1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ምክር ቤት ምርጫ አንደምታ

ሰኞ፣ ግንቦት 19 2011

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አውሮፓውያን ትላንት በአህጉሩ ምክር ቤት የሚወክሏቸውን ፖለቲከኞች  ሲመርጡ ውለዋል። ባለፈው ሐሙስ የተጀመረው የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ምርጫ ጀርመን እና ፈረንሳይን ጨምሮ በ21 ሀገራት ተካሂዷል።

https://p.dw.com/p/3JF9W
Belgien Europawahl in Brüssel
ምስል picture-alliance/AP Photo/F. Seco

በትላንትናው የምርጫው የመጨረሻ ዕለት የአውሮፓ ህብረት ደጋፊዎች አብዛኛውን ድምጽ ቢያገኙም ቀደም ሲል የነበራቸውን የመቀመጫ ብዛት ግን አጥተዋል። በዚህ በጀርመን ይበልጥ በለስ የቀናው የአረንጓዴዎቹ ፓርቲ ነው። ቀኝ አክራሪው አማራጭ ለጀርመን ያቀደውን ያህል ባይሆንም በርካታ ድምጽ አግኝቷል። የጀርመኑ የክርስቲያን ዴሞክራቲክ ኅብረት እና ክርስቲያን ሶሻሊስት ኅብረት የፖለቲካ ፓርቲዎች ያገኙት ድምፅ 28 በመቶ ብቻ ነው። በጀርመን መንግሥት የመራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ፓርቲ ተጣማሪ የሆነው የሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ በምርጫው 15.3 በመቶ ድምፅ አግኝቷል። 

በአውሮፓ ምክር ቤት የመሐል ቀኝ እና የመሀል ግራ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጥምረት የነበራቸውን አብላጫ መቀመጫ በትናንትናው ምርጫ ተነጥቀዋል። ጠንካራ የአውሮፓ ሕብረትን የሚያቀነቅኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ቢኖራቸውም አዳዲስ አጣማሪ መፈለግ ይኖርባቸዋል።

Europawahl 2019 l Fridays for Future - grüne Europaflagge
ምስል Getty Images/AFP/I. Fassbender

ለዘብተኞች እና አረንጓዴዎቹ ድጋፍ ባገኙበት ምርጫ በብሪታኒያ፣ በጣሊያን እና በፈረንሳይ ቀኝ ዘመም የፖለቲካ ፓርቲዎች አሸናፊ ሆነዋል። የብሪታኒያዋ ጠቅላይ ምኒስትር ቴሬሳ ሜይ የምርጫው ውጤት አገራቸውን ከአውሮፓ ሕብረት የማስወጣትን አስፈላጊነት ይጠቁማል ብለዋል። የጠቅላይ ምኒትሯ ወግ አጥባቂ ፓርቲ በምርጫው ከ10 መቶ ድምፅ በታች አግኝቶ አምስተኛ ሆኗል።

በፈረንሳይ የፕሬዝዳንት ኤማኑዌል ማክሮ ተራማጅ ሪፐብሊክ ፓርቲ 22.41 በመቶ ድምጽ በማግኘት ሁለተኛ ሆኖ አጠናቋል። ቀኝ ዘመሙ የማሪን ለፔን የፖለቲካ ፓርቲ በ23.31 በመቶ ድምፅ አግኝቶ የበላይ ሆኗል። በአገራቸው ተቃውሞ የበረታባቸው ፕሬዝዳንት ማክሮ  አውሮፓን ለማዋሐድ የጀመሩት ጥረት ፈተና ውስጥ መውደቁን የትናንቱ የምርጫ ውጤት ጠቁሟል። 

Europawahlen Frankreich Marine Le Pen Rassemblement National
ምስል Reuters/C. Platiau

በጣልያን ስደተኛ ጠሉ የማቴዎ ሳልቪኒ የፖለቲካ ፓርቲ አሸናፊ ሆኗል። ሌጋ ኖርድ የተባለው የፖለቲካ ፓርቲ በምርጫው 34 በመቶ ድምፅ አግኝቷል። ውጤቱን አዎንታዊ ጉልበት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ምኒስትር ማቴዎ ሳልቪኒ ውጤቱ መላው አውሮፓ ወደ ቀኝ እያዘመመች መሆኑን ይጠቁማል ብለዋል።

በምስራቅ አውሮፓ ባሉ ሀገራት ድምጻቸውን ለመስጠት ቀደም ብለው የወጡ መራጮች ቁጥር ከአምስት አመት በፊት ከነበረው ጨምሮ ታይቷል። በሀንጋሪ፣ ሮማንያ፣ ስሎቫኪያ፣ ክሮሺያ እና ቆጵሮስ እስከ ቀኑ አጋማሽ ድረስ ከፍ ያሉ የመራጮች ቁጥሮች ተመዝግበዋል።

የአውሮፓ ምክር ቤት በአጠቃላይ 751 መቀመጫዎች አሉት። ውጤቱ ያሳሰባቸው የአውሮፓ ሕብረት እና በሕብረቱ ተደማጭ መቀመጫ የነበራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ከትናንት ጀምሮ ምክክር ላይ ናቸው።

የአውሮፓ ምክር ቤት ምርጫ ውጤትን በተመለከተ በጀርመን እና በአውሮፓ ምን ይመስል እንደነበር ከበርሊኑን ዘጋቢያችን ይልማ ኃይለሚካኤል እና ከብራስልሱ ወኪላችን ገበያው ንጉሴ ጋር ያደረግነውን ቃለ ምልልስ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ገበያው ንጉሴ/ይልማ ኃይለሚካኤል

ተስፋለም ወልደየስ