኔ ማዕከል» ፕሬዝዳንት እና ተንታኝ ኢማኑኤል ሪቭየ። በርሳቸው አስተያየት የመራጩ ቁጥር ዘንድሮ መጨመሩ ትልቅ መልዕክት አስተላልፏል።

«በዚህ የአውሮጳ ህብረት ምርጫ ፣የመራጮች ቁጥር በ8 በመቶ ከፍ ማለቱ አንድ ትልቅ መልዕክት አለው።በሁለም ሀገራት ባይሆንም ከግምሽ በላይ በሚሆኑ አባል ሀገራት ከእኩሌታው በላይ ህዝብ ድምጹን ሰጥቷል። ጀርመን ፖላንድ ኦስትሪያ ፈረንሳይን በመሳሰሉት ሀገራት ምርጫው ትኩረት የሚስብ ነበር።በምርጫው የተሳተፈው ቁጥር መጨመሩ በብሔረተኛ ፓርቲዎች ጫና ውስጥ ወድቆ በነበረው በአውሮጳ፣ በብዙ ህዝብ ዘንድ አደጋ ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ይወስድ ለነበረው ለዚህ ምርጫ በጣም ጠቃሚ ነበር።በዚህ ምርጫ ይህ ያን ያህል አሳሳቢ እንዳይደለ አይተናል። እድሜ ለህዝቡ ተሳትፎ መጨመር የአውሮጳውያን ሃሳቦች አሁን ተጠናክረዋል።»

እሁድ የተጠናቀቀው የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ምርጫ ብርቱ ፉክክር የተካሄደበት ነበር። በዚህ ምርጫ የአውሮጳ ነባር እና አንጋፋ ፓርቲዎች ከቀድሞው ምርጫ ያነሰ ውጤት ሲያዝመግቡ ቀኝ ጽንፈኛ እና ለአካባቢ ጥበቃ የሚሟገተው የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ከቀድሞው የላቀ ድምጽ አሸንፈዋል።በእሁዱ ምርጫ ለአውሮጳ ህብረት መቀጠል የቆሙ ፓርቲዎች ከ751ዱ የምክር ቤት መቀመጫዎች ሁለት ሦስተኛውን ቢወስዱም  የህብረቱ ተችዎችንና ተቃዋሚ የሆኑ ፓርቲዎች በተለይ በፈረንሳይ እና በብሪግዚት በተከፋፈለችው በብሪታንያ ጥሩ ውጤት አግኝተዋል። ጀርመን ውስጥ ደግሞ የየመራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ህብረት እንዲሁም እህት ፓርቲያቸው ክርስቲያን ሶሻል ህብረት በጋራ ብዙ ድምጽ አጥተዋል። የCDU መራጭ ከነበረው ህዝብ የተወሰነው ለአረንጓዴዎቹ  እንዲሁም መጠነኛው ለቀኝ ጽንፈኞች ድምጹን በመስጠቱ ጥቂት የማይባል ድምጽ ነው የተነጠቁት። እነ የመሀል ቀኝ ወግ አጥባቂ ፓርቲዎች ካለፈው ምርጫ ያነሰ ውጤት ቢያስመዘግቡም 27.7 በመቶ ድምጽ በማሸነፍ የመሪነቱን ደረጃ ይዘዋል። በሀገር አቀፍ ደረጃ የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ከ20 በመቶ በላይ ድምጽ በማግኘት ሁለተኛ ሆኗል። በዘንድሮው ምርጫ ሶሻል ዴሞክራቶች አልቀናቸውም።ካለፈው ምርጫ 11.7 በመቶ ያነሰ ድምጽ ነው ያገኙት። በ15.6 በመቶ ድምጽ ሦስተኛ ሆነዋል።ውጤቱ ሶሻል ዴሞክራቶችን አሳዝኗል።ፓርቲው በተለይ ለአየር ንብረት ለውጥ ትኩረት አለመስጠቱ  ለሽንፈት ያበቃው አንዱ ምክንያት ነው ተብሏል። በአውሮጳ ምክር ቤት ፓርቲውን ወክለው ለኮሚሽኑ ፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት ፍራንስ ቲመርማንስ ፓርቲያቸው በብዙ ሀገራት የተሸነፈበት አንዱ ምክንያት ይኽው መሆኑን አምነው ፓርቲው ወደፊት ለህዝቡ ፍላጎት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባው ተናግረዋል።

