1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአየር ብክለት በአዉሮጳ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 15 2006

የአየር ብክለት በአዉሮጳ ለበርካቶች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት መሆኑ እየተነገረ ነዉ። ዲ ቬልት የተሰኘዉ የጀርመኑ ታዋቂ ጋዜጣ በጎርጎሪዮሳዊዉ 2010 ዓ,ም በአዉሮጳ ሃገራት ጎዳናዎች ላይ በተለያዩ አደጋዎች የ35 ሺ ሰዎች ህይወት መጥፋቱን ሲያመለክት፤

https://p.dw.com/p/1AgVQ
ምስል picture-alliance/chromorange

በተቃራኒዉ በአየር ብክለት መዘዝ በሚመጡ የአስም እና የተለያዩ የመተንፈሻ አካላትን የሚያዉኩ ህመሞችና ካንሰር 400 ሺዎች በአንድ ዓመት ማለቃቸዉን ይፋ አድርጓል። አጋጣሚዉ ለአካባቢ ተፈጥሮ ሊሰጥ የሚገባዉን ትኩረትና መደረግም የሚገባዉን ጥንቃቄ በማመልከቱም የአዉሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ከዚህ ቀደም በአባል ሃገራቱ ስምምነት መሠረት ሲከናወን የቆየዉን ለብክለት መንስኤ የሆኑ ነገሮችን ቅነሳ ማጠናከር እንደሚገባ አመልክቷል። ባለፉት አስርት ዓመታት ከየኃይል ማመንጫዉና ሌሎች ምንጮች ወደከባቢ አየር ይለቀቅ የነበረዉን በካይ ጋዝ መጠን በ50 በመቶ መቀነስ ተችሏል። እንዲያም ሆኖ በአሁኑ ወቅት የሚታየዉ ችግር ከተለያዩ ምንጮች የሚወጣዉ እጅግ ረቂቅ ብናኞችን ያዘለዉ ጢስ የሚያስከትለዉ የጤና እክል ባልተለመደ መልኩ በለጋ እድሜ መቀጠፍንም እያስከተለ መሆኑ ነዉ የታየዉ።

ለአካባቢ ተፈጥሮ የሚቆረቆረዉ በጀርመን የመጓጓዣ ስልቶች ተከታታይ ክለብ ተመራማሪ ሃይኮ ባልዝማየር በአዉሮጳ ሃገራት የተወሰደዉ የብክለት ቅነሳ ርምጃ ዉጤት ማሳየቱ ባይካድም ዛሬም ብክለት መኖሩ ለብዙዎች ግልጽ ያልሆነዉ ቆሻሻዉ ስለማይታይ እንደሆነ ያስረዳሉ፤

Abgase
ምስል KfW / Thomas Klewar

«አየሩ ተሻሽሏል ማለት የሚቻለዉ ቆሻሻዉን ማየት የማይቻልበት ሁኔታ መኖሩ ነዉ። ቀደም ባለዉ ጊዜ ዓመድ ከጭስ ማዉጫ ቧንቧ ሲወጣ በመጠኑም ሆነ ጎላ ብሎ ይታይ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን በዓመድ ወስጥ ያለዉን አቧራ ጠንቅቆ ለማወቅ አስቸጋሪ እየሆነ ነዉ፤ እጅግ ከመላዉ የተነሳ። የዚህ ዓመድ አደገኛነቱ እጅግ የላ,መ ከመሆኑ የተነሳ ሲተነፍሱት ጎሮሮ ላይ ተለጥፎ አይቀርም፤ ወደሳንባ አልፎ ከመግባት ባሻገር በሰዉነት ዉስጥ ከሚዘዋወረዉ ደም ጋር ይቀላቀላል። ይህ ነዉ እጅግ የላመዉ ዓመድ ብናኝ አደጋ።»

