1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውቶሞቢሉ ኢንዱስትሪ ቀውስ

ሐሙስ፣ ግንቦት 27 2001

በዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ በምዕራቡ ዓለም ብርቱ የሕልውና ፈተናና ክስረት ላይ ከወደቀው የኢንዱስትሪ ክፍል አንዱ አውቶሞቢል አምራቹ ዘርፍ ነው።

https://p.dw.com/p/I2u8
ምስል picture alliance / dpa

በዓለም ላይ ታላቁ የሆነው የአሜሪካ አውቶሞቢል ኩባንያ ጀነራል ሞተርስ ሲንገዳገድ ቆይቶ አሁን በመጨረሻ መክሰሩ ተረጋግጧል። መዋቅራዊ ጥገና በማድረግ መልሶ እንዲነሳሳ ለማድረግ እየተጣረ ነው። በዚህ በአውሮፓና በተለይም በጀርመን በዚሁ ግዙፍ ኩባንያ ሥር የነበረው ኦፔልም በሌሎች መዋዕለ-ነዋይና በመንግሥት ድጎማ ሕልውናውን ጠብቆ መቆየት እንዲችል ውጣ-ውረድ ሲባል ነው የሰነበተው። ዓለምአቀፉ የተሽከርካሪ መገጣጠሚያ ዕቃ አቅራቢ ኩባንያ ማግናና ሩሢያ የጀነራል ሞተርስን የአውሮፓ ድርሻ በመግዛት ኦፔልን ከሞተበት ለማንሣት ተስማምተዋል። ዕርምጃው በየቦታው ያሉ የኦፔል ኩባንያ ሠራተኞች ለጊዜውም ቢሆን ዕፎይ እንዲሉ ነው ያደረገው። ሆኖም ዕርምጃው ዘላቂ መፍትሄ መስጠቱ፤ የሥራ ቦታ ዋስትናንም በሰፊው ማረጋገጥ መቻሉ ግን ገና አጠራጣሪ ነው።

አንዴ በዓለም ላይ ታላቁ አውቶሞቢል አምራች የነበረው ኩባንያ ጀነራል ሞተርስ ከተመሠረተ ከአንድ መቶ ዓመታት ሕልውናው በኋላ ባለፈው ሰኞ የኪሣራ ማመልከቻ ለፍርድቤት ማቅረቡ ግድ ሆኖበታል። የኩባንያው ዕዳ 27 ሚሊያርድ ዶላር ሲደርስ መልሶ እንዲጠገን 60 በመቶ በመንግሥት ዕጅ መግባት ይኖርበታል። ጀነራል ሞተርስ እ.ጎ.አ. ከ 1925 ዓ.ም. አንስቶ በፊናንሱ ገበያ ላይ ዋና ዋና ከሚባሉት ሰላሣ የአሜሪካ ኩባንዮች አንዱ ነበር። ካለፈው ሰኔ ወዲህ ግን ከ ዳው-ጆንስ ዝርዝር እስከመውጣት ደርሷል።

ጀነራል ሞተርስ ባለፈው ሰኞ ጉዳዩ ለሚመለከተው የኒውዮርክ ፍርድቤት የኪሣራ ማመልከቻውን ሲያቀርብ ኩባንያው የካፒታል ባለድርሻዎችን ቢቀር በተወሰነ ደረጃ ለማካካስ ግዙፍ የሆነ መዋቅራዊ ለውጥ ማድረግ ይኖርበታል። ባለፉት ቀናት ከወዲሁ አንዳንድ ዕርምጃ መደረጉና አስታራቂ መፍትሄ መገኘቱም አልቀረም። ከኩባንያው ባለድርሻዎች ከግማሽ የሚበልጡት የይገባኛል ጥያቄያቸውን በተወሰነ ደረጃ በመቀነስ በአንጻሩ በአዲሱ ኩባንያ አሥር በመቶ ድርጃ እንዲይዙና ወደፊት ይሄው ድርሻ ወደ 15 በመቶ ከፍ እንዲል ዋስትና እንዲኖራቸው ከሚያደርግ ስምምነት ከወዲሁ ተደርሷል። ከዚሁ በተጨማሪ ኩባንያው ከአሜሪካ የአውቶሞቢል ሠራተኞች የሙያ ማሕበር ጋር በያመቱ 1,3 ሚሊያርድ ዶላር መቆጠብ የሚያስችል አዲስ የደሞዝ ክፍያ ውል አድርጓል።

