1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ሕብረትና የኤ.ሲ.ፒ. የኤኮኖሚ ውል ድርድር

ረቡዕ፣ መስከረም 29 2000

የአውሮፓ ሕብረት በአሕጽሮት ACP በመባል ከሚታወቀው የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሲፊክ አካባቢ መንግሥታት ስብስብ ጋር አዲስ የኤኮኖሚ ሽርክና ውል ለማስፈን የሚያካሂደው ድርድር በተጣለለት የጊዜ ገደብ፤ እስከያዝነው 2007 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ስኬት ማግኘቱ አሁንም ገና እርግጠኛ አይደለም።

https://p.dw.com/p/E0ce
ምስል AP

ሆኖም ድርድሩን በጊዜው ለማከናወን ከአውሮፓ ኮሚሢዮን በኩል አንዳንድ የማግባባት ጥረት መደረጉ አልቀረም። ለምሳሌ ያህል ኮሚሢዮንኑ ድርድሩን ለማቅለል በአገልግሎት ሰጪው ዘርፍ አኳያ ያስቀመጠውን ቅድመ-ግዴታ ለማለዘብ ዝግጁ መሆኑን ባለፈው ሰኞ አመልክቷል። ሃሣቡ ድርድሩን ወደፊት ለማራመድ ይበጅ-አይበጅ ግን በወቅቱ እንዲህ ብሎ ለመናገር የሚያዳግት ነው።

ብራስልስ ታዳጊዎቹ አገሮች ለአውሮፓውያኑ አገልግሎት ሰጭ ዘርፍ ገበዮቻችውን እንዲከፍቱ ታደርግ የነበረውን የድርድር ግፊት በመቀነስ በምርት-ነክ ስምምነት ላይ ለማተኮር ዝግጁ መሆኗን ሰሞኑን ለአውሮፓ ፓርላማ ዓባላት የገለጹት የኮሚሢዮኑ የንግድ ባለሥልጣን ዴቪድ ኦ-ሣሊቫን ናቸው። ባለፈው ዓመት አጋማሽ ብራስልስ ላይ የተገናኙት የአውሮፓ ሕብረትና የ ACP ተጠሪዎች እስከ ዓመቱ መጨረሻ የነጻ ንግዱን ውል ለማስፈን የተጣለው የጊዜ ገደብ እየተቃረበ መሄዱን ምክንያት በማድረግ ድርድሩን ለማፋጠን መጣራችው አይዘነጋም። ሆኖም የአውሮፓው ኮሚሢዮን ግፊት ለዝቦ ለአስታራቂ መፍትሄ የሚያበቃ ዕርምጃ እስካሁን አልታየም፤ ጊዜውም እየጠበበ በመሄድ ላይ ነው።

እንደሚታወቀው 78 በአብዛኛው የቀድሞ የአውሮፓ ቅኝ ግዛቶች የነበሩ ሃገራትን የሚጠቀልለው የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሢፊክ ስብስብ የሁለት ወገን ገበያ ከፈታን ግድ የሚያደርገውን አዲስ የኤኮኖሚ ሽርክና ውል እንዲፈርም ኮሚሢዮኑ ግፊት ሲያደርግ ነው የቆየው። ከታዳጊው ዓለም ስብስብ በርከት ያሉት የድሃ ድሃ የሚባሉ ሃገራት በፊናቸው ውሉ እስካሁን ወደ አውሮፓ ገበያ ለመዝለቅ ተሰጥቷቸው የቆየውን ልዩ የንግድ አስተያየት ከንቱ የሚያደርግ ከሆነ ለመፈረም ዝግጁ አለመሆናቸውን በየጊዜው ማስገንዘባችው አልቀረም። እነዚሁ አውሮፓውያን መንግሥታት ለስጋታችን ተገቢውን ትክረት ሊሰጡ ይገባል ባዮች ናቸው።

