1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ህብረት የስደት ፖሊሲ እና ትችቱ 

ማክሰኞ፣ ጥር 28 2011

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ወጣት አፍሪቃውያን እጅግ አደገኛ በሚባሉ የየብስ እና የባህር ጉዞዎች ወደ አውሮጳ ለመሰደድ የሚያደርጉት ሙከራ ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኖ ዘልቋል። የስደተኛው ቁጥር በዝቶብናል የሚሉ በርካታ የአውሮጳ ሀገራት ደግሞ  ስደተኞች እንዳይመጡባቸው ጥብቅ የድንበር ቁጥጥር ዘርግተዋል።

https://p.dw.com/p/3CmER
Symbolbild | Flüchtlinge im Mittelmeer
ምስል picture-alliance/dpa/AP/S. Palacios

የአውሮጳ ህብረት የስደት ፖሊሲ እና ትችቱ 

በህገ ወጥ መንገድ ሀገራችን ገብተዋል የሚሏቸውንም ወደመጡበት ይመልሳሉ። ይሁን እና አንድ የፍልሰት ጉዳዮች አጥኚ እና አማካሪ፣ በእነዚህ እርምጃዎች አውሮጳውያን ከፍልሰት የሚያገኟቸውን ጥቅሞች እያጡ ነው ሲሉ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ተናግረዋል። የሰው ልጅ በተለያዩ ምክንያቶች ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ተዘዋውሮ መኖር መሥራቱ ያለ ፣የነበረ እና ወደፊትም የሚቀጥል ነው። እንደ ቀደሙት ጊዜያት ሁሉ ባለንበት ዘመንም ሰዎች በፈቃዳቸው፣በሞያቸው ተፈላጊነት ወይም በተለያዩ አስገዳጅ ፖለቲካዊ ኤኮኖሚያዊ እና ተፈጥሮአዊ ምክንያቶች የትውልድ ሀገራቸውን እየተዉ ወደ ሌሎች ሀገራት ይሰደዳሉ። ይህ የተለመደ ቢሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ወጣት አፍሪቃውያን እጅግ አደገኛ በሚባሉ የየብስ እና የባህር ጉዞዎች ወደ አውሮጳ ለመሰደድ የሚያደርጉት ሙከራ ግን ብዙ ትኩረት የሳበ ጉዳይ ሆኖ ዘልቋል። የስደተኛው ቁጥር በዝቶብናል የሚሉ በርካታ የአውሮጳ ሀገራት ደግሞ  ስደተኞች ድርሽ እንዳይሉባቸው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በደቡባዊ የክፍለ ዓለሙ ድንበር ሀገራት ጥብቅ ቁጥጥር ዘርግተዋል። ከአውሮጳ የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግላቸው የአፍሪቃ መንግሥታትም ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ የሚካሄድ ስደትን ለመከላከል በትብብር እየሰሩ ነው። የአውሮጳ ሀገራት ህገ ወጥ የሚሏቸውን ተገን ጠያቂዎችን ማመልከቻዎችንም ውድቅ በማድረግ ወደ መጡባቸው ሀገራት ይመልሳሉ። ስደተኞችን ተስፋ ለማስቆረጥ የሚወሰዱት እነዚህን መሰል እርምጃዎች  ከጥቅማቸው ጉዳታቸው እንደሚያመዝን የፍልሰት ጉዳይ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። ስቴፋን አዳዌን በፍልሰትና በልማት ጉዳዮች ላይ በጀርመን እና በአፍሪቃ ለሚገኙ የጥናት ተቋማት እና ሌሎች ድርጅቶች በአማካሪነት የሚሰሩ የጋና ተወላጅ ናቸው።