1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲሱ ህገመንግስት ተስፋ በዚምባቡዌ

ረቡዕ፣ መጋቢት 11 2005

አንዳንዶች እንደሚሉት የበርካቶችን ድጋፍ ባገኘዉ ህገመንግስት ምክንያትም ነገሮች ከእንግዲህ ለሙጋቤ እንደነበሩ የሚቀጥሉ አይመስሉም። ሌሎች ደግሞ ህገመንግስቱ የታሰበዉን ያህል ለዉጥ አያመጣም፤ ይልቁንም ዛሬም የፀጥታ ኃይሎች በተቃዋሚዎች ላይ የሚወስዱትን ርምጃ መገመት ያዳግታል ይላሉ።

https://p.dw.com/p/180uQ
ምስል Alexander Joe/AFP/Getty Images

የዚምባቡዌ የምርጫ ኮሚሽን በሳምንቱ ማለቂያ የተከናወነዉን የህዝበ ዉሳኔ ድምፅ ዉጤት ይፋ ሲያደርግ የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ባህር ማዶ ተሻግረዉ ነበር። አዲሱን ረቂቅ ህገመንግስት ከሶስት ሚሊዮን በላይ ህዝብ እንደደግፈዉ ወደ180 ሺህ የሚጠጋዉ ወገን ደግሞ እንደተቃወመዉ ይፋ ሲደረግ ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ በቫቲካን በተካሄደዉ የካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነጳጳሳት ፍራንሲስ በዓለ ሲመት ላይ ታድመዋል።

በአዲሱ ህገመንግስት መሠረት ከእንግዲህ ፕሬዝደንት ሮበርት ሙጋቤ የክፍላተ ሀገራትን ገዢዎች ብቻቸዉን ለመሾም አይችሉም። እሳቸዉም ቢሆኑ ከእንግዲህ ካንዴ በቀር መመረጥ አይችሉም፤ ፓርላማዉንም ብቻቸዉን ሊበትኑ አይችሉም። ህገመንግስቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የዜጎችን መሠረታዊ መብትም አረጋግጧል እየተባለለት ነዉ።

Papst Franziskus Amtseinführung
ሮበርት ሙጋቤ በቫቲካንምስል Reuters

ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የኮንራድ አደናወር ተቋም ኃላፊ ዩርገን ላንገን እንደሚሉት አዲሱ ህገመንግስት ዚምባቢዌ ለተሻለ ዴሞክራሲ በምታደርገዉ ጥረት ቀላል የማይባል ርምጃ ነዉ። ጠቅላይ ሚኒስትር ሞርጋን ቻንጊራይም በበኩላቸዉ የዚምባቡዌ የዴሞክራሲ ትግል ልጅ ነዉ ብለዉታል፤

«አዲሱ ህገመንግስት ዚምባብዌ ዉስጥ ለዴሞክራሲ የሚደረገዉ ትግል ልጅ ነዉ። ይህ ህገመንግስት የተባበረዉ የዚምባቡዌ ህዝብ ልጅ በመሆኑ ምክንያትም ቻርተሩን ለመጣስ የሚደረግ ማንኛዉም አመፅና ርምጃ ጭቅላ ህፃን እንደማጥፋት ስለሚቆጠር በዝምታ የሚታለፍና የሚታገሱት አይሆንም።»

ባለፈዉ ቅዳሜ በረቂቁ ህገመንግስት ላይ የተካሄደዉ ህዝበ ዉሳኔ በሀገሪቱ ባልተለመደ መልኩ የተረጋጋ መሆኑ ሲገለፅ በቅርበት ለመታዘብ እድሉ የተሰጣቸዉ ወገኖች ነፃና ፍትሃዊ ነበር ብለዉታል። በዚምባቡዌ የአዉሮጳ ኅብረት ምክትል አምባሳደር ካርል ስካዉ አፍሪቃዊቱ ሀገር ህዝበ ዉሳኔዉን ያካሄደችበትን መንገድ ኅብረቱ ማድነቁን ገልፀዋል።

«የህዝበ ዉሳኔዉ ሂደት በሁሉም መለኪያዎች የተረጋጋና የሰከነ ነበር። ህገመንግስታዊዉን ሂደት ለማጠናቀቅም ይህ ወሳኝ ርምጃ ከመሆኑ በተጨማሪ በሚቀጥለዉ ዓመት ለሚካሄደዉ ምርጫ መንገድ ይጠርጋል ብለን እናስባለን።»

