1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ህብረት የተገን ጠያቂዎች መርህና ተቃውሞው

ማክሰኞ፣ ግንቦት 11 2007

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው ተገን ጠያቂዎችን ለመታደግ ፣ለማስተናገድና ለመቆጣጠር ያወጣው አዲስ እቅድ እያነጋገረ ነው ። እቅዱ በአንድ በኩል በበጎነቱ ሲወደስ በሌላ በኩል ደግሞ ተግባራዊነቱ አጠራጣሪ መሆኑ እየተሰማ ነው ።

https://p.dw.com/p/1FSop
Italien Flüchtlinge werden aus dem Mittelmeer gerettet
ምስል picture alliance/dpa/A. Di Meo

የአውሮፓ ህብረት የተገን ጠያቂዎች መርህና ተቃውሞው

በጎርጎሮሳዊው 2014 በአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ጥገኝነት የጠየቁት ስደተኞች ቁጥር ከ600 ሺህ ይበልጣል። ከነዚህም አብዛኛዎቹ በረሃብና በጦርነት ምክንያት ከአፍሪቃና ከመካከለኛው ምስራቅ የመጡ ናቸው ። ባለፉት 4 ወራት ብቻ የሜዲቴራንያንን ባህር አቋርጠው አውሮፓ የገቡ ስደተኞች ቁጥር ደግሞ ወደ 51 ሺህ ይጠጋል ። እነዚህ በህይወት አውሮፓ የደረሱት ሲሆኑ የተሳፈሩባቸው ጀልባዎች ወይም መርከቦች በመስጠማቸው ካለፈው ጥር ወዲህ ብቻ 1800 ስደተኞች ፣ በጉዞ ላይ ህይወታቸው አልፏል ።በሜዲቴራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ የሚጎርፈው ና መንገድ ላይ የባህር ሲሳይ የሚሆነው ስደተኛ ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መሄድ የአውሮፓ ህብረት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ አስገድዷል ። ከጥቂት ሳምንታት በፊት የህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች ከዚያም ቀደም ሲል የሃገር ውስጥና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ለችግር አፋጣኝ መላ እንዲፈለግለት ባሳሰቡት መሠረት የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት መፍትሄ ያለውን አዲስ እቅድ አቅርቧል ። እቅዱ በጥቅሉ በባህር ጉዞ የሚደርስ የሰዎች እልቂትን መከላከል ፣ አውሮፓ የገቡትን ተገን ጠያቂዎችን መከፋፈልና ማስፈር እንዲሁም የስደተኞች መነሻ በሆኑ ሃገራት ተጨማሪ የስደተኞች መጠለያዎችን መክፈት እና በህገ ወጥ መንገድ ሰዎችን የሚያሸጋግሩት ግለሰቦች ላይ ዘመቻ መካሄዱን ያካትታል ። የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ባለፈው ረቡዕ እንዳስታወቀው አባል ሃገራት አውሮፓ የሚገኙ ተገን ጠያቂዎችን እንዲከፋፈሉ እና ተጨማሪ 20 ሺህ ስደተኞችንም እንዲቀበሉ አቅዷል ። አነዚህ የህብረቱ ኮሚሽን ያወጣቸው እቅዶች ለስደተኞች መብት በሚታገሉ ወገኖችና በግብረ ሰናይ ድርጅቶች በአመዛኙ ተወድሰዋል ። ሆኖም ተግባራዊነታቸው ና የታሰበላቸውን ዓላማ ማሳካታቸው ግን ማነጋገሩ አልቀረም ። በሜዲቴራንያን ባህር የሚጓዙ ስደተኞችን የሚረዳው አበሻ ኤጀንሲ የተባለው ድርጅት መሥራችና ሃላፊ አባ ሙሴ ዘርአይ እቅድ መልካም ቢሆንም በተለይ ተገን ጠያቂዎችን በኮታ የመከፋፈሉ ሃሳብ የሁሉንም አባል ሃገራት ድጋፍ አለማግኘቱ ተግባራዊነቱን አጠራጣሪ አስቸጋሪም ያደርገዋል ይላሉ ።
