1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ህብረት የልማት መርህ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 21 2006

የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ምርጫ ጥቂት ሳምንታት በቀረቡት በአሁኑ ጊዜ በየሃገሩ የምርጫ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ነው ። በነዚህ የምርጫ ዘመቻዎችም የህብረቱ የልማት ፖለቲካ መርህ እምብዛም ትኩረት አለማግኘቱ እየተተቸ ነው ።

https://p.dw.com/p/1BqzG
ምስል picture-alliance/dpa

የአውሮፓ ህብረት የህዝብ እንደራሴዎች ምርጫ በ28 ቱ የህብረቱ አባል ሃገራት ከግንቦት እስከ ግንቦት 2006 ዓም ይካሄዳል ።የአሁኑ ምርጫ የአባል ሃገራት ዜጎች እንደራሴዎችቻቸውን በቀጥታ መምረጥ ከጀመሩበት እጎአ ከ1979 ወዲህ የሚካሄድ 8 ተኛው ምርጫ መሆኑ ነው ።በየአምስት ዓመት በሚካሄደው በዚህ ምርጫ የሚካፈሉ እጩዎች የምርጫ ዘመቻዎችን በማካሄድ ላይ ናቸው ። ይሁንና በነዚህ የምርጫ ዘመቻዎች የህብረቱ የልማት መርህ ያን ያህል ትኩረት አለማግኘቱ እያነጋገገረ ነው ።የአውሮፓ ህብረት ከዓለማችን ከፍተኛ የልማት እርዳታ ለጋሾች አንዱ ነው ።ሆኖም ይህ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ለህብረቱ ምክርቤት አባልነት የሚወዳደሩ እጩዎች ሲያነሱት እንዳልተሰማ ከዚያ ይልቅ የህብረቱ ኤኮኖሚያዊ ጥቅሞች የምርጫ ዘመቻውን ትኩረት እንደሳቡት የዶቼቬለዋ ሚሪያም ጌርከ ዘግባለች ።ዩሮን ከውድቀት መታደግ የባንኮች ህብረት ቢሮክራሲን እንዲቀነስ እንዲሁም የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ተጨማሪ ሥልጣን እንዲያገኝ የሚሉት እዚህ ጀርመን ውስጥ በሚካሄዱ የምርጫ ዘመቻዎች ልዩ ትኩረት የተሰጣቸውጉዳዮች ናቸው ።

Symbolbild Entwicklungshilfe
ምስል Imago

ለአውሮፓ ህብ,ረት ፓርላማ የሚወዳደሩት ልዩ ልዩ ፓርቲዎች እጩዎቹ የአውሮፓ ህብረት ዜጎች ተወካዮች እንደመሆናቸው በአፍሪቃ ድህነትን ለማስወገድ መወሰድ ስላለበት እርምጃ ፣ በእስያ የኤኮኖሚ ልማት እንዲስፋፋ ስለማበረታታት ፣ወይም ደግሞ በላቲን አሜሪካ ሃገራት ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት እንዲጠናከር የሚሉትን ጉዳዮች ባያነሱ ላይገርም ይችላል ። በአውሮፓ ፓርላማ የሶሻል ዲሞክራቶች ፓርቲ ተወካይ ና በፓርላማው የልማት ኮሚቴ አባልኖርበርት ኖይዘር ምክንያቱን ይገልፃሉ ።

«አሳዛኙ ነገር የልማትፖለቲካ መርህ በምርጫ ውሳኔ ላይ የሚኖረው ሚና በ2ተኛ ደረጃ የሚታይ ነው ።»