የቦትሱዋና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞምፓቲ ሜራፌ ባለፈው ግንቦት ብራስልስ ላይ እንዳሉት የሚደረገው የንግድ ስምምነት የታዳጊዎቹን ሃገራት ተጨባጭ አቅም ያገናዘበ መሆን ይኖርበታል። አጠቃላዩ ዝንባሌ ይህ ሲሆን የአውሮፓ ኮሚሢዮን በበኩሉ ውሉ የታዳጊዎቹን አገሮች ልማት ለማፋጠን እንደሚረዳ ዕምነቱ ነው። ለምሳሌ የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ሃይደማሪ-ቪቾሬክ-ሶይል የኤኮኖሚው ሽርክና ውል የ ACP አገሮች ወደ አውሮፓ የሚያደርጉትን የውጭ ንግድ እንደሚያዳብርና አፍሪቃ ውስጥ የአካባቢ የኤኮኖሚ ትስስርን የሚያበረታታ እንደሚሆን ዕምነታቸውን ነው። ቪቾሬክ-ሶይል ከብራስልሱ ንግግር በኋላ ለጋዜጠኞች ሲያስረዱ ስምምነቱ ልማትን የሚያራምድ መሆኑን ማረጋገጡ የሁላችንም ሃላፊነት ነው ሲሉ ነበር የተናገሩት።


የአፍሪቃ፣ ካራይብና ፓሢፊክ ስብስብ ሊቀ-መንበር የሌሶቶው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሕላቢ ሴኮዋ በበኩላችው የሁለቱ ወገኖች ድርድር ምንም እንኳ ፈታኝ ቢሆንም አውሮፓውያኑ ለታዳጊዎቹ አገሮች ስጋት ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ብዙ መጣራቸውን ነው የሚናገሩት። ሁለቱ ወገኖች ድርድሩን በተጣለው የጊዜ ገደብ ያጠቃልላሉ ብለውም ያምናሉ። በዚህ አባባል እርግጥ ከታዳጊዎቹ ሃገራት ይልቅ የብራስልሱ ኮሚሢዮን ታላቅ ዕርካታ እንደሚሰማው አንድና ሁለት የለውም። ምክንያቱም ከተለያየ አቅጣጫ ተቃውሞና ጥርጣሬ ገጥሞት የቆየ መሆኑ ነው።

ከመንግሥታት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች የአውሮፓ ሕብረት ለማስፈን የሚፈልገው ውል ታዳጊዎቹ አገሮች በቀላሉ ሊቀበሉት የሚከብድ ነው፤ ድህነትን ለመታገልም አይበጅም ሲሉ ቆይተዋል። ውሉ ታዳጊዎቹ አገሮች ኤኮኖሚያቸውን ብዙ-ወጥ በማድረግ እንዲለሙ የሚረዳ ሆኖ የታሰበ ነው ይባል እንጂ በዓለም ንግድ ድርጅት ውሣኔ መሠረት ገበዮቻቸውን ለአውሮፓ ምርቶችና አልግሎቶች እንዲከፍቱ የሚያደርግ መሆኑ እነዚህን ወገኖች አልተዋጠላቸውም። በዓመቱ መጨረሻ ማክተም ያለበት እስካሁን ሲሰራበት የቆየው የኮቶኑ ውል ታዳጊዎቹ አገሮች ገበዮቻቸውን እንዲከፍቱ የሚጠይቅ አልነበረም።
በአንጻሩ የተወሰኑት ድሆች አገሮች በልዩ የንግድ አስተያየት ምርቶቻቸውን ለአውሮፓ ገበዮች እንዲያቀርቡ ተፈቅዶላቸው ቆይቷል። ብዙዎቹን እነዚህን አገሮች ስጋት ላይ የጣለውም ይሄው ልዩ የንግድ አስተያየት የመቅረቱ ሃሣብ ነው። የቆየው ውል የሚያበቃበት የዓመቱ መጨረሻ እየተቃረበ መሄድ በያዘበት በአሁኑ ወቅት የአውሮፓ ሕብረት ከስኳርና ከሩዝ በስተቀር በመላው የ ACP ምርቶች ላይ ጥሎ ያቆየውን ኮታና ቀረጥ ጨርሶ እንደሚያስወግድ ቃል በመግባት ድርድሩን ለማነቃቃት ሞክሯል። ሃሣቡ በአብዛኛው ተቀባይነት ቢያገኝም የስኳር ምርት ተለይቶ መቀመጡ ይሄው ዋነኛ የውጭ ንግድ የገቢ ምንጫቸው የሆኑ አገሮችን ግን ማስከፋቱ አልቀረም።