ተገን ጠያቂዎችን መከፋፈልን በግንባር ቀደምትነት የምትቃወመው ብሪታንያ ስደተኞችን በኮታ የመከፋፈል ሃሳብ ሰዎች ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው እንዲሰደዱ ከማበረታት ውጭ የሚፈይደው ነገር አይኖርም ባይ ናት ። ብሪታንያና ሌሎቹ ይህን እቅድ የተቃወሙ ሃገራት ከዚያ ይልቅ በህገ ወጥ መንገድ ሰዎችን የሚያሻግሩ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ማደኑና መከላከሉ ላይ ይበልጥ ይሰራ ነው የሚሉት ። በእቅዱ ውስጥ ከተካተቱት ሃሳቦች አንዱም በህገ ወጥ አሻጋሪዎችና የግንኙነት መረባቸው ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ ነው ።ይህ እርምጃም ህገ ወጥ አሻጋሪዎቹ ስደተኞችን አሳፍረው ወደ አውሮፓ የሚልኩባቸውን ጀልባዎች እንዲሁም ለዚሁ ተግባር የሚጠቀሙባቸውን ሌሎች መሣሪያዎች ማውደምን ያካትታል ። በዚሁ ጉዳይ ላይ ትናንት ብራሰልስ ውስጥ የመከሩት የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የውጭ ጉዳይና የመከላከያ ሚኒስትሮች እቅዱ ተግባራዊ እንዲሆን ተስማምተዋል ።አባ ሙሴ አሁንም ይህ እቅድ የታሰበለትን ዓላማ የሚያሳካ ከሆነ ጥሩ ነው ይላሉ። ሆኖም አተገባበሩ ላይ ብዙ ጥያቄዎችን ማንሳታቸው አልቀረም ።
ህብረቱ በሜዴቴራንያን ባህር በተደጋጋሚ የደረሰውን የስደተኞች እልቂት ለመከላከል የነፍስ አድን ተልዕኮውን ለማጠናከርም አስቧል ። ከዚህ ቀደም ስደተኞችን ሲታደግ በነበረው በኢጣልያው ማሬኖስትሩም የባህር ኃይል ተልዕኮ የተተካውን የአውሮፓ ህብረቱን የትሪቶንን በጀት ከፍ ለማድረግ ታቅዷል ።ይሁንና አባ ሙሴ ትሪቶን ማሬኖስትሩም ሊተካ አልቻለም ይላሉ ።
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ይፋ ካደረጋቸው እቅዶች አንዱ በሺህዎች የሚቆጠሩ የምዕራብ አፍሪቃ ስደተኞች ወደ ሊቢያ በሚገቡባቸው ኒጀር በሚገኙ ዋነኛ የመሸጋገሪያ ቦታዎች የመጠለያ ጣቢያዎች እንደሚከፈቱም አስታውቋል ። ከመካከላቸው ዋኘኛ የሚባለው በሰሜናዊቷ ከተማ በአጋዴዝ በሚቀጥለው ዓመት ታህሳስ አጋማሽ ላይ ይከፈታል ተብሎ የሚጠበቀው ማዕከል ነው ። በአውሮፓ ህብረት የገንዘብ እርዳታ መሰል የመጠለያ ጣቢያዎች የማቋቋሙ እቅድም አባ ሙሴ እንደሚሉት ብዙ መልስ የማያገኙ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ እቅድ ነው ።
በአባ ሙሴ አስተያየት የአውሮፓ ህብረት ችግሩን መፍታት የሚያስችለውን ቀላሉን መንገድ ትቶ ብዙ ወጪ የሚጠይቀውን መንገድ እየተከተለ ነው ። እርሳቸውን እንደሚሉት ቀላሉ መፍትሄ ህጋዊውን መንገድ ክፍት ማድረግ ብቻ ነው ።
ኂሩት መለሰ

EU Mogherini beim EU-Außen- und Verteidigungsministertreffen
ምስል Reuters/F. Lenoir
Mittelmeer Küstenwache Italien Flüchtlingsboot Flüchtlinge Rettung
ምስል Picture-alliance/epa/Italian Coast Guard

አርያም ተክሌ