1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአየር ጠባይ ለዉጥና ስደት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 17 2006

ሳይንቲስቶች ሳይቤሪያ በቅርቡት አደገኛ ጎርፍና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች በተደጋጋሚ ሊገጥማት እንደሚችል አመለከቱ። ባለሙያዎቹ እንደሚሉት እያደገ የመጣዉ የዓለም የሙቀት መጠን ያስከተለዉ ጎርፍም በተጠቀሰዉ አካባቢ ባለፈዉ እና በያዝነዉ ወር ከ50 ሺህ የሚበልጡ ሰዎችን ኑሮ አናግቷል።

https://p.dw.com/p/1CPRv
Bildergalerie Wilderei
ምስል Fotolia/st__iv

ይህ የተፈጥሮ አደጋ የደረሰዉ ከዚህ ቀደም ዓመት በማይሞላ ጊዜ ዉስጥ ሳይቤሪያን ያጥለቀለቀዉ ከባድ ጎርፍ ያስከተለዉ ጉዳት ገና ሳያገግም ነዉ። በዚህ ስፍራ ለሚደርሰዉ ጎርፍ ዋናዉ ምክንያት የሚቀልጠዉ የበረዶ ክምር መሆኑ በግንባር ቀደምትነት ቢገለጽም በቅርቡ የደረሰዉ የጎርፍ አደጋ ግን ከመጠን በላይ በሳይቤሪያ የተለያዩ ግዛቶች የወረደዉ ዝናብ መሆኑ ተነግሯል። የዓለም የሙቀት መጠን መጨሩን መቀጠሉም ተጨማሪ ጎርፍን ሊያከታትል እንደሚችል ይጠበቃል። ሳይቤሪያ የሚታወቀዉ እጅግ ጠንካራ በሆነዉ ቅዝቃዜዉ ነዉ፤ አብዛኛዉን ጊዜም የሙቀት መጠኑ ከዜሮ በታች አንዳንዴም እጅግ ይወርዳል። ሆኖም ባለፉት አስርት ዓመታት የተካሄዱ ጥናቶች የሚያመለክቱት በሳይቤሪያ አንዳንድ አካባቢ የሙቀት መጠኑ ከሌላዉ የዓለም ክፍል በበለጠ እየጨረ መሄዱን ነዉ። ሳይቤሪያ በበለጸገዉ የእዕፅዋት ብዝሃህይወትም ይታወቃል፤ የሙቀት መጠኑ መለወጥና መጨመሩ ታዲያ ከእዕፅዋቱ ሌላ እዚያ ብቻ የሚገኘዉን አሙር ታይገር ወይም የሳይቤሪያ ታይገር/ነብር/ ዝርያ ለአደጋ አጋልጧል። የአየር ንብረት መለወጥ እፅዋትና እንስሳትን ብቻ ሳይሆን ሰዎችንም ህይወት አጥፍቶ ኑሯቸዉን አናግቶ ለተለያየ ችግር ይዳርጋል።

Philippinen Taifun Haiyan 10.11.2013
ምስል Getty Images/Afp/Noel Celis

ስዊዛዊዉ የስታትስቲክስ ባለሙያ ቫልተር ኪሊን ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2008 እስከ 2011 ድረስ ባለዉ ጊዜ ብቻ የአየር ንብረት ለዉጥ ባስከተለዉ የተፈጥሮ አደጋ ከቤት ንብረታቸዉ የመፈናቀሉት ወገኖች 144ሚሊዮን እንደሚሆኑ ያመለክታሉ።እንደእሳቸዉ በየዓመቱም 29 ሚሊዮኖች ለዚህ ይዳረጋሉ። ይህን የዘረዘሩት ኪሊን ስደተኞችን በሚመለከተዉ የወጣዉ የጄኔቫዉ ስምምነት በተፈጥሮ አደጋዎች ለመፈናቀልና ስደት የሚዳረጉ ወገኖችም ከግምት እንዲያስገባ በአፅንኦት ነዉ የሚገልፁት። የእሳቸዉን ሃሳብም የጀርመኑ ቀይ መስቀል፣ ርሃብን ከዓለም ለማስወገድ የሚጥረዉ ድርጅት ቬልት ሁንገር ሂልፈ እና ማልቴዜር የተሰኘዉ ግብረ ሠናይ ድርጅቶች እዉነትነቱን ያረጋግጣሉ። ባለፉት ዓመታትም ሰብዓዊ ርዳታ የሚያስፈልጋቸዉ ወገኖች ቁጥር እጅግ ማሻቀቡ ነዉ የሚነገረዉ። የአየር ንብረት ለዉጥ በተለይ በአዳጊ ሃገራት ዉስጥ የሰዎችን የኑሮ ሁኔታ ለችግር ለመዳረግ እያሰጋ ነዉ።

ዛቢነ ኪንካርትዝ/ ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