1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓው ኅብረት መሪዎች፧ አዲሱ ህገ መንግሥት ነክ ውል፧

ዓርብ፣ ጥቅምት 8 2000

በዓለም የአየር ንብረት ለውጥና በዓለም አቀፉ አጽናፋዊ የኤኮኖሚ ትሥሥር ላይ ለመምከር ሊዝበን፧ ፖርቱጋል ውስጥ የተሰበሰቡት የኻያ ሰባቱ አውሮፓው ኅብረት አባል አገሮች መሪዎች ሁለት ዓመታት ሲያነታርክ ለቆየው የኅብረቱ ረቂቅ ህገ-መንግሥት፧ በዛሬው ዕለት እልባት ያደረጉለት መሆኑ ተገለጠ።

https://p.dw.com/p/E87b
ምስል AP

አሁን ውድቅ የሆነውን ረቂቅ ህገ-መንግሥት፧ ቀደም ሲል ፈረንሳይና ኔደርላንድ፧ በውሳኔ-ህዝብ ውድቅ ያደረጉት መሆኑ አይዘነጋም። አሁን፧ በግልግል ሥምምነት የተደረገበት ውል፧ የወቅቱን የአውሮፓው ኅብረት ፕሬዚዳንት የፖርቱጋልን ጠቅላይ ሚንስትርና ባጠቃላይ አባል መንግሥታቱን አርክቷል። ከብራሰልስ Anke Hagedorn የላከችልንን ዘገባ ተክሌ የኋላ እንደሚከተለው ሰብሰብ አድርጎ አቅርቦታል።
የአውሮፓው ኅብረት አባል መንግሥታት መሪዎች አሁን የተስማሙበትን አዲስ ውል፧ የፊታችን ታኅሳስ 3 ቀን 2000 ዓ ም፧ በፊርማቸው ያጸድቁታል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚያም የየሃገራቱ ፓርላማዎች በህግ እስኪያጸድቁት የአንድ ዓመት ጊዜ የተሰጠ ሲሆን፧ እ ጎ አ ከ ጥር 1 ቀን 2009 ዓ ም አንስቶ በተግባር እንደሚተረጎም ነው እቅዱ የሚያመላክተው። የፖርቱጋል ጠቅላይ ሚንስትር Jose Socrates በአዲሱ ውል ላይ ስምምነት መደረጉን መንስዔ በማድረግ በሰጡት ቃል።
«ይህ ለአውሮፓ ድል ነው። በአዲሱ የተሃድሶ ለውጥ ስምምነት መሠረት አውሮፓ፧ በመጨረሻ ግትር አቋሙን ማስወገድ ችሏል።«
የጀርመን መራኂተ-መንግሥት ወይዘሮ አንጌላ ሜርክልም፧ በሥምምነቱ ተደስተዋል።
«በዛሬው ምሽት እዚህ የተገኙት ብዙዎቹ፧ ባለፉት ስድስት ዓመታት፧ በዚህ ርእስ ዙሪያ ሲነጋገሩ ቆይተዋል። ጀርመን ፕሬዚዳንት ሆና ባሳለፈቸው ጊዜያት ያዘጋቸው ረቂቅ ውል አሁን በተረኛይቱ በፖርቱጋል አመራር ተሳክቶ እልባት ለማግኘት ችሏል።«
የአውሮፓው ኅብረት የተሃድሶው ውል፧ አሁን ቁጥራቸው ወደ 27 ከፍ ያለውን አባል አገሮች ይበልጥ ዴሞክሪያሳዊ አሠራር እንዲከተሉና የተቀላጠፈ ተግባር እንዲያከናውኑ የሚገፋፋ ነው። ከእንግዲህ፧ ሁሉም በአንድ ድምፅ ካልተስማማ ስለማይባል፧ የኅብረቱ ውሳኔዎች በቀላሉ ተፈጻሚነት ያገኛሉ። የአውሮፓው ኮሚሽንና የፓርላማው አባላት ቁጥርም እንዲቀነስ ይደረጋል።
ቀደም ሲል እንዳቀደው ሳይሆን፧ ኢጣልያ አንድ መቀመጫ ይቀነስባታል። ኢጣልያ ላቅ ያለ የህዝብ ቁጥር እንዳላቸው እንደ ፈረንሳይና ብሪታንያ ነው በአውሮፓው ፓርላማ በዛ ያሉ እንደራሴዎች እንዲወከሉ ያደረገች።
ፖላንድ በበኩሏ፧ የራሷን አቋም በማክረር፧ በኢዮኒና፧ ግሪክ የጸደቀ አንድ አንቀጽ፧ በአንዳንድ ልዩ ጉዳዮች፧ ኅዳጣን የአውሮፓው ኅብረት አባላት፧ የብዙኀኑን ውሳኔ እንዲዘገይ ሊያደርጉ የሚችሉበትን ሁኔታ አሁንም በተሃድሶው ለውጥ በውትወታ እንዲካተት ለማድረግ በቅታለች። ያም ሆኖ፧ የመንግሥታቱ ጉባዔ ይህ አንቀጽ ሊሻር የሚችለት ጠባብ በርም ቢሆን ክፍት ሆኖ እንዲቆይ ሳይስማማ አልቀረም።
ሐያስያን እንዳሉት ከሆነ፧ እያንዳንዱ አባል ፍላጎቱ ተቀባይነት የሚያገኝበትን መንገድ እየፈለገ ነው።
የአውሮፓው ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ሆሴ ማኑኤል ባሮሶም በበኩላቸው፧
«እርግጥ ነው፧ በአጠቃላይ በብዙኀን ድምፅ ውሳኔ ላይ ለመድረስ፧ የተሃድሶ ለውጥ ማድረግ በሚያስችል ውል ላይ ስምምነት የተደረሰው፧ አንዳንድ አገሮች፧ የቆየ አቋማቸውን በማላላታቸው መሆኑን ስናስብ ቅሬታ ይሰማናል። ይሁንና ይህን አቋማቸውን ማክበር ግዴታችን ነው። ለአንድ ወይም ሁለት አገሮች ሲባል የተለየ ሁኔታ ሊኖር ቢችልም፧ አሁን በብዙኀን ድምፅ መሥራት የሚቻልበትን መፍትኄ ነው አጥብቀን በመሻት ላይ ነን። በጥቂቶች ተቃውሞ ሳቢያ ስምምነት ማጣት አያስፈልግንም።«
የፖርቱጋል ው. ጉ ሚ. Luis Amado የአውእሮፓው ኅብረት ዜጎች እስካሁን ስምምነቱ መጓተቱ እንዳሳዘናቸው በመጥቀስ
«ህዝቡና ፖለቲከኞች፧ ይህ ረዥም ጊዜ የወሰደ የህገ-መንግሥት ድርድር አሳዝኗቸዋል። አሁን ማትኮር ያለብን፧ አውሮፓውያን በገጠሟቸው ተጨባጭ ችግሮች ላይ ነው።«