ይሁን እንጂ ጀነራል ሞተርስ ያለ አሜሪካ መንግሥት ድጋፍ ከወደቀበት ሊነሣ አይችልም። የአሜሪካ መንግሥት ለኩባንያው እስካሁን ሃያ ሚሊያርድ ዶላር ብድር ሲሰጥ በዚሁ ላይ ሰላሣ ሚሊያርድ ዶላር ለማከልም ያቅዳል። አብዛኛው የኩባንያው ድርሻ ከመንግሥት ዕጅ ይገባል ወይም ኩባንያው በመንግሥት ይዞታነት መቆየት ይኖርበታል ማለት ነው። ሆኖም ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ እንዳስገነዘቡት መንግሥታቸው በኩባንያው ሥራ በቀጥታ ጣልቃ ለመግባት አይፈልግም። መንግሥት የሚያምነው ጀነራል ሞተርስ በአምሥት ዓመት ጊዜ ውስጥ ዕዳውን ከፍሎ እንደሚጨርስ ነው። እርግጥ ከዚህ ከግብር ከፋዩ ሕዝብ ገንዘብ የተወሰነው ቀልጦ መቅረቱን የሚያምኑ ተጠራጣሪዎች ደግሞ መኖራቸው አልቀረም።

ከወዲሁ በግልጽ የሚታወቅ ነገር ቢኖር ጀነራል ሞተርስ የተወሰኑ ፋብሪካዎችን እንደሚዘጋና በሌሎች ሶሥት ይዞታዎቹ ደግሞ ለጊዜው የምርት ተግባሩን እንደሚያቆም ነው። ዝነኞቹን የአውቶሞቢል ዓይነቶች ሼቭሮሌትንና ካዲላክን የመሳሰሉ ስምንት ሞዴሎች ምርት የሚቆም ሲሆን የሚቀሩት አራት ብቻ ናቸው። በዚሁ አሜሪካ ውስጥ ብቻ ሃያ ሺህ ሰዎች ሥራቸውን ያጣሉ። ኩባንያው በአውሮፓ በኦፔል ላይ ያለው ድርሻም ወደ ሲሶ ያቆለቁላል። በኤኮኖሚው ቀውስ ሳቢያ የአሜሪካ የአውቶሞቢል ሽያጭ ከዓመት በፊት ከነበረው ሲነጻጸር 34 ከመቶ ያህል ቀንሷል። ይህም የሆነው በገበያው ሁኔታ ሳቢያ የተሽከርካሪ ዋጋ ባቆለቆለበት ወቅት ነው። በአጠቃላይ ለአውቶሞቢል ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሠራተኞች መጪው ጊዜ እጅግ ከባድ የሚሆን ነው የሚመስለው።

በአሜሪካ ጀነራል ሞተርስ በአዲስ መልክ አዲስ ጅማሮ ለማድረግ መዋቅራዊ ለውጥ ውስጥ ገብቶ ሳለ በዚህ በአውሮፓና በጀርመን በተመሳሳይ የሕልውና ፈተና ላይ የወደቀው ኦፔል አዳኝ ያገኘ እየመሰለ ነው። የኦፔል ሠራተኞች ኩባንያውን በመንግሥት የፊናንስ ዕርዳታ፤ እንዲሁም በአውስትሮ-ካናዳው የተሽከርካሪ ዕቃ አቅራቢ ኩባንያና በሩሢያ መዋዕለ ነዋይ ለማዳን ስምምነት በመደረሱ ጥቂትም ቢሆን ዕፎይ ማለታቸው አልቀረም።
“ከማግና ጋር ዓመታት የፈጀ ጥሩ ልምድ ነው ያለን። ኩባንያው ከአሠርተ-ዓመታት ወዲህ የመኪና ዕቃዎችን ሲያቀርብልን የቆየ ነው። ስምምነቱ እንግዲህ ጥሩ ነገር ነው”

እንደገና መዋዕለ-ነዋይ አቅራቢ ማግኘታችንና መልሰን የወደፊቱን በተሥፋ ለማየት መቻላችን ድንቅ ነገር ነው”

የጀርመኑ ኩባንያ 26 ሺህ ተቀጣሪዎች ሲኖሩት አብዛኞቹ በሥራ ተሰማርተው የሚገኙትም በዋነኛ ፋብሪካው በሩስልስሃይም፣ ቦሁም፣ ካይዘርስላውተርንና አይዘናህ በተሰኙት ከተሞች ውስጥ ነው። የሩስልስሃይም ሠራተኞች ብቻ ከ 15 ሺህ ይበልጣሉ። ጥንታዊውን አምራች በተለይ ለችግር የዳረገው የእናት ኩባንያው የጀነራል ሞተርስ ኪሣራ ላይ መውደቅ ነው።

ለማንኛውም ባለፈው ሰንበት በተደረገው ስምምነት የኦፔል ሕልውና ለጊዜውም ቢሆን መረጋገጡ አልቀረም። በስምምነቱ መሠረት የአሜሪካው ጀነራል ሞተርስ በኦፔል አውሮፓ ላይ የነበረውን ድርሻ የአውስትሮ-ካናዳው ዕቃ አቅራቢ ኩባንያ ማግና ከሩሢያው አውቶሞቢል አምራች ከጋስና በከፊል መንግሥታዊ ከሆነው የሩሢያ ባንክ ከስቤርባንክ ጋር ይይዛሉ። የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክልም በዚህ ስድሥት ሰዓታት በፈጀ ጠንካራ ድርድር በተገኘው ውጤት መርካታቸውን ነው የገለጹት።

