1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ህብረት እና የብሪታንያ ፍቺ 

ማክሰኞ፣ መጋቢት 26 2009

ድርድሩ በአውሮፓ ኅብረት የጋራ ገበያ ውስጥ ከ40 በመቶ በላይ የውጭ ንግድ ለምታካሂደው ለብሪታንያም ሆነ ከዓለም በኤኮኖሚ አምሰተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘዋን እና ለህብረቱ ከፍተኛ የበጀት አስተዋጽኦ የምታደርገውን ብሪታንያን ለሚያጣው ለአውሮፓ ህብረት ቀላል እና ከችግር የፀዳ እንደማይሆን ከወዲሁ እየተነገረ ነው ።

https://p.dw.com/p/2agei
EU Großbritannien Brexit Brief Botschafter Barrow mit Tusk
ምስል Getty Images/AFP/Y. Herman

የአውሮጳ ኅብረት እና የብሪታንያ ፍቺ 

ብሪታንያ ከአውሮጳ ኅብረት አባልነት ለመውጣት እንደምትፈልግ ባለፈው ሳምንት ለአውሮጳ ኅብረት ባቀረበችው ደብዳቤ በይፋ አሳውቃለች ። የአውሮጳ ኅብረትም ብሪታንያ ከኅብረት የምትወጣበትን ረቂቅ  የመደራደሪያ መመሪያዎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ለአባል ሀገራት ልኳል ። ብሪታንያ ለ44 ዓመታት በአባልነት ከቆየችበት ከአውሮጳ ኅብረት እንደምትወጣ በደብዳቤ በይፋ ካሳወቀች ዛሬ ሰባት ቀናት ተቆጠሩ ። የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ከ9 ወር በፊት በተካሄደ ህዝበ ውሳኔ የብሪታንያ ህዝብ ከህብረቱ ለመውጣት መወሰኑን የሀገሪቱ ፓርላማም ይህንኑ ማፅደቁን በዚሁ ደብዳቤያቸው አስታውሰው ፣በሊዝበኑ ውል አንቀጽ 50  መሠረት ሀገራቸው ከአውሮጳ ኅብረት አባልነት ለመውጣት እንደምትፈልግ አስታውቀዋል ። ሜይ ለሀገራቸው ፓርላማ እንደተናገሩት ሀገራቸው ብሪታንያ ላትመለስ ነው ከህብረቱ የምትወጣው ። 
«ይህ ወደ ኃላ ልንመለስ የማንችልበት ታሪካዊ ወቅት ነው ። ብሪታንያ ከአውሮፓ ኅብረት ትወጣለች ። የራሳችንን ውሳኔዎች እና የራሳችንን ህጎች እናወጣለን ። ይበልጥ የሚያሳስቡንን ጉዳዮች በኛ ቁጥጥር ስር እናደርጋለን ።» 
ብሪታንያ ለአውሮፓ ኅብረት ያቀረበችው የመልቀቂያ ደብዳቤ ሁለቱ ወገኖች የፍቺውን ድርድር የሚጀምሩበትን መንገድ ከፍቷል ። የአውሮጳ ኅብረት ከደብዳቤው በኋላ  ረቂቅ የመደራደሪያ መመሪያዎችን ለአባል ሀገራት ልኳል ። የአባል ሀገራት መሪዎችም ከ25 ቀናት በኋላ በሚያካሂዱት ጉባኤ በረቂቁ ላይ ተነጋግረው ስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል ። ድርድሩ ከሁለት ወር በኋላ እንደሚጀመር ይጠበቃል ። የአውሮጳ  ኅብረት ዋነኛ ተደራዳሪ ሚሼል ባርንየ 20 ከሚደርሱ የቡድናቸው ጠበበት ጋር በመሆን ነው ከብሪታንያ ጋር ድርድር የሚያካሂዱት ።  