ከዚህ ቀደም ወደአየር ይቀላቀል የነበረዉ ሰልፈር ዳይኦክሳይድ የአሲድ ዝናብ እንዲወርድ ምክንያት እንደነበር አይዘነጋም። በአዉሮጳ ብቻ ሳይሆን አብዛኛዉ የዓለማችን ኗሪ ጤናማ ይዞታ ባለዉ የአካባቢ ተፈጥሮ አካባቢ እንደማይኖር ይፋ ሆኗል። የተበከለ ከባቢ አየር ለሰዎች ጤና ብቻ ሳይሆን ለሚበቅሉ አዝርዕትም ጠንቅ መሆኑ ነዉ የተገለጸዉ። የዓለም የጤና ድርጅት በከፋፈለዉ ደረጃ መሠረት በአዉሮጳ ከተሞች ከሚኖረዉ 90 በመቶዉ ለብክለቱ አስተዋፅኦ አድራጊነዉ። በአዉሮጳ ቁጥራቸዉ እየተበራከተ የመጣዉ እየተሻሻሉ ለገበየሚቀርቡት እና ከቤንዚን ይልቅ በናፍታ የሚዘወሩት አዉቶሞቢሎችና ይትሮጂን ዳይኦክሳይድን ወደከባቢ የአየር በመልቀቅ ለብክለቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋቾች ይገልጻሉበጀርመን የአካባቢ እና ተፈጥሮ ጥበቃ ሚኒስቴር የመጓጓዣ ዘርፍ ባለሙያ የሆኑት የንስ ሂልገንበርግ አዉሮጳ የከባቢ አየር ብክለትን ከመቀነስ የተደረገዉ ጥረት ዉጤት ማሳየቱ ባይካድም ከመጓጓዣ ስልቶች የሚወጡት አደገኛ ጋዞች ላይ ከፍተኛ ትኩረት መደረግ እንዳለበት ያሳስባሉ፤

«እስካሁን የኗሪዎቹን ጤና ለመጠበቅና አየሩን ንፁህ ለማድረግ የተወሰዱት እርምጃዎች በቂ አይደሉም። በእርግጥ የአየሩ ንፅህና ተሻሽሏል ግን በቂ አይደለም። ከምንም በላይ በመጓጓዣዉ ዘርፍ ሁለት ነገሮችን ማለትም ካርቦን ዳይኦክሳይድና ናይትሮጅን ኦክሳይድን ለመቀነስ አንድ ነገር መደረግ ይኖርበታል።»

Symbolbild Stau in Deutschland Berlin
ምስል picture-alliance/dpa

በአዉሮጳ የተለያዩ ከተሞ የሚገኙ ኗሪዎችም ለዚሁ ጥረት የየበኩላቸዉን አስተዋፅኦ ለማድረግ እንዲችሉ ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በሚጠቀሙ መጓጓዣዎች ከመጠቀም በተጨማሪ ብስክሌቶችን ቢያዘወትሩ እንደሚበጅም ይመክራሉ። ለአካባቢ ተፈጥሮ የሚቆረቆረዉ በጀርመን የመጓጓዣ ስልቶች ተከታታይ ክለብ ተመራማሪ የሆኑት ሃይኮ ባልዝማየር በየሃገራቱ ለብክለት ምክንያት የሚሆኑት ምንጮች እንደሚለያዩ ያመለክታሉ፤

«የብክለቱ ሁኔታ ከሀገር ሀገር ይለያያል። ለምሳሌ በዴንማርክ እጅግ አሳሳቢዉ ሳንክ በምድጃ የሚቀጣጠል እንጨት ነዉ። ጭስ መዉጫ ባለዉ ክፍት ወይም የተከደነ ምድጃ በጀርመን ካሉት ዐበይት ችግሮች አንዱ በዚህ ረገድ ማለት ነዉ የተሽከርካሪዎች ብዛት ነዉ።»

Deutschland Luftverschmutzung Kraftwerk in Hanau
ምስል AP

የአዉሮጳ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም እንደሚለዉ ባለፉት ዓመታት የተከናወነዉ የብክለት ቅነሳ ርምጃ ዉጤት አሳይቷል። ከባቢ አየሩን ከበከሉት አደገኛ ጋዞች የልቀት መጠንም የተወሰኑት በ15 በመቶ ቀንሶ ታይቷል። ሂልገንበርግ የሚሉት ግን በእርግጥ እዉነት ነዉ የበካይ ጋዞች ቅነሳዉ ጥረት በሁለም አባል ሃገራት ርብርብ ዉጤት አሳይቷል ሆኖም ግን አሁንም አየሩ ከብክለት ድኗል ማለት አይቻልም ነዉ። እሳቸዉ የሚሉት አየሩን የበከሉትን ጥቃቅን ብናኞች ማየት አለመቻላችን እንጂ እነዚሁ ብናኞች ወደሳንባ እየገቡ የሰዎችን የመተንፈሻ አካላት በማወቅ ለጤና እክል ብሎም ለህልፈተ ህይወት ማድረሳቸዉን የማይካድ ነዉ። የአየር ብክለት አዉሮጳ ዉስጥ ከፍተኛዉ የአካባቢ ተፈጥሮ ችግር መሆኑን በማመልከት የአዉሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ወደከባቢ አየር የሚገቡ በካይ ጋዞች ላይ ተጨማሪና ከፍተኛ ቁጥጥር እንዲደረግ ሃሳብ አቅርቧል። ሃይኮ ባልዝማየር ኅብረቱ አሁንም ተጨማሪ የብክለት ቅነሳ እንዲደረግ እየሠራ መሆኑን ያመለክታሉ፤