በርሳቸው አስተያየት የአውሮጳ ህብረት ስደትን ለመግታት የሚከተለው ይህን መሰሉ አቅጣጫ እንደገና ሊፈትሽ እና ሊታሰብበት ይገባል። የህብረቱ የድንበር ቁጥጥር፣በስደት ላይ የጣለው እገዳ እና ስደተኞችን መመለስም እጅግ የተጋነኑ እርምጃዎች ናቸው ይላሉ። በእነዚህ እርምጃዎች ሰዎች ወደ አውሮጳ እንዳይመጡ መከላከል መቻሉ አይታያቸውም። ከዚያ ይልቅ ተመራማሪው አዳዌን  አውሮጳውያን ከፍልሰት በሚገኘው ጥቅም ላይ ቢያተኩሩ ይሻላል ይላሉ።
«ፍልሰት በአግባቡ ከተያዘ ልማትን የማመቻቻ አንዱ መንገድ ነው። ከውጭ የሚላክ ገንዘብን እንመልከት ለአብዛኛዎቹ አፍሪቃውያን ቁልፍ ሚና አለው። አውሮጳም ከፈላስያን ጉልበት ትጠቀማለች። ምክንያቱም የሰው ኃይል እጥረት ያለባቸው የምጣኔ ሀበት ዘርፎች አሉ። ይህን ግምት ውስጥ ያስገባ የሰዎች እንቅስቃሴን ቢፈቅዱ ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናል።» አሁን ያሉትን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት የአፍሪቃን የህዝብ ቁጥር እድገት፣ የምጣኔ ሀብት ልማት ፈተናዎችን እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥ እና ግጭቶችን ስንመለከትም እኔ በበኩሌ መሠረታዊዎቹ ችግሮች ካልተፈቱ ስደት ይቀንሳል ብዬ አላስብም። ስለዚህ እንቅስቃሴን ከመገደብ ይልቅ ፍልሰትን በአግባቡ መጠቀም ይገባል።»  
የአውሮጳ መንግሥታት የስደት መነሻ እና መተላለፊያ የሆኑ የአፍሪቃ ሀገራት ስደትን ለማስቆም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በተለያየ መንገድ ግፊት ያደርጋሉ። ወጣቱ እንዳይሰደድ በአፍሪቃ ሀገራት ለሥራ ፈጠራ ይውላሉ የተባሉ የገንዘብ የቁሳቁስ እና የቴክኒክ ድጋፍ ስምምነቶች ከአውሮጳ መንግሥታት ጋር ተደርገዋል። ቃልም ተገብቶላቸዋል። በአመዛኙ የአፍሪቃ መንግሥት የዜጎቻቸውን አስከፊ ስደት ለመከላከል ብዙም ደንታ እንደሌላቸው ተደርጎ ይቆጠር እንጂ በሁኔታው ደስተኛ አይደሉም በአዳዌን አመለካከት። ዜጎቻቸው ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ወደ አውሮጳ ከሄዱ በኋላ እንዳይገቡ መከልከላቸው ከገቡ በኋላም መባረራቸው የአፍሪቃ መንግሥታትን ማሳዘኑም አይቀርም ይላሉ። ይህ የሚሆነው በርሳቸው አባባል መንግሥታቱ በውጭ ከሚኖሩ ዜጎቻቸው ሊያገኙ የሚችሉትን ጥቅምም የሚያስቀር በመሆኑ ነው።