የሁለት ዓመት የጊዜ ገደብ የተቀመጠለት ይኽው ድርድር በባርንዮ ቡድን ግምት በ18 ወራት ውስጥ ሊጠናቀቅ ይችላል ። ድርድሩ በአውሮፓ ኅብረት የጋራ ገበያ ውስጥ ከ40 በመቶ በላይ የውጭ ንግድ ለምታካሂደው ለብሪታንያም ሆነ ከዓለም በኤኮኖሚ አምሰተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘዋን እና ለህብረቱ ከፍተኛ የበጀት አስተዋጽኦ የምታደርገውን ብሪታንያን ለሚያጣው ለአውሮፓ ኅብረት ቀላል እና ከችግር የፀዳ እንደማይሆን ከወዲሁ እየተነገረ ነው ። ለመሆኑ የአውሮጳ ኅብረት እና ብሪታንያ የሚያካሂዱት የፍቺ ድርድር ዋነኛ ትኩረት ምንድነው ? ።አቶ ታዬ አለማየሁ ከ26 ዓመት በላይ ብሪታንያ የኖሩ የህግ ባለሞያ እና የአውሮጳ የስደተኞች ሕግ አማካሪ ናቸው ፣ ርሳቸው እንደሚሉት ድርድሩ ይበልጥ ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች ውስጥ የሰዎች ዝውውር ንግድ እና የፋይናንስ ተቋማት አገልግሎት ይገኙበታል ። በአሁኑ ጊዜ ብሪታንያ ውስጥ ከ3.3 ሚሊዮን በላይ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ዜጎች ይኖራሉ ። በተቀሩት የህብረቱ አባል ሀገራት ውስጥ የሚኖሩት ብሪታንያውያን ቁጥር ደግሞ ወደ አንድ ሚሊዮን ይጠጋል ። ብሪታንያ ከአውሮጳ ኅብረት እንድትወጣ የሚፈልጉ ወገኖች ከህዝበ ውሳኔው በፊት  ደጋግመው ያነሷቸው ከነበሩት ጉዳዮች ውስጥ የውጭ ዜጎች የብሪታንያውያንን ሥራ ይሻማሉ የሚለው ክርክር አንዱ እንደመሆኑ ለዚህ ጉዳይ ብራሰልስንም ሆነ ለንደንን የሚያረካ መፍትሄ ማግኘቱ ቀላል እንደማይሆን ይገመታል ። ከዚህ ሌላ ለንደን ከዚህ ቀደም ለአውሮጳ ህብረት መክፈል የነበረባት እና  ልትከፍል ቃል የገባችው 60 ቢሊዮን ዩሮ የሚገመት ገንዘብ ጉዳይም እንዲሁ በድርድሩ ይካተታል ተብሏል ። የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶናል ቱስክ  ድርድሩ አስቸጋሪ ውስብስብ እና አንዳንዴም ፍጥጫ የሚኖርበት ሊሆን ይችላል ብለዋል ። ይህን ያስታወሱት አቶ ታዬ የቱስክ ስጋቶች እውን ሊሆን የሚችሉባቸውን ምክንያቶች ያስረዳሉ ። 
የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ ሀገራቸው ከህብረቱ አባልነት ስትወጣ ከተቀሩት የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ጋር በነፃ ንግዱ መቀጠል ነው የሚፈልጉት ። ብሪታንያ ከኅብረቱ ጋር አለመቀጠሏ ሀገሪቱ አማሮኛል የምትለውን  ቁጥጥር የማይካሄድበትን ከመሀል አውሮጳ ወደ ብሪታንያ የሚደረግ ስደትን የመሳሰሉ ችግሮችን እንዲሁም በዓመት ለአውሮጳ ኅብረት ትከፍል የነበረውን የ12 ቢሊዮን ዩሮ መዋጮም ያስቀራል ። ይሁን እና የኤኮኖሚ ባለሞያዎች እንደሚሉት ብሪታንያ በፍቺው ከምታገኘው የምታጣው ይበልጣል ። ስቴፋን ዉድሎክ በለንደን ስኩል ኦፍ ኤኮኖሚክ የንግድ ጉዳዮች አዋቂ ናቸው ። ብሪታንያ ከአውሮፓ ኅብረት ስትወጣ አወስዳቸዋለሁ የምትላቸው አማራጮች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ አይደሉም ይላሉ ።