Symbolbild Europawahl
ምስል picture-alliance/AP Photo/F. Seco

«መቀመጫዎችን ተነጥቀናል። ያ ማለት ሁሉንም ማቀፍ መቻል አለብን፣የፓርቲያችን መርሃ ግብር ግልጽ ሊሆን ይገባል።ያም ሆኖ አሁንም አዎንታዊ አመለካከት ነው ያለኝ ይኽውም ባለፉት ወራት ከአውሮጳውያን ከሰማሁት በመነሳት ነው።ህዝቡ የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ በአስቸኳይ አንድ ነገር እንድናደርግ ይፈልጋል።ህዝቡ በአውሮጳ ደረጃ ማህበራዊ ፍትህ እንዳይሰፍን እንቅፋት የሆኑትን እንድናስወግድ ይፈልጋል።ትላላቅ ኩባንያዎች ተገቢውን ቀረጥ መክፈል እንዲጀምሩ ፣እንድናደርግ እንዲሁም መሰል አስተሳሰብ ካላቸው በሀገር ደረጃ ልናስወግዳቸው የማንችላቸውን ችግሮች ከሚመስሉን አውሮፓውያን ጋር  በመስራት መፍትሄ እንድንፈልግላቸው ይሻሉ።»

Europawahl 2019 Marine Le Pen
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Spingler

ከቅርብ አመታት ወዲህ የአውሮጳ ህብረትን የሚተቹ ወይም የማይፈልጉ ቀኝ ክንፍ ፓርቲዎች ቁጥር በጣም ጨምሯል። በ2014ቱ ምርጫ እነዚህን ኃይሎች የሚወክሉ ሦስት ቡድኖች ከምክር ቤቱ መቀመጫ ሀያ በመቶውን ነበር ያገኙት ከዛ በቀደመው በጎርጎሮሳዊው 2009ኙ ምርጫ ግን እነዚህ ኃይሎች ያሸነፉት መቀመጫ 11 በመቶ ብቻ ነበር። በዘንድሮው ምርጫ ደግሞ እንደተፈራውም ባይሆን ከባለፈው መጨመሩ አልቀረም። እነዚህ ፓርቲዎች በፈረንሳይ በኢጣልያንና በብሪታንያ አብላጫ ድምጽ ነው ያገኙት። በጎርጎሮሳዊው 2017 በፈረንሳይ በተካሄደ ምርጫ የህዝቡ ድምጽ ለሥልጣን ያበቃው የኢማኑዌል ማክሮ ፓርቲ ላሪፐብሊክ ኦን ማርሽ በአሁኑ የአውሮጳ ምክር ቤት ምርጫ በተቀናቃኙ የማሪን ለፔን ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ ተሸንፏል። በማቲዮ ሲልቪኒ የተመራው ሊጋ የተሰኘው የኢጣልያ ቀን ጽንፈኛ ፓርቲ ደግሞ 32 በመቶ ድምጽ ሰብስቧል። የዛሬ አምስት ዓመት ግን 6 በመቶ ድምጽ ብቻ ነበር ያገኘው። ምንም እንኳን ቀኝ ጽንፈኞች ከቀድሞው የበለጠ ድምጽ ቢያሸንፉም ከዚህ ቀደም የአውሮፓ ህብረትን ለማፍረስ እንደፎከሩት አልተሳካላቸውም።ህብረቱን የሚደግፉ ፓርቲዎች ከምክር ቤቱ 751 መቀመጫዎች ሁለት ሶስተኛውን አሸንፈዋልና። በአውሮጳ ምክር ቤት ከሚገኙት 8 ቡድኖች መካከል ክርስቲያን ዴሞክራቶች እና ሶሻል ዴሞክራቶች እስካሁን በይፋ ባልታወጀ ህብረት በአንድ ላይ ሲሰሩ ቆይተዋል። ከ1979 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በጋራ አብላጫ ድምጽ ባጡበት በአሁኑ የምርጫ ውጤት መሠረት ግን ከገለልተኞች ወይም ከነፃዎቹ አለያም ከአረንጓዴዎቹ ጋር በጋራ መሥራት ግድ ሳይላቸው አልቀረም ይላሉ ኢማኑኤል ሪቭየ።።

