የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በካቶቪትስ

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:36 ደቂቃ
04.12.2018

ተግባር የሚጠበቅበት COP 24

የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች ዓለም አቀፍ ተከታታይ ጉባኤ ትናንት በፖላንዷ ካቶቪትሰ ከተማ ተጀምሯል። ጉባኤው የአየር ንብረት ለውጥን አስመልክቶ ሃገራት ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ የተስማሙበት ውል ተግባራዊ የሚሆንበትን ደንብ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል።  ለሁለት ሳምንት በሚዘልቀው በዚህ ጉባኤ 200 የሚሆኑ ሃገራት ተወካዮች ይሳተፋሉ።

«ችግር ውስጥ ነን። ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ጥልቅ ችግር ውስጥ ገብተናል። የአየር ንብረት ለውጥ ከእኛ ይበልጥ ፈጥኖ እየሮጠ ነው። ሳይረፍድብን በፍጥነት ልንደርስበት ይገባል። ይህ ደግሞ ለበርካታ ሕዝቦች፣ አካባቢዎች፣ ሃገራትም ሳይቀር የሕይወት ወይ ሞት ጉዳይ ሆኗል።» ይህ የተናገሩት የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ ናቸው COP 24 በመባል የሚታወቀው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች ዓለም አቀፍ ዓመታዊ ጉባኤ በፖላንዷ ደቡባዊ ከተማ ካቶቪትሰ ሲከፈት ነው።

COP 24 በመባል የሚታወቀው የተመድ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ዓመታዊ ጉባኤ በፖላንድ ደቡባዊ ክፍለ ሀገር ውስጥ የምትገኘው ካቶቪትሰ ከተማ ትናንት ተጀምሯል። ይህን ጉባኤ ለየት የሚያደርገው ከሦስት ዓመታት በፊት ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ ሃገራት የገቡት የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት የመቀነስ እና አዳጊ ሃገራትን በታዳሽ ኃይል ምንጮች ተጠቃሚ የማድረግ ቃልን ያካተተ ውል ወደ ተግባር ያሸጋግራል የሚለው ተስፋ ነው።  

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ እውነትነቱን እያረጋገጠ የመጣው የዓለም የሙቀት መጠንን ለመቀነስ ሃገራት ማድረግ የሚገባቸውን ከማድረግ እጅግ መራቃቸውን  ጠቁመዋል። የተመድ ዘገባዎች እንዳመለከቱት በከባቢ አየር ውስጥ የተከባቸው የካርቦን ዳይኦክሳይድ መጠን በሦስት ሚሊዮን ዓመታት ውስጥ እጅግ ከፍተኛው ደረጃ ላይ ደርሷል። በዚህ መዘዝም በተለይ ያለፉት አራት ዓመታት በመላው ዓለም ታይቶ የማይታወቅ ሙቀት ተከስቷል። ባለፈው ወር ከ90 የሚበልጡ ገለልተኛ ሳይንቲስቶች ባካሄዱት ምርምር መሠረትም ከፍተኛ የሙቀት መጨመር የከፋ ጉዳት ሳይከተል በፊት በቀጣይ 12 ዓመታት ውስጥ የሰው ዘር በሙሉ የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት መቀነስ ይኖርበታል። ዋና ፀሐፊ አንቶዮ ጉተሬሽ በምድራችን እጅግ የከፋ የተፈጥሮ ቁጣዎችን ከተለያዩ አካባቢዎች እየተመለከትንም ምንም አልሰራንም፤ ፈጥነንም ያንን ሊቀለብሱ የሚችሉ ርምጃዎችን አልወሰድንም ሲሉም ወቅሰዋል።

«እጅግ መራቃችን ሲታሰብ በጣም ያማል። የበለጠ ተግባር እና ፍላጎት ያስፈልገናል። እናም ይህን የብክለት ክፍተት ፈጽመን መዝጋት ይኖርብናል።  አርክቲክ እና አንታርክቲክን ማዳን ካቃተን መቅለጡ ይቀጥላል። የባሕር ውስጥ ተክሎችም እየተቃጠሉ ይሞታሉ። ውቅያኖሶች ከፍታቸው ይጨምራል። በአየር ብክለት ብዙ ሕዝብ ይሞታል። የውኃ እጥረት የሰው ዘር ዋነኛ የችግር አካል ይሆን እና አደጋዎች የሚያደርሱት ጉዳት መጠን እጅግ ከፍ ይላል።»  