አዲሱ የዚምባቡዌ ህገመንግስት የሀገሪቱን ገፅታ የሚያሻሽል ይመስላል። ስካዉ እንደጠቆሙትም የአዉሮጳ ኅብረት የፊታችን ዓርብ ዕለት በዚህች ሀገር ላይ የጣለዉን ማዕቀብ ዳግም ለማጤን ተዘጋጅቷል። በጎርጎሮሳዊዉ 2002ዓ,ም ነዉ የአዉሮጳ ኅብረት ዚምባቡዌ ላይ ማዕቀብ የጣለዉ። ማዕቀቡ ካካተታቸዉ መካከል ፕሬዝደንት ሙጋቤን ጨምሮ አንድ መቶ ሰዎች ወደአዉሮጳ ኅብረት ሀገሮች እንዳይገቡ፤ በባንክ የሚገኝ ንብረታቸዉ እንዳይንቀሳቀስ፤ እንዲሁም ዚምባቡዌ የጦር መሣሪያም እንዳታስገባ ማገዱ ይጠቀሳሉ።

«የአዉሮጳ ኅብረት በየካቲት ወር ካሳለፈዉ ዉሳኔ ጋ በተጓዳኝም ባፋጣኝ በግለሰቦችና በተቋማት ላይ ኅብረቱ ከጣለዉ ገደብ የቀሩትን ለማንሳት ፖሊሲዉን ለመፈተሽ ዝግጁ ነዉ።»

እንዲያም ሆኖ አዲሱ ህገመንግስት የሚያመጣዉ ለዉጥ የለም የሚል ስጋታቸዉን ነዉ ስማቸዉ እንዳይጠቀስ ያሳሰቡ የሀገሪቱ የሲቪል ማኅበረሰብ አባል ያሰሙት። እሳቸዉ እንደሚሉት የሀገሪቱ ፀጥታ ኃይሎች በቀጣይ ስለሚወስዱት ርምጃ መገመት ይከብዳል። ህዝበ ዉሳኔዉ በተካሄደ ማግስት የጠቅላይ ሚኒስትር ሻንግራይን የሥራ ባልደረቦች ታስረዋል። ጠበቃቸዉም እስር ቤት እንደሚገኙ እስር ቤት ነዉ። ከህዝበ ዉሳኔዉ አስቀድሞ ፖሊስ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለኅብረተሰቡ ሊያከፋልሉ የነበረዉን ራዲዮ በመያዙ ግንባር ቀደም የዜና ርዕስ ሆኖ ነዉ የሰነበተዉ። እስካሁንም የፀጥታ ኃይሎች ህጉን ወደጎን በመተዉ ለፕሬዝደንት ሙጋቤና ለZANU-PF ፓርቲያቸዉ ዘብ እንደቆሙ ነዉ። የፖሊስ አዛዡ አዉጉስቲን ቺሁሪ በሥራቸዉ ስለሚገኙት ሲገልፁ፤ የፕሬዝደንቱ ደጋፊዎች ብቻ በእሳቸዉ ሠራዊት ዉስጥ ስፍራ እንደሚኖራቸዉ አመልክተዋል። አሁን ትኩረትን የሳበዉ አዲሱ ህገመንግስት በመጪዉ ምርጫ ቅስቀሳ ላይ ሊኖረዉ የሚችለዉ አዎንታዊ ሚና ነዉ። እስከሚቀጥለዉ ዓመት ጥቅምት ድረስ ዚምባቡዌ ምክር ቤታዊና ፕሬዝደንታዊ ምርጫዋን ታካሂዳለች። የኮንራድ አወር ተቋም ባልደረባ ዩርገን ላንገን ፕሬዝደንት ሙጋቤና ጠ/ሚ ሻንጊራይ ተዓማኒ የሆነ የድምፅ አሰጣጥ እንዲኖር ይፈልጋሉ የሚል እምነት ነዉ ያላቸዉ። ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ደግሞ በሁለት ፍላጎት ብቻ የሚወሰን ሳይሆን በሀገሪቱ የስልጣን ኃይል አሰላለፍ በሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ የሚገኙትን የፀጥት ኃይሉን ጨምሮ ትብብር ይጠይቃል። በተለይ የሻንጊራይ ባልደረቦች ከታሰሩ በኋላ አዲሱ ህገመንግስት ቢኖርም በተቃዋሚዎችና በሲቪክ ማኅበራት ላይ የሚደረገዉ ጫና አለማባራቱ በበርካቶች ላይ ስጋት አሳድሯል።

Morgan Tsvangirai Simbabwe
ሞርጋን ሻንጊራይምስል AFP/Getty Images

ዳንኤል ፔልስ

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