1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአየር ንብረት ተስፋ በካንኩን

ማክሰኞ፣ መስከረም 25 2003

የአየር ንብረት ለዉጥን ለመታደግ የየአገራቱ መንግስታት ሊያደርጉ ይገባቸዋል፤ በሚል የሚጠበቀዉ ስምምነት ዘንድሮም እንደአምናዉ መጓተቱን ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/PVv5
የቻይና የአየር ንብረት ተሟጋቾችምስል AP

ባለፈዉ ከሁለት ዓመታት በላይ ዝግጅት ሲደረግበትና የየመገናኛ ብዙሃኑን ሰፊ ሽፋን ሲያገኝ ቆይቶ በመጨረሻ ዴንማርክ ኮፐንሃገን ላይ ሌላ ዉዝግብ ቀስቅሶ ካለዉጤት መጠናቀቁ አይዘነጋም። ሩቅ የመሰለዉ የዓመት ቀጠሮ የአንድ ወር እድሜ ሲቀረዉ፤ ለሜክስኮዉ የካንኩን ጉባኤም ይዞ የሚቀርበዉ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚመለከታቸዉን ወገኖች ማሳሰቡ አልቀረም። ትናንት በቻይና ሰሜናዊ ግዛት ቲያንጂን የተከፈተዉና ለስድስት ቀናት የሚዘልቀዉ የተመድ የአየር ንብረት ለዉጥን ለመግታት ያለመዉ ድርድርም ከካንኩን ጉባኤ አስቀድሞ በቀጣዩ ዉል ላይ የሚሰፍሩ አገራቱን የሚያስማሙ ነጥቦችን እንዲያወጣ ይጠበቅበታል። የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለዉጥ ተከታታይ ዘርፍ ዋና ጸሐፊ ክርስቲና ፊጎርስ ትናንት በስብሰባዉ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር አገራት ከህዳሩ የሜክስኮ ጉባኤ አስቀድመዉ የጋራ መግባቢያ ላይ እንዲደርሱ ነዉ ያሳሰቡት፤

«ካንኩን ከመሄዳችን በፊት ይህ የመጨረሻ የድርድር ወቅት ነዉ። አሁን ነዉ የጋራ መግባቢያችንን ላይ ለመድረስ መፋጠን የሚኖርብን። እንደምታዉቁት ከካንኩን ተጨባጭ የሆነ ዉጤት ባስቸኳይ ይፈለጋል።»