የዘንድሮው የአየር ንብረት ለውጥ ተከታታይ ዓለም አቀፍ ጉባኤ COP 24 አስተናጋጅ ፖላንድ ለኃይል ምንጫቸው በከፍተኛ መጠን የድንጋይ ከሰል ከሚጠቀሙት ሃገራት አንዷ ናት። የፖላንድ እና የድንጋይ ከሰል ትስስር አስርተ አስርት ዓመታትን የዘለቀ ነው። ቀዝቃዛው ጦርነት ካከተመ በኋላ ፖላንድ የኃይል ምንጭ መቶ በመቶ ይኸው ከሰል ሆነ። በቀደሙት ዓመታት የአካባቢ ተፈጥሮ ክብካቤ ጉዳይ ቦታ አልነበረውም። ውሎ አድሮ አሳሳቢነቱ ትኩረት መሳብ ሲጀምር ፖላንድም 20 በመቶ የሚሆን ኃይሏን ከታዳሽ የኃይል ምንጮች ማግኘት ጀመረች። አምና ጀርመን ቦን ከተማ ላይ ጉባኤው ሲካሄድ ለአካባቢ ተፈጥሮ ደህንነት የሚሟገቱ ወገኖች በርሊን በአብዛኛው ድንጋይ ከሰል ላይ የተደገፈው የኃይል አቅርቦቷን መላ እንድትፈልግለት ውትወታው ፀንቶባት ከርሟል፤ ዘንድሮም አላባራም። ባለተራዋ ፖላንድ ደግሞ አሁን ተመሳሳይ ጥሪ እየቀረበላት ነው። ፖላንድ የድንጋይ ከሰል የኃይል ምንጭ ዘርፏን ለመደጎም 2 ቢሊየን ዩሮ በየዓመቱ እንደምታወጣ ይፋ አድርጓል። ባለግዙፍ ኢንዱስትሪ ሃገራቱ የሙቀት አማቂ ጋዞች ቅነሳ ላይ መስማማታቸው አዎንታዊነቱ ባያጠያይቅም ተግባራዊ ለማድረግ የሚያሳዩት ጥረት ግን አሁንም እያነጋገረ ነው።

እንደብዙዎቹ ግምት ይህ የካቶቪትሰ ጉባኤ ሃገራት ከዚህ ቀደም ፓሪስ ፈረንሳይ ላይ ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን የሙቀት አማቂ ጋዞች መጠን የመቀነስ ብሎም በአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ ለጉዳት ለተዳረጉ ሃገራት በየዓመቱ ሊሰጡ ያቀዱት የ100 ቢሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ውሳኔ ነፍስ እንዲዘራ ያስችላል። ሆኖም ግን አዳጊ ሃገራት በታዳሽ የኃይል ምንጮች እንዲጠቀሙ የማድረግ ቃል ያካተተው ይህ የገንዘብ ድጋፍ እስካሁን ይህ ነው የሚባል የተጨበጠ ውል አልያዘም። ትናንት የወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱትም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው በኢንዱስትሪ ያደጉት እና በዚሁ ዘርፍ ፈጣን እድገት ላይ የሚገኙት የቡድን ሃያ አባል ሃገራት ከፍተኛ ልዑካን በዚህ ጉባኤ ላይ አልታዩም። ይህ ደግሞ የዓለምን የሙቀት መጠን ጨምሮ የተለያዩ የተፈጥሮ ቁጣዎች እንዲባባሱ በማድረግ የሚወገዙትን ሙቀት አማቂ ጋዞች ወደ ከባቢ አየር ባይልኩም በመዘዙ የተጎዱት ሃገራትን ቅሬታ ከፍ ማድረጉ ተነግሯል።

ከሰልን በኃይል ምንጭነት መጠቀም ይቁም የሚለው ተቃውሞ

የጉባኤው ተሳታፊዎች ከሆኑት መካከል የፖለቲካ መሪዎች በየሀገራቸው የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለውን ተፅዕኖ ለመግለፅ ሞክረዋል።  መሪዎቹ ሕዝባቸውን ወክለው ባደረጉት አጠር አጠር ያለ ንግግር ችግሩ ይቀረፍበታል ያሏቸውን ሃሳብ እና እቅዶችም ሰንዝረዋል። ተራራማ መልክአምድር ከሜዳ አዋሕዳ የያዘችው የኔፓል ፕሬዝደንት እንደፊጂ የመሰሉ ሃገራት ባለጠፉት ጥፋት በተፈጥሮ ቁጣ እየተቀጡ እንደሚገኙ ነው ያመለከቱት።የናይጀሪያው ፕሬዝደንደት ሙሃመዱ ቡሃሪ በበኩላቸው ለከባቢ አየር ብክለቱ የሚወቀሱት በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሃገራት ቃል የገቡት 100 ቢሊየን ዶላር በአየር ንብረት ለውጡ ለተጎዱ አዳጊ ሃገራት የሚቀርብበት መንገድ እንዲመቻች አሳስበዋል።

«የአየር ንብረት ለውጡን ለሚመለከቱ ተግባራዊ ርምጃዎች ከበለጸጉት ሃገራት አዳጊ ኤኮኖሚ ላላቸው ሃገራት የሚሰጠው የገንዘብ እና ፋይናንስ ጉዳይ ግልፅ ያሉ መለኪያዎች እንዲኖሩት ይደረጋል ብለን እናምናለን። ይህ ደግሞ በግልፅነት እና በሚጠበቁ ትንበያዎችን መሠረት በማድረግ መከናወን አለበት።»

