1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ሕብረትና የእሢያ መንግሥታት ጉባዔ

ሐሙስ፣ መስከረም 4 1999

በአሕጽሮት ASEM በመባል የሚታወቀው የኤውሮ-እሢያ መንግሥታት ስብስብ በየሁለት ዓመቱ የሚያካሂደውን መደበኛ የመሪዎች ጉባዔውን ባለፈው ሰኞ አጠናቋል።

https://p.dw.com/p/E0dW
በጉባዔው የተሳተፉት የጀርመንና የፖላንድ መሪዎች
በጉባዔው የተሳተፉት የጀርመንና የፖላንድ መሪዎችምስል picture-alliance/ dpa

ዘንድሮ ፊንላንድ ርዕሰ-ከተማ ሄልሢንኪ ላይ በተካሄደው ጉባዔ የ 25ቱ የአውሮፓ ሕብረትና የ 13 እሢያ መንግሥታት መሪዎች ሲሳተፉ የዓለም ኤኮኖሚን ማዕከላዊ ርዕሱ ያደረገው ስብሰባ የተጠናቀቀው ውሱን በሆነ ውጤት ነው። የአውሮፓ ሕብረትና የ 13 የእሢያ መንግሥታት የአሰም ስብሰባ ከተጀመረ አሥር ዓመታት አለፉት። የውይይቱ መድረክ በጊዜው የተፈጠረው በዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ትስስር ሳቢያ የተከሰተውን የዓለም የምጣኔ-ሐብት ሁኔታ ተከትሎ ነበር። ከዚያን ወዲህ የመንግሥታቱ መሪዎች በየሁለት ዓመቱ እየተሰበሰቡ ሲመክሩ ቆይተዋል። የዘንድሮው ጉባዔ የተካሄደው በወቅቱ የአውሮፓን ሕብረት ርዕስነት ይዛ በምትገኘው በፊንላንድ ርዕሰ-ከተማ በሄልሢንኪ ነበር።

የጉባዔው አጀንዳ በቅርቡ ከከሸፈው የዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ ድርድር ዙር እስከ አካባቢ ተፈጥሮ ይዞታ በርከት ያሉ ርዕሶችን የጠቀለለ ነበር። ጉባዔው እርግጥ መለስ ብሎም ያለፉትን አሠርተ-ዓመታት ዕርምጃውን አጢኗል። ከዚህ የተገኘው ግንዛቤም አንድ የአውሮፓ ዲፕሎማት እንዳሉት ያን ያህል የሚያረካ አይደለም። ለምን? የተወራውን ያህል ዕርምጃ አልታየም። የፊንላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲ ፋንሃነን በበኩላቸው ወደፊት በማተኮር የአውሮፓ ሕብረትና እሢያ ተመሳሳይ ፍላጎት፤ ግብም ስላላቸው የጋራ ዕርምጃ መውሰድ ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።

ሕብረቱና የእሢያው መንግሥታት አባቢ የኤኮኖሚ ሥርዓት ያላቸው እንደመሆኑ መጠን የነዳጅ ዘይትና የጋዝ ጥማቸው ከፍተኛ፤ ፍላጎታቸውም ተመሳሳይ ነው።
ፋንሃነን ከነዳጅ ዘይት ጥገኝነት ለመላቀቅ በጋራ ስልታዊ ዘዴ የማስፈኑን አስፈላጊነት አስገንዝበዋል። 38ቱ የአሰም ስብስብ አገሮች በዓለም ገበያ ላይ ከጠቅላላው ምርት ግማሹን የሚያቀርቡት ናቸው። እርግጥ እነዚህ የአውሮፓና የእሢያ መንግሥታት ተፎካካሪዎችም መሆናቸው የሚታወቅ ነው። በዚሁ የተነሣ በተለይ በቻይናና በቪየትናም የዋጋ ማጣጣልና ግልባጭ ምርትን የማቅረብ ዘይቤ አዘውትሮ ብርቱ የንግድ ውዝግብ መታየቱ አልቀረም። ሆኖም ለአውሮፓ ሕብረት የዓለም ንግድ ድርጅትን የዶሃ የንግድ ድርድር ዙር መልሶ ማነሳሳቱ ቀደምት ፍላጎት ነው።

ሁለቱ ወገን በፖለቲካ ይዞታቸውም የተለያዩ ናቸው። በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ አንድ ዓይነት የፖለቲካ ርዕዮት የሰፈነ ሲሆን የእሢያው በአንጻሩ ለየቅሉ ነው። የአውሮፓ ሕብረት በቻይናና በበርማ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ የሚኮንን ሲሆን ቤይጂንግ በበኩሏ ሕብረቱ ከ 17 ዓመታት በፊት የአገሪቱን መፍቀረ-ዴሞክራሲ እንቅስቃሴ በአጭር በመቅጨቷ የተነሣ የጫነባት የጦር መሣሪያ ማዕቀብ እንዲያነሣ ትፈልጋለች። ይህ የፖለቲካው ውዝግብ ደግሞ በኤኮኖሚው ግንኙነት ላይ በያጋጣሚው ችግር ማስከተሉ አልቀረም።

የሆነው ሆኖ የአሰም መንግሥታት በከፈቱት መድረክ መቀጠላቸው ጠቃሚና ትክክለኛም ነው። የማይጣጣሙ አቋሞችን በመቻቻል መንፈስና በበጎ የፖለቲካ ባህል በማለዘብ ወደፊት ማራመዱን ሁለቱም ይፈልጉታል። እንዲያውም ስብስቡን በአዳዲስ ዓባል ሃገራት የማስፋፋቱ ፍላጎት ዛሬ ከፍተኛ ነው። ቢዘገይ ከአንድ ዓመት ተኩል በኋላ፤ በ 2008 ቡልጋሪያና ሩሜኒያ እንደ አዳዲስ የአውሮፓው ሕብረት ዓባል መንግሥታት የአሰምን ስብስብ እንደሚቀላቀሉ ይጠበቃል።

የፊንላንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ፋንሃነን እንዲያውም ከዚያም ራመድ ብለው ነው የሚያስቡት። “እርግጥ ስለዚህ የዓባልነት ጉዳይ ከተወያየን አዳዲስ የእሢያ መንግሥታት መካተት በሚችሉበት ሁኔታም መነጋገር ይኖርብናል” ብለዋል። በርካታ የአውሮፓ ሕብረት ተጠሪዎች በተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ የምትገኘው ሕንድና ፓኪስታንም ዓባል መሆናቸውን ይሻሉ። ሶሥተኛው የኤውሮ-እሢያ መንግሥታት የመሪዎች ጉባዔ የተጠናቀቀው በአጠቃላይ ለተሻለ ትብብር፣ ለዓለም የኤኮኖሚ ትስስር ግሎባላይዜሺን ማሕበራዊ ገጽታ ይዞ መራመድና ለነጻ ንግድ መዳበር ለመሥራት የጋራ መግለጫ በማውጣት ነው።
የመንግሥታቱ መሪዎች በዓለም ንግድ ድርድር እንደገና ለመቀጠል እንደሚፈልጉም አመልክተዋል። በሌላ በኩል በተመሳሳይ ጊዜ ብራዚል ውስጥ በዚሁ ጉዳይ የተካሄደ እነዚሁ መንግሥታት የተሳተፉበት የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባዔ እንደገና መክሸፉ ግድ ሆኖበታል።