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አውሮፓ ከአፍሪቃ ጋር በትብብር ባካሄዳቸው የልማት ሥራዎች ብዙ ውጤቶችን ተመዝግበዋል ። ህብረቱ በአምዓቱ የልማት ግቦች ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ አመርቂ ፤ሊባሉ የሚችሉ ውጤቶች ተገኝተዋል ። ለምሳሌ በኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታዎች የአውሮፓ ህብረት 200 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 276.3 ሚሊዪን ዶላር ሰጥቷል ።በዚህም ራቅ ባሉ መንደሮች የሚኖሩ ሰዎች ፈጣንና አስተማማኝ በሆነ መንገድ ምርቶቻቸውን ለገበያ ማቅረብ ከመቻሉም በላይ በገጠር የሚያታየው ድህነት እንዲቀንስ አስተዋጽኦ አድርጓል ።የአውሮፓ ህብረት የልማት እርዳታ ዓላማ ከሰብዓዊና ኤኮኖሚያዊ ልማት ጋር በሃገራቱ መልካም አስተዳደርን ማበረታት ነው ። ከዚሁ ጋርም ረሃብና ድህነትን ለመዋጋት በሚደረግ ጥረት ውስጥ የበኩሉን ድርሻ ማበርከት የተፈጥሮ ሃብቶችን በዘላቂነት መጠቀምን ማበረታታትንም ያካትታል ። የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እንደሚለው በአውሮፓ ህብረት የልማት ትብብር ሥራዎች ውስጥ ፍልሰትን

Afrika Bauer Symbolbild German food partnership
ምስል Andreas Wolf/Fotolia

ለማስቆም የሚደረጉ ጥረቶች አልተካተቱም ።

ሆኖም ከአውሮፓ በስተደቡብ በሚገኙ ሃገራት በልማትም ሆነ ድህነትን ለመቀነስ በሚከናወኑ ተግባራት መሳተፍ የአውሮፓ ህብረት ፍላጎት ነው ። የአንድ ሃገር ልማት ከተሳካ ደግሞ ሰዎች ሃገራቸውን ለቀው እንዳይሄዱ እገዛ ያደርጋል ።ይሁንና በሃገራቸው ተስፋቸው የተሟጠጠ በርካታ አፍሪቃውያን ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በሰዎች በተጨናነቁ ጀልባዎች በሜዴትራንያን ባህር አድርገው ወደ ኢጣልያ ስፓኝና ግሪክ መጉረፋቸው ቀጥሏል ።

ከዓለማችን የልማት ትብብር እርዳታዎች ከግማሽ በላይ የሚሆነው ከአውሮፓ ህብረት ና ከአባል ሃገራቱ ነው የሚሰጠው ። የእነዚህ እርዳታዎች ትኩረትም የአፍሪቃ የፓስፊክና የካሬብያን አዳጊ ሃገራት ያቀፈው የልማት ተባባሪ ሃገራት ቡድን ነው ።በአፍሪቃ ፓስፊክና ካሬብያን ሃገራት ትብብር ቡድን ውስጥ ከታቀፉት 79 ሃገራት አብዛኛዎቹ የቀድሞ የአውሮፓ ቅኝ ግዛቶች ናቸው ። እጎአ በ2009 ሥራ ላይ በዋውለው በተሻሻለው የአውሮፓ ህብረት ውል ህብረቱ ልማትን በተመለከተ የተጣጣመ የፖለቲካ መርህ ለመከተል ቃል ገብቷል ። በዚሁ መሠረት በውጭ ግንኙነት በግብርና ወይም ኤኮኖሚን በማስፋፋት ረገድ የሚተላለፉ የአውሮፓ የፖለቲካ መርህ ውሳኔዎች በህብረቱ የልማት ፖለቲካ መርህ ዓላማዎች ውስጥ ጣልቃ መግባት የለባቸውም ። ይሁንና እውነታው ግን ከዚህ በተቃራኒው ነው ይላሉ ክሪስታ ራንድዝዮ ፕላትዝ የጀርመን መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት

«በአንድ በኩል የአውሮፓ ህብረት ድህነትንና ረሃብን ለመዋጋት የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ይፈልጋል ።በሌላ በኩል ደግሞ ለነዚህ ሃገራት ምግብ በመሸጥ የልማት ጥረቱን ይፃረራሉ ። የአውሮፓ ህብረት በርካሽ የህብረቱ የእርሻ ውጤቶች የአፍሪቃን ገበያዎች ማጥለቅለቁ ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ ለሚገፉ ገበሬዎች ምን ይጠቅማል