« ስሜታዊ ሳትሆን የድርድሩ መመዘኛዎች ስትመለከት ብሪታንያ ጠንካራ የመደራደር አቅም አላት ብዬ አላስብም ። ኤኮኖሚዋ ትንሽ ነው ። ይበበልጡን የአውሮጳ ኅብረት ጥገኛ የሆነችው እርስዋ ናት ። በድርድር ጊዜ ታጋሽ ወገን ጠንካራ ነው ይባላል ። አሁን ብሪታንያ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ አንድ መደምደሚያ ላይ መድረስ አለባት ብሪታንያ ያሏት አማራጮች ምንድናቸው ተብሎ ሲጠየቅ የሚነሳው ከቻይና ከህንድ እና ከሌሎችም ትላልቅ ገበያ ካላቸው ሀገራት ጋር ልንደራደር እንችላለን የሚል ነው መከራከሪያው ። ለኔ ይህን ተግባራዊ ማድረግ የማይቻል ነው ።በእነዚህ ስምምነቶች ላይ መደራደር ረዥም ጊዜ ይወስዳል»
ብሪታንያ ብዙታጣለች ሲባል የአውሮጳ ኅብረት በብሪታንያ መልቀቅ አይጎዳም ማለት አይደለም ። በዉድሎክ አስተያየት በድርድሩ አሸናፊም ተሸናፊም አይኖርም ። ይልቁንም ማን ብዙ ያጣል ማን በመጠኑ ይጎዳል ነው ጥያቄው  ። አቶ አታዬ አለማየሁም ተመሳሳይ አስተያየት ነው ያላቸው ። 
ብሪታንያ ከአውሮጳ ህብረት አባልነት የምትወጣ የመጀመሪያ ሀገር ናት ። በሌሎች የህብረቱ አባል ሀገራት በተለይ ብሔረተኛ ፓርቲዎች ሥልጣን ከያዙ የብሪታንያን ፈለግ ሊከተሉ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ። ይሁን እና በአሁን ደረጃ 27ቱ የኅብረቱ አባል ሀገራት የብሪታንያ መውጣት ይበልጥ እንዲጠነክሩ የሚያደርጋቸው እንጂ የሚለያያቸው እንደማይሆን እያሳዩ ነው ። ባለፈው ሰሞን የተፈራረሙት አዲሱ የሮሙ ውልም ለዚህ እንደ አንድ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል ። ከብሪታንያ ህዝብ አንዳንዱ ከአውሮጳ ኅብረት መውጣት በራስ መተማመንን የሚያሳይና ነፃነትን የሚያጎናጽፍ አድርጎ ነው የተወሰደው ። ለሌሎች ደግሞ ወደማይታወቅ አቅጣጫ እንደመግባት ነው የታየው ።  ከሁለት ወር በኋላ ይጀመራል ተብሎ የሚጠበቀው የአውሮፓ ኅብረት እና የብሪታንያ የፍቺ ድርድር በተያዘለት የሁለት ዓመት ጊዜ ላያበቃ ይችላል የሚል ግምት አለ ። ከዚያ በኋላ ሁለቱ ወገኖች የሚደራደሩበት የወደፊቱ የንግድ ውል ከሁለት እስከ አምስት ተጨማሪ ዓመታት ሊወስድ  እንደሚችል ይነገራል ። 

Italien EU Gipfel
ምስል picture-alliance/dpa/A.Tarantino
Brexit Symbolbild
ምስል picture alliance/Klaus Ohlenschläger
England Theresa May unterschreibt Brexit-Antrag
ምስል REUTERS/C. Furlong

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