“ኦፔል ለወደፊት የሚሆነውን ተሥፋ አግኝቷል። ይህ ለኩባንያው ሠራተኞች መልካም ዕድል ነው። የሚገባቸውም ነው ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም የችግሩ መንስዔ የአሜሪካው ኩባንያ የጀነራል ሞተርስ የአስተዳደር ጉድለት እንጂ ጥፋተኞቹ ሠራተኞቹ አይደሉም”

በስምምነቱ መሠረት የጀርመን መንግሥት ኦፔልን ከክስረት ለማዳን 2,1 ቢሊዮን ዶላር መሸጋገሪያ ገንዘብ የሚያቀርብ ሲሆን ዘላቂ ውል እስኪሰፍን ድረስም ኩባንያውን በበላይነት ይቆጣጠራል። በርሊን ከዚሁ በተጨማሪ ለማግናና ለሩሢያ ተባባሪዎቹ ከ 4,5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የኪሣራ ዋስትናም ትሰጣለች። ሩሢያ ደግሞ 35 ከመቶ የኩባንያውን ድርሻ እንደምትይዝ ነው የሚገመተው። በስምምነቱ የሩሢያ የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪ በቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ ይሆናል። ታዛቢዎች የሩሢያን ከዚህ ስምምነት ውስጥ መግባት ከአውቶሞቢል ኢንዱስትሪዋ ድክመት’ ጋር አያይዘው ነው የሚመለከቱት። ይህ ሁሉ ሲሆን እርግጥ ኦፔል በማዕከላዊ ቁጥጥር በሚገኘው በሩሢያ የመኪና ገበያ ላይ ስር መስደድ መቻሉ ገና አጠያያቂ ነው።
ኦፔል በሩሢያ ገበያ ከሚፈቀሩት የውጭ አውቶሞቢሎች መካከል በሰባተኛ ቦታ ላይ ነው የሚገኘው። ተወዳጅነቱን ለማሳደግ ምናልባት ዋጋ መቀነስ ሊኖርበት ይችላል። ከአሁኑ ዋጋውን በግማሽ እንዲቀንስ የሚመክሩ የመስኩ ባለሙያዎችም አልታጡም። ይህ ከሆነ ደግሞ የምርት ተግባሩን የሠራተኛው ደሞዝ ርካሽ ወሆነበት ወደ ሩሢያ ማሸጋሸግ ግድ ሊሆን ነው። ይሀን መሰሉ ዕርምጃ ደግሞ በአውሮፓ፤ በዚህ በጀርመንም የፋብሪካዎችን መዘጋትና ሥራ አጥነትን ነው የሚያስከትለው። እርግጥ ለጊዜው በዚህ አቅጣጫ የተባለ ጭብጥ ነገር የለም።
ሆኖም ግን አይደረግም አይባልም። ኦፔል በአዲስ ባለድርሻዎች በመያዙ በራሱ አሥር በመቶ ያህል ሠራተኞች መቀነሣቸው እንደማይቀር ከወዲሁ ተነግሯል። በአማካይ ጊዜ እንዲያውም በዚህ ተወስኖ ቢቀጥል የሠርቶ-አደሩን ጉዳት ገደብ አድርጎ ለመያዝ ይቻል ይሆናል። የኦፔል አስተዳደር ዓባል ዚግፍሪድ ቮልፍ በበኩላቸው ኩባንያውን በአሁኑ መጠኑ ይዘን ለማቆየት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን ባይ ናቸው።

“መላውን በጀርመን የሚገኙ ፋብሪካዎች፤ እንደገና ለማስረገጥ እወዳለሁ፤ እንዳሉ ለማቆየት እንፈልጋለን። በተቻለ መጠን ብዙ የሥራ ቦታዎችን ለማቆየት መፍትሄ እንደምናገኝ በጣሙን ነው ተሥፋ የምናደርገው”

ያም ሆነ ይህ መንግሥት በአስተዳደር ብልሽት ጭምር ከክስረት አፋፍ ላይ የሚወድቁ ኩባንዮችን ወይም ባንኮችን ለማዳን የግብር ከፋዩን ሕዝብ ገንዘብ እስከመቼ ነው የሚያፈሰው? ገደብ ሊኖር አይገባውም ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች አሁንም ማነጋገራቸውን እንደቀጠሉ ነው። በሌላ በኩል መንግሥት የኤኮኖሚ ይዞታዎችንና የሥራ ቦታዎችን ጠብቆ የማቆየት ግፊት አለበት። ችግሩ የግብሩ ገንዘብ መፍሰሱን በቀጠለ ቁጥር የዜጋውም ዕዳ እየጨመረ መሄዱ ላይ ነው። በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ ቀውስ የመታውን የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪ መልሶ ለማነቃቃት የሚደረገው ድጎማና መዋቅራዊ ለውጥ ምን ውጤት እንደሚያስከትል ጠብቆ መታዘቡ ግድ ይሆናል። መንግሥት ያፈሰሰው የግብር ገንዘብ ግን ሙሉ በሙሉ ተመልሶ ከካዝናው መግባቱ ከአሁኑ የማይታሰብ ነገር ነው።

MM/AA/DW/RTR