ውሉ ለታዳጊዎቹ አገሮች ልማት ከመበጀቱ ይልቅ የእስካሁኑን ስምምነት ሕገ-ወጥ ያደረገውን የዓለም ንግድ ድርጅትን የጊዜ ገደብ ለማክበር ተብሎ ከተፈረመ ከመንግሥት ነጻ የሆኑት ድርጅቶች እንደሚሉት ፈሩን የሣተ ነው የሚሆነው። ታዳጊዎቹ አገሮች በተለይ ለአውሮፓ የአልግሎት ዘርፍና የመዋዕለ-ነዋይ ኩባንያዎች ገበዮቻችውን በመክፈታቸው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ድሃ ሕዝባቸው የኑሮ መሠረቱን ሊያጣ ይችላል። እ.ጎ.አ. ከ 1975 ዓ.ም. የሎሜ ውል ጀምሮ የነበረው ለታዳጊ አገሮች የአውሮፓን ገበዮች ከፍቶ የቆየው ልዩ የንግድ አስተያየት በአንድ መንገድ ቀጣይነት ካላገኘ ስጋቱ፤ ችግሩ በቀላሉ ወደጎን መገፋቱ ቢቀር በወቅቱ ጥቂትም ቢሆን የሚያጠራጥር ነው።
ስለዚህምም የተለያዩ አማራጮችን አጣምሮ መመልከቱ የሚጠቅም ጉዳይ ይሆናል። በአውሮፓ ፓርላማ አመለካከት በጉዳዩ ፈታ ያለ አቋም ለመያዝ የሚያበቃ ሁኔታ አሁንም አለ። ስለዚህም ድርድሩ እስከ ዓመቱ መጨረሻ በተሟላ ሁኔታ ባይጠናቀቅ ምን እንደሚያደረግ ከአሁኑ ማጤኑ የሚከፋ አይሆንም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ድርድሩ ለ ACP ሃገራት ወደ አውሮፓ ገበዮች የመዝለቅ አስተማማኝ ሁኔታ ኖሮ መጠናቀቁ የግድ አስፈላጊ ነው። እርግጥ በዚህ ረገድ እስካሁን ብዙም ጭብጥ ዕርምጃ ታይቷል ለማለት አይቻልም። ስምምነቱ እንደታሰበው በዓመቱ መጨረሻ ዕውን ይሆናል ብሎ መጠበቁን አዳጋች የሚያደርገውም ይሄው ሃቅ ነው።

የሆነው ሆኖ የአውሮፓ ሕብረት ታዳጊዎቹን አገሮች ለማግባባት ወይም ስጋታቸውን ለማለዘብ አንዳንድ ሃሣቦችን ማፍለቁ አይቀርም። የጀርመኗ የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ሃይደማሪ-ቪቾሬክ-ሶይል ለምሳሌ የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሢፊክ ስብስብ አገሮች በተወሰኑ ምርቶች ረገድ የነጻውን ንግድ መርሃ-ግብር ለማስፈን እስከ 25 ዓመት የሚዘልቅ መሸጋገሪያ ጊዜ እንደሚኖራችው ተናግረዋል። ሆኖም ከመንግሥት ነጻ የሆኑት ድርጅቶች በፊናቸው ታዳጊ አገሮች በተቻኮለ ሁኔታ ለአውሮፓ ምርቶች ገበዮቻቸውን በመክፈት ገበሬዎቻቸውንና ጨቅላ ኢንዱስትሪያቸውን እንዳይጎዱ ነው የሚያስጠነቅቁት።

ከአውሮፓው ኮሚሢዮን በኩል የታዳጊዎቹን አገሮች ስጋት ለማለዘብ እስካሁን የተባለው ሁሉ ተብሎ እንግዲህ ውሉ በጊዜው መፈረሙ ገና ያልለየለት ጉዳይ መሆኑ ነው። የታሰበው ካልተሣካ ከአውሮፓ ፓርላማ አኳያ እንደሚጠቀሰው ምናልባት መሸጋገሪያ ጊዜ ሊያስፈልግም ይችል ይሆናል። ይህ ሁኔታ ከተፈጠረ ደግሞ አዲስ ውል እስኪፈረም ድረስ የታዳጊዎቹ አገሮች ምርት በልዩ የንግድ አስተያየት ወደ አውሮፓ ገበዮች መዝለቅ መቀጠሉን ለተወሰነ ጊዜ ማራዘም አስፈላጊ ነው የሚሆነው። ማለት ለሽግግሩ ጊዜ!