Deutschland | SPD Reaktion | Europawahlen
ምስል Getty Images/AFP/J. Macdougall

«የሚያስገርመው ነገር ለወትሮው ተጻራሪ አቋም ያላቸው ፓርቲዎች የጋራ አቋም መያዛቸውን የሚቃወሙት ወገኖች በዚህ ምርጫ ምናልባት ከሶሻል ዴሞክራቶች እና ከአውሮጳውያን ፓርቲ ጋር ህብረት ለመፍጠር የሚያስችላቸው ጥሩ ውጤት አላቸው። ከነዚህም መካከል ALDE በሚል ምህጻር የሚታወቀው ነጻ ገበያ አራማጅ የገለልተኞች እና የዴሞክራቶች ህብረት ለአውሮጳ የተሰኘው ፓርቲ  በፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት በኢማኑዌል ማክሮ «ኦን ማርሽ» ፓርቲ ድጋፍ ከ100 በላይ መቀመጫዎች ያገኙት አንደኛዎቹ ሊሆኑ ይችላሉ።ከዚህ ሌላ ፍጹም ያልተጠበቀ ውጤት ያገኙት አረንጓዴዎቹ ሊሆኑ ይችላሉ።ከ20 በመቶ በላይ ድምጽ በማግኘት በጀርመን ሁለተኛውን ደረጃ ይዘዋል።በፈረንሳይ ደግሞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ናቸው።ይህም ያልተጠበቀ ነው። ለዚህ መብቃታቸው በአውሮጳ አሳሳቢነቱ ከጨመረው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ይያያዛል።»
ሆኖም ህብረት ለመፍጠር የሚካሄደውን ንግግር ውስብስብ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።በዚህ ምርጫ አስገራሚ ከተባሉት መካከል ካታሎንያ የተባለችውን የስፓኝን ግዛት ለመገንጠል የሚታገሉትን እና አሁን ቤልጂግ በስደት ላይ የሚገኙትን የቀድሞ የግዛቲቱትን ፕሬዝዳንት ካርልስ ፑጂሞን ጨምሮ ምክትላቸው እና የቀድሞ የካቢኔ አባላት የፓርላማ መቀመጫ ማሸነፋቸው ነው። በስደት ከሚኖሩበት ከብራስልስ ቤልጅየም ወጣ ብሎ በሚገኝ ስፍራ የምርጫ ዘመቻ ያካሄዱት ፑጂሞ እና ሌሎች ሁለቱ ባልደረቦቻቸው በስፓኝ መንግሥት የሚፈለጉ በመሆናቸው ችግር ሊገጥማቸው እንደሚችል ተገምቷል። እነዚህ የምክር ቤት መቀመጫ ያገኙ ሰዎች የምክር ቤት አባልነት የምስክር ወረቀታቸውን ማድሪድ ስፓኝ ሄደው መውሰድ ይኖርባቸዋል። በስፔይን ማዕከላዊ የምርጫ ቦርድ ተገኝተውም ቃለ መሃላ መፈጸም አለባቸው።ይሁን እና እነዚህን ማድረግ መቻል አለመቻላቸው እያነጋጋገረ ነው። የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት አባላት  በ28ቱ የህብረቱ አባል ሀገራት የሚገኙ 512 ሚሊዮን የአውሮፓ ዜጎችን ወክለው ሕጎችን ያወጣሉ። ብሪታንያ የአውሮጳ ህብረትን ለቃ ከወጣች የምክር ቤት አባላቱ ቁጥር ወደ 705 ዝቅ ይላል። ምክር ቤቱ ባለፈው የስራ ዘመኑ 1100 ህጎችን አጽድቋል። እነዚህ ሕጎችም በየአባል ሀገራቱ ምክር ቤቶች መጽደቅ ይኖርባቸዋል።የአውሮፓ ምክር ቤት ምርጫ ነጻ እና ፍትሀዊ ነው ቢባልም አሰራሩ መተቸቱ አልቀረም።አባል ሀገራት የምክር ቤቱ መቀመጫ የሚያገኙት በህዝባቸው ቁጥር መሠረት ነው።ሆኖም በዚህ አሰራር ተጠቃሚዎቹ ብዙ ህዝብ ያላቸው ሳይሆኑ አነስተኛ ህዝብ ያላቸው ሀገራት ናቸው የሚሉ ስሞታዎች ይቀርባሉ።ለምሳሌ 80 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ጀርመን ፣በምክር ቤቱ 96 መቀመጫዎች አሏት።600 ሺህ ህዝብ ያላት ትንሽትዋ ሀገር ሉክስምበርግ ግን 6 የምክር ቤት አባላት መላክ ትችላለች።ይህ በንጽጽር ሲታይ ጀርመን አነስተኛ ውክልና ነው የተሰጣት ሲል የፌደራል ጀርመን ህገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ቅሬታ ያቀርባል።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