«አንዳንድ ሰዎች የሚሰደዱት በአሳማኝ ምክንያቶች ነው። መንግሥታቱ ዳያስፖራው በሚልከው ገንዘብ ተጠቃሚ ናቸው። ጥቅሙ የገንዘብ ብቻ አይደለም። እውቀት እና ክህሎትን ይዘው ወደ ሀገራቸው የሚመለሱም አሉ።  እናም  ከስደቱ ተጠቃሚ ከሆኑ አውሮጳውያን ዜጎቻቸውን ሲመልሱባቸው እንዴት ደስተኛ ይሆናሉ።»
ስለዚህ በአዳዌን አስተያየት መሆን ያለበት  ደህንነቱ የተረጋገጠ እና ህጋዊ ስደትን ማበረታታት ነው። በሌላ በኩል አብዛኛዎቹ የአፍሪቃ ሀገራት ከስደት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ከአውሮጳ ህብረት ጋር የጀመሩት አጋርነት በእኩል ደረጃ የሚካሄድ ነው ብለው አያስቡም እንደ አዳዌ። 
«አብዛኛዎቹ የአፍሪቃ ሀገራት የአፍሪቃ መንግሥታትን እንደ እኩል አጋር ማየት እና መተባበርን በሚያካትተው በጋራው የአጋርነት ስምምነት አውሮጳውያን ትኩረት ሰጥተዋል የሚል ስሜት የላቸውም። ስለዚህ አንዳንዶቹ መንግሥታት የአውሮጳ ህብረት ከበላይ ሆኖ ለማዘዝ የሚሞክር ሆኖ ነው የሚሰማቸው። ስደትን ለመቆጣጠር ለአፍሪቃ መንግሥታት የሚሰጣቸው የማበረረታቻ ገንዘብም ያህን ያህል አይደለም። ስለዚህ ከአፍሪቃ መንግሥታት በኩል ህገ ወጥ የሚባለውን ስደት የማስቆም ፍላጎት አለ። ሆኖም አውሮጳ እና አፍሪቃ ደህንነቱ የተጠበቀ ህጋዊ ስደተን ማበረታቱ ላይ ማተኮር አለባቸው።»
ይህ ገቢራዊ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ለተማሪዎች ነጻ የትምህርት እድል እና የሙያ ሥልጠናዎችን በመስጠት፣  በአውሮጳ ተፈላጊ የሆኑ ሙያተኞችን ለምሳሌ ነርሶችን የመሳሰሉ የጤና ባለሞያዎች  በተደራጀ መንገድ በአውሮጳ የሥራ ገበያ ሊሰማሩ የሚያስችላቸውን ፣የሠራተኛ ፍልሰት አጋርነትን በመመስረት ነው። አዳዌን ለዚህ ሀገራቸው ጋና ውስጥ ያለውን ሁኔታ በምሳሌነት አቅርበዋል። ጋና  ይላሉ አዳዌን በርካታ ነርሶች አሏት ።ሆኖም የሀገሪቱ የጤና ዘርፍ ለሁሉም ስራ መስጠት አልቻለም። እናም እነዚህ የሰለጠኑ ባለሞያዎች የነርስ እጥረት ባለባቸው ጀርመንን በመሳሰሉ ሀገራት መሥራት ቢችሉ ጥቅሙ የሁለቱም ሀገራት ይሆናል ሲሉ ያስረዳሉ።
« በሚቀጥሉት 20 እና 25 ዓመታት ጀርመን ቁጥሩ 150 ሺህ ሊደርስ የሚችል የነርሶች እጥረት ይደርስባታል። ይህ ትልቅ አሀዝ ነው። እናም ጋናውያን እድሉን አግኝተው እዚህ ከመጡ ወደ ሀገራቸው ገንዘብ መላክ ይችላሉ። በጀርመን ቆይታቸው አዳዲስ ቴክኒኮችን ቀስመው ከዓመትት በኋላ ወደ ሀገራቸው ጋና ይመለሳሉ። ሰዎች ጀርመን መጥተው ወደ ሀገራቸው መመለስ መቻላቸውን ካወቁ ለምን ይቀራሉ። በአደገኛ ጉዞስ ለምን ይጀምራሉ። ስለዚህ ይበልጥ ፈታ ያለ የቪዛ አሰጣጥ ይህን ለማመቻቸት ይረዳል።»  
ይህም ሁለቱንም ወገን የሚጠቅም እርምጃ ሊሆን እንደሚችልም ያስረዳሉ። ይሁን እና አንዳንድ ምሁራን  እና ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎቹ ጀርመን መጥተው ጥሩ ሥራ ካገኙ ወደ ሀገራቸው አይመለሱም፤ይህ ደግሞ በአፍሪቃ የምሁራን ወይም የሰለጠኑ ባለሞያዎች እጥረት ይፈጥራል ሲሉም ይከራከራሉ። አዳዌን በዚህ አይስማሙም።