አርባ ከሚሆኑት ልዩ የንግድ አስተያየት ሲደረግላቸው ከቆዩት የ ACP ሃገራት አብዛኞቹ የሚገኙት አፍሪቃ ውስጥ ነው። የአፍሪቃ ድህነትና የልማት ዕጣ ደግሞ በዚህ በጀርመን በቅርቡ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ ቀደምት መንግሥታት የቡድን 8 መሪዎች ጉባዔ መነጋገሪያ ጉዳይ ነበር። ጀርመን ያስተናገደችው የቡድን 8 ጉባዔ ከዓለም ኤኮኖሚ ሁኔታና ከተፈጥሮ ጥበቃ ቀጥሎ የአፍሪቃን ልማት ዓቢይ ርዕሱ ሲያደርግ አፍሪቃ ከድህነት አዙሪት እንድትወጣ መደረግ ያለበትና የሚገባው ሁሉ በተለያየ ደረጃ ተደርድሯል። እርግጥ ፍሬ መስጠቱ ቀስ በቀስ በተግባር መታየት የሚኖርበት ጉዳይ ነው።

በሌላ በኩል የበለጸጉት መንግሥታት መሪዎች ባለፉት ዓመታት በየጊዜው አፍሪቃን መነጋገሪያችው ቢያደርጉም በተለይ ከሁለት ዓመታት በፊት በስኮትላንድ-ግሌንኢግልስ ተሰብስበው ያደረጉት ውሣኔ ከዚያ ቀደም ያልታየ ተሥፋ የተጣለበት ነበር። መንግሥታቱ ለተወሰኑ ድሆች ለተባሉ አገሮች ዕዳ ሲሰርዙ የልማት ዕርዳታቸውን እስከፊታችን 2010 በዕጥፍ ለማሳደግ መስማማታቸውም አይዘነጋም። ግን ይህን የኋላኛውን ቃል በጊዜው ገቢር ማድረግ መቻላቸው በወቅቱ ሲበዛ ያጠራጥራል። የእስካሁኑ ሂደትና ልምድ እንደሚያሣየው ከሆነ ታዳጊዎቹን አገሮች በተለይም አፍሪቃን ለመፈወስ ጭብጥ ነገር ዕውን ማድረጋቸውን ማመኑ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የሚያዳግት ነው።

ለዚህ ጥርጣሬ ምክንያት የሚሆነው መንግሥታትና ለጋሾች ለአፍሪቃ ያቀረቡት ዕርዳታ በነበረበት መጠን ተወስኖ መቅረቱ ነው። በስኮትላንዱ ጉባዔ በተገባው ቃል መሠረት ከተባለው በብዙ መቶ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ወደ አፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የዘለቀው ጥቂቱ ብቻ ነው። የክፍለ-ዓለሚቱ አገሮች “የአፍሪቃ ዓመት” በተባለው በ 2005 ያገኙት ዕርዳታ 106 ቢሊዮን ዶላር ያህል ይሆን ነበር። ታዲያ ይሄው በተከታዩ ዓመት በሶሥት ቢሊዮን ሲያቆለቁል በአጠቃላይ ለዕርሻ ልማትና ለገጠር ልማት የሚቀርበው ዕርዳታ ባለፉት ሁለት ዓመታት እየቀነሰ ነው መጥቷል።
ለዚያውም 55 በመቶው ዕርዳታ የሄደው ምዕራባውያኑ መንግሥታት ከራስ ጥቅም አንጻር በተለየ ዓይን ወደሚያይዋቸው ናይጄሪያንና ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎን ወደመሳሰሉት አገሮች ነው። የአፍሪቃን ክፍለ-ዓለም የውስጥ ንግድ ብቃት ማዳበሩና በለጋሾች ላይ ያለውን ጥገኝነት መቀነሱ ድህነትን ለመታገል፤ ከችግሩ መላቀቅ የሚቻልበትን ስልታዊ ዘዴ ለማመቻቸትም ወሣኝ ጉዳይ ነው የሚሆነው። ዕርዳታ ብቻውን አፍሪቃን ከድህነት ማላቀቅ መቻሉ ብዙ ያጠያይቃል።

ለማጠቃለል ያህል የአውሮፓ ሕብረት ከ ACP ሃገራት ጋር የንግድ ውል ለማስፈን በሚያደርገው ጥረት ከተጣለው የጊዜ ገደብ ባሻገር ቢመለከት የሚበጅ ነው የሚመስለው። አሁን ድርድሩ ከሚገኝበት ሁኔታ አንጻር በቀሩት ጥቂት ሣምንታት ውስጥ የድርድሩን ምዕራፍ በስኬት መዝጋት መቻሉ ሊያምኑት የሚያዳግት ነው።