«የአዉሮጳ ኅብረት በአሁኑ ወቅት ብክለትን ለመቀነስ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እየሠራ ነዉ። ይህም ኅዳር ወር ላይ ይፋ ያደረገዉ እያንዳንዱ አባል ሀገር ሊጠብቀዉ የሚገባ የብከይ ጋዝ ልቀት መጠን ገደብን የሚያመለክት ሲሆን፤ በተለይ በስም ተለይተዉ የተጠቀሱ አደገኛ ጋዞችን የመቀነስ ርምጃ እንዲወስዱና የኅብረቱን የብክለት ቅነሳ እሴት እንዲጠብቁ ይታሰባል።»

ለብክለቱም ከፍተኛዉን ደረጃ የሚወስደዉ ለኃይል ምንጭነት ከሚዉለዉ ድንጋይ ከሰል የሚገኘዉ ካርቦን ዳይኦክሳይድ ነዉ። በታዳሽ የኃይል ምንጭ መጠቀሙ ባለሙያዎች እንደሚሉት የዓለማችን ሙቀት ከሁለት ዲግሪ እንዳይበልጥ ይረዳል። ለከባቢ አየር ንፅህና የሚሟገተዉ የመጓጓዛ ዘርፍ ክለብ ከጀርመን የአካባቢ እና ተፈጥሮ ጥበቃ ሚኒስቴር እና ከሌሎች የአዉሮጳ መሰል ድርጅቶች ጋ በጋራ አየሩ የንፅህና ደረጃ የሚሻሻልበትን ርምጃ ለመዉሰድ ኃላፊነት ተረክቧል። ለዚህ ሲሉም በግርድፍ ትርጉሙ «ንፁህ አየር» የተሰኘ ፕሮጀክት ቀርጸዉ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸዉ። በእነሱ እምነትም እስካሁን የአየር ብክለቱን ለመቀነስ የተወሰዱ ርምጃዎች በቂ አይደሉም የአዉሮጳ ኅብረት ጠንካራና የተሻሉ መመሪያዎችን ማጽደቅና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል። ያንስ ሂግለንበርግ ምንም እንኳን የአዉሮጳ ምክር ቤት ያወጣቸዉ መመሪያ ደንቦች ግሩም ናቸዉ ቢሉም አባል ሃገራቱ ለተግባራዊነቱ የወሰዷቸዉ ርምጃዎች በቂ አይደሉም ሲሉ ይወቅሳሉ፤

Bildergalerie Airlines Logo AeroMexico
ምስል picture-alliance/dpa

«በአዉሮጳዉ ኅብረት የወጣዉን ደንብ አባል ሃገራት ማክበር ይጠበቅባቸዋል። በተለይ ናይትሮጂን ዳይኦክሳይድን በተመለከተ አባል ሃገራቱ ገና ምንም የወሰዱት ርምጃ የለም።»

ፖላንድ ዉስጥ የድንጋይ ከሰል ኢንዱስትሪዉ፤ በዴንማርክ ቤት ለማሞቅ የሚነደዉ እንጨት፤ ጀርመን ዉስጥ ደግሞ ከየተሽከርካሪዉ የሚወጣዉ አደገኛ ጋዝ ከባቢ አየሩን ለመበከል ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለዉ የአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ ተሟጋቾች ይገልፃሉ። እንዲያም ሆኖ ከባቢ አየርን ከብክለት ለማፅዳት በምታደርገዉ ጥረት ጀርመን በአዎንታዊ ርምጃቸዉ ከሚጠቀሱ ሃገራት ግንባር ቀደሟ ናት። ሂልገንበርግ እንደሚሉትም በበርካታ የጀርመን ግዛቶች የአየር ብክለቱን ለመቀነስ ሲባል ትናንሽ አዉቶሞቢሎች ብቻ እንዲሽከረከሩ ተደንግጓል። ችግሩ ግን የተሽከርካሪዉ ቁጥር መብዛት፤ እንዲሁም ፋታ የሌለዉ የአየር በረራ የሚያስከትለዉ ብክለት ከራሷ አልፎ ለጎረበት ብሎም ለሌላዉ ዓለም የሚተርፍበት ሁኔታ መኖሩ ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