«ይህ አይደለም ጉዳዩ። እዚህ መጥተው ወደ ሀገራቸው የተመለሱ ሰዎች አሉ። ለዚህ ብዙ ምሳሌዎች አሉ። ግልጽ አሳሪ ውሎች ሊደረጉ ይችላሉ፤ ሰዎች ጀርመን መጥተው ለሦስት ለ4 ዓመታት መሥራት፣ ክህሎታቸውን ማዳበር ከዚያ በኋላ ደግሞ መርሃ ግብሩ ዘላቂነት እንዲኖረው ወደ ሀገራቸው መመለስ አለባቸው። ሁኔታው ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ነው። ጀርመን ከባለሞያዎቹ ተጠቃሚ መሆን አለባት። የዐዕምሮ ብዝበዛ እዚህ ላይ የሚነሳ አይደለም።ሂደቱ በሥራ ውሎች እና ስምምነቶች በአግባቡ መመራት ይገባዋል።»
የስደት ጉዳዮች ተመራማሪው አዳዌን ሁለቱን ወገኖች ተጠቃሚ ያደርጋል የሚሉትን መፍትሄ ከግምት ውስጥ በማስገባት የአውሮጳ ህብረት የስደት ፖሊሲው ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለበት ይገነዘባል ብለው ያምናሉ። በርሳቸው አስተያየት ወደዚህ ዓይነቱ መፍትሄ የመሳብ አዝማሚያም አለ። ለዚህም በምሳሌነት የሚያነሱት ጀርመን መንግሥት የሶስተኛው ዓለም ሀገራት ባለሞያዎችን ክህሎት ወደ ጀርመን ለማሸጋገር ያወጣውን አዲስ የስደት ጉዳዮችን ህግ ነው።
«ጀርመን በምጣኔ ሀብት የበላይ ሆና ለመዝለቅ የማህበራዊ ዋስትና ስርዓትዋን እና የሰው ኃይልዋን ዘላቂነት አስተማማኝ ለማድረግ ስደተኞችን ማስገባት አለባት። ምክንያቱም የአብዛኛው የጀርመን ህዝብ እድሜ እየገፋ ነው የሚሄደው። የምጣኔ ሀብት እድገቱ ዘላቂ እንዲሆን በሀገሪቱ ማህበራዊ ድጎማ ስርዓት ላይ ጥገኛ የማይሆኑ ሰዎችን ማስገባት ያስፈልጋል። እንደ ጀርመን ሁሉ ሌሎች የአውሮጳ ሀገራትም ይህን መገንዘብ ጀምረዋል። ሆኖም መልዕክቱ መገናኛ ብዙሀን እና ተመራማሪዎች መልዕክቱን በተገቢው መንገድ ማስተላለፍ ይኖርባቸዋል።»
አዳዌን እነዚህ አካላት ጥቅሞቹን እና ስጋቶቹን ለይተው የማስቀመጥ ሃላፊነት አለባቸው ይላሉ ።

Spanien | 314 gerettete Flüchtlinge erreichen des Hafen von Malaga
ምስል picture-alliance/dpa/ZUMAPRESS
Efenbeinküste EU-Afrika-Gipfel in Abidjan Gruppenbild
ምስል picture-alliance/AP Photo/G. V. Wijngaert
Mittelmeerroute - Flüchtlinge im Boot
ምስል picture-alliance/dpa/AP/E. Morenatti
Spanien Hunderte Flüchtlinge stürmen in spanische Nordafrika-Enklave
ምስል imago/Agencia EFE/Reduan

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