Symbolbild Entwicklungshilfe Moderne Zahnarztpraxis im Senegal
ምስል picture-alliance/dpa

በዚህ ዓመት ብቻ የአውሮፓ ህብረት ወደ አፍሪቃ ለሚላኩ የእርሻ ምርቶች የውጭ ንግድ ለገበሬዎች የሰጠው ድጎማ 150 ሚሊዪን ዩሮ ነው ።ባለፈው ጥር የህብረቱ የእርሻና የገጠር ልማት ኮሚሽነር ዳስያን ቺዮሎስ ወደ አፍሪቃ ምርቶቻቸውን ለሚልኩ ገበሪዎች ይሰጥ የነበረው የውጭ ንግድ ማበረታቻ ድጎማ ሙሉ በሙሉ እንደሚቋረጥ አስታውቀዋል ። ይህ ከመቼ ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ግን ኮሚሽነሩ አልተናገሩም ። በዛም ሆነ በዚህ የዶሮ ስጋን የመሳሰሉ ምርቶችን ወደ አፍሪቃ ለሚልኩ የአውሮፓ ገበሬዎች ለአሥርት ዓመታት ያህል ሲሰጥ የቆየው ድጎማ የበርካታ አፍሪቃውያንን ገበሬዎችን ህይወት አበላሽቷል ።

በዚህን መሰሉ አሰራር ችግር የገጠመው የግብርናው ዘርፍ ብቻ አይደለም ። የአውሮፓ አሣ አጥማጆች መረቦቻቸውን በአፍሪቃ ውሃ ላይ በጣሉ ቁጥር አፍሪቃውያኑ አሣ አጥማጆች እንደሚጎዱ ራንድዝዮ ፕላትዝ ያስረዳሉ ።

«አሳ ማስገርን የተመለከተው ስምምነት ከአፍሪቃ የአሣ ሃብት ክምችት የአካባቢው ነዋሪ ሳይሆን የአውሮፓ ህብረት ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርግ ነው ።»

የአውሮፓ ህብረት በውሃ ክልሎቻቸው አሳ ማስገርን ለሚፈቅዱ ሃገራት ካሳ ይከፍላል ። ለምሳሌ ሴኔጋል ለዚህ ትብብርዋ በየዓመቱ ከአውሮፓ ህብረት 16 ሚሊዮን ዩሮ ታገኛለች ። ሞዛምቢክ ከ4 ሚሊዮን ዩሮ የሚበልጥ ገንዘብ ሞሪቴንያ ደግሞ 86 ሚሊዮን ዩሮ ይሰጣታል ። ሆኖም የዓለም የእንሰሳት ሃብት ድርጅት እንዳስታወቀው ከነዚህ ሃገራት ውሃ የሚሰገረው አሳ የገበያ ዋጋ ፣ ከሚሰጣቸው

Symbolbild Entwicklungshilfe Kinder holen Wasser in Kabul
ምስል picture-alliance/dpa

ማካካሻ እጅግ የሚልቅ ሆኖ ተገኝቷል ። ከዚህ ሌላ በነዚህ ሃገራት የባህር ዳርቻዎች አሳ የሚያሰግሩ ዜጎችን ህይወት ይበላሻል ። የአውሮፓ ህብረት አሳ አስጋሪ መርከቦች የሚፈልጉትን ያህል አሳ ከወሰዱ በኋላ ለአካባቢው አሳ አጥማጆች ምንም አሳ አይተርፍም ። ይህንና የአውሮፓ ህብረት በእንግሊዘኛው ምህፃር ACP በሚል ምህፃር ከሚታወቁት የአፍሪቃ የካሬብያንና የፓስፊክ ሃገራት ጋር የሚያካሂዳቸውን ሌሎችንም ድርድሮች የአውሮፓ ፓርላማ አባል ኖይዘርም ይተቻሉ ።