የዓለም ባንክ የአየር ንብረት ለውጡ ለሚያጠቃቸው ድሀ ሃገራት የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ በእጥፍ እንደሚያሳድግ ትናንት ይፋ አድርጓል። ከባንኩ የሚገኘው 200 ቢሊየን ዶላር ነው።  ጉባኤው ከመጀመሩ ቀደም ብሎም የቡንድ ሃያ 19 አባል ሃገራት መሪዎች ፓሪስ ላይ የፈረሙትን ውል አክብረው እንደሚገፉበት ማመላከታቸው ለCOP 24 ተሳታፊዎች ተስፋ የፈነጠቀ አይነት መስሏል። በአፈንጋጭነት የቀጠሉት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራንም ብቻ ናቸው። በዚህ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ትናንት ንግግር ካደረጉት መካከል በተደጋጋሚ የሰደድ እሳት የምትጠቃው የካሊፎርኒያ የቀድሞ አገረ ገዢ አርኖልድ ሽቫርስኒገር ግን ዋሽንግተን ላይ በሚታየው ኋላ ቀር ባሉት አካሄድ ምክንያት አሜሪካ ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ውል ወጥታለች ማለት ስህተት ነው ባይ ናቸው።

«በየጊዜው  ስለአሜሪካ ስትናገሩ ዋሽንግተን ውስጥ ያለው አስተዳደራችን በመጠኑ ኋላቀር በመሆኑ ትክክል ናችሁ። ነገር ግን ከፓሪሱ ስምምነት አሜሪካ ወጥታለች ማለታችሁ ስህተት ነው። 70 በመቶ የሚሆነውን ብክለት የሚቆጣጠሩ ግዛቶች እና ከተሞችን የአካባቢ መንግሥታትን ታያላችሁ። በዚያም ላይ እጅግ አስደናቂ የሆኑ ሥራዎችን በአሜሪካ በግዛት እና ከተሞች ደረጃም መመልከት ትችላላችሁ። ስለዚህ ግዛቶች እና ከተሞች አሁንም በፓሪስ ስምምነት ውስጥ ናቸው።»

በዚህ ብቻ አላበቁም ዘ ተርምኔተር የተሰኘው ፊልም ተዋናይ እና ለአካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ በሚያደርጉት ያላሰለሰ ትግል ሦስት ጊዜ ሚስተር ዩኒቨርስ የተሰኘው ሽልማት አሸናፊ ሽቫርስኒገር፤ መንግሥታት የሕዝብን ደህንነት ለመከላከል ሠራዊት እንደሚያደራጁ ሁሉ በአየር ንብረት ለውጥ ከሚመጣው ጉዳትም ዜጎቻቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። የሀገራቸውን በፓሪሱ ስምምነት መፅናት አስመልክተውም ሌሎችን ባስፈገገ መልኩ እንዲህ አስረግጠው ተናግረዋል።

«ዩናይትድ ስቴትስ አሁንም በስምምነቱ ውስጥ ናት እናም እጅግ አስደማሚ ሥራዎችን መሥራትዋን ትቀጥላለች። እርግጥ ነው እብድ መሪ ዋሽንግተን ውስጥ አለን፤ እሱ በዚህ ውስጥ የለም፤ ወጥቷል። ሆኖም ግን አሜሪካ ከዋሽንግተን ወይም ከአንድ መሪ በላይ መሆኗን አስታውሱ።»  

አፍሪቃ ለአየር ንብረት ለውጡ እጅግም አስተዋጽኦ ሳታደርግ በመዘዙ የምትጠቃ ክፍለ ዓለም ናት። ጎርፍ እና ከባድ ዝናብ በአንድ ወገን በሌላው ወገን ጠንካራ ድርቅ ይፈታተናታል። የብዙዎችን ኑሮ ያናጋል። በሌላው ክፍለ ዓለም ደግሞ የሙቀት ወራትን ተከትሎ ሰደድ እሳቱ፤ የባሕር ማዕበሉ እና ወጀቡ ጠንቷል። የተመድ ዋና ፀሐፊ እኒህን ክስተቶች ለማጠየቅ ነው ዓለም ሲንቀራፈፍ የተፈጥሮ ቁጣው ፈጥኖ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ያመለከቱት። ኢትዮጵያ በዚህ ጉባኤ የምትሳተፍ ስትሆን በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ የሚገኙ 47 ሃገራት የተሰባሰቡት ቡድን መሪ እንደመሆኗ የቡድኑን አቋም የማንፀባረቅ ዕድል እንደምታገኝ የአካባቢ የደን እና የአየር ንብረት ኮሚሽን መግለጫ ያመለክታል። ትናንት የተጀመረው COP 24 እስከ ታሕሣስ አምስት ቀን 2011 ድረስ ይዘልቃል። ከጉባኤው የሚገኘው ፍሬም በመጪው ሳምንት ውስጥ የሚታይ ይሆናል።

ሸዋዬ ለገሠ 

ኂሩት መለሰ    


ተከታተሉን