እንዲያም ሆኖ ግን ጉባኤ በተለያዩ ጉዳዮች ሰበብ ከታሰበዉ የሚደርስ አልመሰለም። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች እንደሚሉት፤ ለመግባባት እንቅፋት የሆኑት ለአየር ንብረት በሚል የሚመደበዉ ገንዘብ ላይ በድሃና በበለፀጉ አገራት መካከል የተፈጠረዉ አለመተማመን፤ በካይና አደገኛ ጋዞችን ለመቀነስ የሚሰነዘረዉ ሃሳብ ግልፅነት ማጣትና በኢንዱስትሪ ያደጉት አገራት እንቀንሳለን ሲሉ ያቀረቡት የብክለት መጠን የፈጠረዉ ቁጣ ነዉ። ባለፈዉ ዓመት ባለመሳካቱ ወደዘንድሮ በይደር የተንከባለለዉ በአዉሮጳዉያኑ 2012 የሚያበቃዉን የኪዮቶ ስምምነትን ይተካል ተብሎ የሚጠበቀዉ ዉል የየመንግስታቱን ፈቃደኝነት ይፈልጋል። እንደአምናዉ ሁሉ ዘንድሮም ወሳኝ ተብሎ የሚጠበቀዉ ጉባኤ አስተናጋጅ የሜክሲኮ ፕሬዝደንት በበኩላቸዉ ከዚህ ድርድር ከፍተኛ ዉጤት ይወጣል ብለዉ እንደማይጠብቁ በሚጠቁም አነጋገር፤ አገራት ቢያንስ በመጠኑ ሊያግባባቸዉ በሚችል ጉዳይ ቢስማሙ እንደሚበጅ ከወዲሁ ለቻይናዉ ጉባኤ አመልክተዋል። በካይ ጋዞችን ወደከባቢ አየር ከሚለቁት አገራት ዛሬ ግንባር ቀደም ደረጃን የያዘችዉ ቻይና የዚህ ጉባኤ አስተናጋጅ መሆን ምናልባትም ከዚህ ቀደም ከምዕራባዉያን አገራት ጋ በመፎካከር የያዘችዉን አቋም እንድታለዝብ ሊያደርጋት እንደሚችል ተገምቷል። ቻይና እስከ የአዉሮጳዉያን 2020ዓ,ም በ2005ዓ,ም የነበረዉን የበካይ ጋዞች ልቀት መጠን ከ40 እስከ 45በመቶ ዝቅ ለማድረግ ኮፐንሃገን ላይ ቃል ገብታለች። ያ የሚያመለክተዉ ከፍተኛ የኃይል አጠቃቀሟን መሆኑን የገመቱ ወገኖችም በቃሏ እጅግም አልተደሰቱም። የመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ጉዳይ ኃላፊዋ ቻይና በካይ ጋዞችን ለመቀነስ በሚደረገዉ ስምምነት ቤጂንግ አቋሟን እንድታለዝብ ጠይቀዋል። ዛሬም እንደአምናዉ በዚህ ረገድ ያላትን አቋም አገሪቱ እንድታለዝብ ሲጠየቅ የቻይና የአየር ንብረት ጉዳይ ባለስልጣን ዢ ሴንዋ በኮፐንሃገኑ ጉባኤ ላይ አገራቸዉ የገባችዉ ቃል በቂ ነዉ በሚል፤ በአዳጊ አገራት ሉዓላዊነት ጣልቃ መግባት አይገባም ሲሉ ተቃዉመዋል። ቻይና ከዚህ በፊትም የበካይ ጋዝ ልቀት መጠንና የሚያደርሰዉ ጉዳት እንዲለካ የሚለዉን ሃሳብ ሉዓላዊነት መዳፈር በሚል ስትቃወም ቆይታለች። የቻይና ሙግት የበለፀጉት አገራት ዛሬ ከደረሱበት የተገኙት በከባቢ አየር ላይ ዘመን ለተሻገረዉ ተፅዕኖ አስተዋፅኦ አድርገዉ ነዉ የሚል ሲሆን በካይ ጋዞችን ቅነሳ በሚል የማፈሰዉ ገንዘብና የማዉለዉ ጊዜ የጀመርኩትን የእድገት ርምጃ ያደናቅፋል ባይ ናት። ከዚህ በመነሳትም ለድርድሩ መፋጠንና ለስምምነቱ የበኩሌን አደርጋለሁ ብትልም፤ አሜሪካንና ሌሎች የበለፀጉ አገራት ወደከባቢ አየር የሚለቁትን በካይ ጋዝ ለመቀነስ ቀዳሚዎች እንዲሆኑና፤ ድሃ አገራትም ከአየር ንብረት ለዉጡ ጋ መኖር ይችሉ ዘንድ እንዲረዱ ጠይቃለች። እንዲያም ሆኖ የኮፐንሃገኑ ድርድር ከስምምነት ላለመድረሱ አሳድራለች በተባለችዉ ጫና ስትወቀስ የነበረችዉ ቻይና ለዘንድሮዉ የካንኩን የአየር ንብረት ጉባኤ የተሻሉ ጉዳዮችን ይዞ ለመቅረብ በዚህ ሳምንቱ ጉባኤ የመተባበር መንፈስ እንዳሳየች እየተነገረ ነዉ። 177 አገራትን የወከሉ ተሳታፊዎች ከትናንት የተገኙበት የቲያንጂኑ የአየር ንብረት ለዉጥ ድርድር በአዉሮጳዉያን 2011ዓ,ም ማለቂያ ገደማ ይጸድቃል ለሚባለዉ ቀጣይ የአየር ንብረት ለዉጥ መቆጣጠሪያ ዉል ያዋጣል ባሏቸዉ ነጥቦች ላይ ለመስማማት እንደሚጥሩ ይጠበቃል።

Yvo de Boer
የቀድሞዉ የተመድ የአየር ንብረት ኃላፊ ዩቮ ደቦር በኮፐንሃገኑ ጉባኤምስል AP

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