« በአሁኑ ጊዜ የአውሮፓ ህብረት የሚደራደርባቸው የንግድ ስምምነቶች አሰቸጋሪ ናቸው ። በዚህ ላይ ምክክሮችን ማካሄድ ይገባል ። እና የምንደራደርባቸው የፖለቲካ መርሆች በማደግ ላይ ካሉት ሃገራት ወገን ሲታይ ፍትሃዊ አይደለም ።»

Entwicklungshilfe Deutscher Entwicklungshelfer in Niger Afrika
ምስል picture-alliance / dpa/dpaweb

የአውሮፓ ህብረት ከACP አባል ሃገራት ጋር የሚያካሄዳቸው የትብብር ስምምነቶች ዓላማ በሃገራቱ ልማትን ማበረታታት ነው ። የእርዳታ ድርጅቶች እንደሚሉት ግን የሚሆነው በተቃራኒው ነው ። በነርሱ አስተያየት በአሁኑ ሁኔታ የኤኮኖሚ ትብብር ስምምነቶቹ የሚጠቅሙት አውሮፓውያን የውጭ ነጋዴዎችን ነው ። ስምምነቶቹ የአፍሪቃ ሃገራት ከአውሮፓ ለሚገቡ ምርቶች ገበያዎቻቸውን ክፍት እንዲያደርጉ ይጠይቃል ። እነዚህ ሃገራት አገልግሎት ሰጭ ዘርፎችን ከመንግሥት ቁጥጥር ነጻ በማድረግ የአውሮፓ ባለሃብቶችም የመጠጥ ውሃን በመሳሰሉ ዘርፎች እንዲሰማሩ ይፈቅዳሉ ። ይህ ደግሞ በአንዳንድ ሃገራት እንደታየው ብዙውን ጊዜ የውሃው ጥራት ሳይሻሻል የዋጋ ንረትን አስከትሏል ። በኖይዘር አስተያየት ከአውሮፓ ህብረት በኩል ከአፍሪቃ ሃገራት ጋር የሚጣጣም የፖለቲካ መርህ አለመኖር አንዱ የችግሩ ገፅታ ሲሆን ከአፍሪቃውያኑም በኩል የሚታዩ ድክመቶች አሉ ፤በተለይ ከአፍሪቃ ባለሥልጣናት በኩል ።

« ለዚህ አሉታዊ ምሳሌ ናይጀሪያ ናት ። ለነዳጅ ዘይት ክምችቷ ምስጋና ይግባውና ሃገሪቱ ሃብታም ናት ። ሆኖም እጅግ ከፈተኛ ገንዘብ ይባክናል ። ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ለእነርሱም ቅርበት ያላቸው ሰዎች ደግሞ እጅግ ባለፀጋ ናቸው ። ይህ ደግሞ ለመቀበል የሚያዳግት ነው ። የአውሮፓ ህብረት በነዳጅ ዘይቱ ሜዳ ላይ ተንሳፈው ገንዘቡን የሚያጋብሱትን ባለሥልጣናት መጋፈጥ አለበት ። »

ይህን መታገያው አንዱ መንገድ ውጤታማ የሆነ የግብር አሰባሰብ ስርዓት መዘር,ጋት ነው ። ከዚህ ሌላ የአውሮፓ ህብረት ከአፍሪቃ የሚሸሸው ገንዘብ እንዲቆም ለብዙዎች የገንዘብ መሸሸጊያ የሆኑትን ባንኮች መዝጋት አለበት ።

የዛሬው አውሮፓና ጀርመን ዝግጅታችን በዚሁ አብቅቷል ። አድማጮች ለአውሮፓና ጀርመን ዝግጅት ጥያቄ ጥቆማ ወይም አስተያየት ካላችሁ በSMS EMAIL ወይም በFACE BOOK ፃፉልን እናስተናግዳለን ።

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