1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ንግግርና የምሁራን አስተያየት

ማክሰኞ፣ መጋቢት 25 2010

ያለፈዉ ሳምንት  መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ/ም የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነዉ የተመረጡት ዶክተር አብይ አህመድ በትናንትናዉ  ዕለት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነዉ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሰይመዋል። በዚህ በዓለ ሲመት ላይ ዶክተር አብይ ያደረጉት ንግግር በይዘቱና በአቀራረቡ ከዚህ ቀደም ያልተለመደ ነዉ በሚል ብዙዎችን ማነጋገሩ ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/2vQix
Äthiopien Vereidigung Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture alliance/AP Photo/M. Ayene

Intellectuals Opinion About New PM's Speech - MP3-Stereo


የጠቅላይ ሚንስትርነት ስልጣናቸዉን በፈቃዳቸዉ በለቀቁት በአቶ ኀይለማርያም ደሳለኝና  በዶክተር አብይ አህመድ መካከል  ህገ-መንግስቱ በሚፈቅደዉ መሰረት በትናንትናዉ ዕለት ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር መካሄዱ  በብዙዎች ዘንድ አድናቆት የተቸረዉን ያህል ፤የአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ንግግርም የብርካቶችን ትኩረት ስቧል። ምንም እንኳ የስልጣን ሽግግሩ በኢህአዴግ መካከል፤ ተመራጩም ከዚሁ ድርጅት የወጡ ቢሆንም ፤በሀገሪቱ  የተለያዩ አካባቢዎች ከተቀሰቀሰዉ  ተቃዉሞ እንቅስቃሴ አንፃር  ብዙዎች አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር  በመጀመሪያው ቀን ካሰሙት የመግቢያ ንግግር ጀምሮ ተስፋ ጥለዉባቸዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችና በግል ጋዜጦች የሰላ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ትችቶችን በመጻፍ የሚታወቁትና በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የስነልሳን መመህር የሆኑት ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ከእነዚህ መካከል አንዱ ናቸዉ። እሳቸዉ እንደሚሉት ዶክተር አብይ  ከዚህ ቀደም ካደረጓቸዉ ንግግሮችና ከሀገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ በመነሳት ንግግራቸዉ አወንታዊ እንደሚሆን ጠብቀዉ ነበር።
«እንደጠበኩት ነዉ ያገኜሁት ቢያንስ ከዚህ በኋላ ህዝብ የሚፈርጅ አሸባሪ ፣ፀረ-ልማት የሚሉ ነገሮች እንደማንሰማ መገመት እንደሚቻል ከሳምንት በፊት ፅፌ ነበር። በጠበኩት መንገድ ነዉ ያገኘሁት።»

የአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ንግግር በእዉነትና በእዉቀት ላይ የተመሰረተ ነበር ያሉት ደክተር በድሉ፤ ያ መሆኑ  ወደፊት በአግባቡ በስራ ይተረጎማል የሚል እምነት አሳድሮብኛል ይላሉ። ጠቅላይ ሚንስትሩ ከኢህአዴግ ስለወጡ ለዉጥ አያመጡም  የሚሉ አስተያየቶች ቢኖሩም እንደማይቀበሏቸዉ በምክንያት ያብራራሉ።  
«የወጡት ከኢህአዴግ ስለሆነ ብዙ ለዉጥ አያመጡም የሚሉ ሰዎች አሉ።እኔ ግን የምለዉ የመጡበት መንገድ ይናገራል።የወጡበት መንገድ ብዙ ይናገራል ።ላለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ሀገራችን ዉስጥ ሰላም የለም።በየ ቦታዉ ሰዎች እየሞቱ ነዉ።ወጣቶች ነፃነትና ዴሞክራሲ እየጠየቁ ነዉ።በዚህ የተነሳ እነዚህ አመራሮች በተለይ የኦህዴድ አመራሮች የህዝብ ጥያቄ ይዘዉ ከህዝብ ጋር ወግነዉ የራሳቸዉን ድርጅት ወጥረዉ የያዙበት ጊዜ ነዉ የነበር።»
በአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ንግግር ዉስጥ የተገለፀዉ ኢትዮጵያዊነት፤ አንድነትና  የህዝቦቿ ታሪክ በይዘቱና በአቀራረቡ አሁን ቀደም ከሰሟቸዉ የፖለቲካ ንግግሮች የተለየ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ  በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የታሪክና የስነ ጥበብ ታሪክ መመህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር  አበባዉ አያሌዉ ናቸዉ።
«ይዘት ላይ ትልቅ ለዉጥ አለ ነዉ የምለዉ።ከታሪክ ተነስተዉ ከዚህ በፊት ብዙ ትዉልዶች የከፈሉትን  መሰዋዕትነት መሰረት አድርገዉ አንድነትን ማቀንቀናቸዉ ይሄ ትልቅ የይዘት ልዩነት ነዉ ብዬ አምናለሁ።ሁለተኛዉ ደግሞ ኢትዮጵያ ብዙ የፖለቲካ ዉጣ ዉረዶችን አልፋለች እና ከንግግራቸዉ መጀመሪያ አካባቢ ያሉት ምንድነዉ ።ብዙ በጎ አጋጣሚወችን አምልጠዉናል በአግባቡ ሳንጠቀምባቸዉ ወደ ዲሞክራሲ ለመጓዝ ።እነዛን ያባከናቸዉን እድሎች አሁን እንጠቀም ነዉ ያሉት።ይሄም ትልቅ የይዘት ለዉጥ ነዉ ብዬ አምናለሁ።»
እንደ አቶ አበባዉ ዶክተር አብይ  በንግግራቸዉ የተጠቀሙበት ቀላል ሰዉኛና  አወንታዊ  ቃላትም መቀራረብን የሚጋብዝ ነዉ።በዉጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንና ለተፎካካሪ ፓርቲወች ያቀረቡት የተባብረን እንስራ ጥሪም  ከጠበቁት በላይ መሆኑን ነዉ የተናገሩት። 
የሴቶችን  እኩል ተጠቃሚነት እንዲሁም እዉቅና በተመለከተ እስካሁን ተነግሮ የማያዉቀዉንና  ፖለቲካዉ በደንብ ያላየዉን   ሴቶች ትዉልድ ከመቅረፅ አንፃር ያላቸዉን የማይተካ  ሚና በእናትና በባሌቤታቸዉ አማካኝነት የገለፁበት መንገድም ለአቶ አበባዉ የተለየና ስሜት የሚነካ ነበር።
«የሴቶች አስተዋፅኦ በተለይ ሰዉን ከመቅረፅ ትዉልድን ከማነፅ አንፃር ጥሩ ዜጋ ከማፍራት አኳያ ከቤተሰብ ጀምሮ የሚጫወቱት በእናትነትም በሚስትነትም የሚጫወቱት ሚና ሲያጎሉት ዝም ብሎ ሴት የፓርላማ ተወካዮች ቁጥር መጨመር፣ሴት አስተዳደሮች ፣ ከንቲባወችና ስራ አስፈፃሚወች መበራከትና እነሱን ማሳተፍ የተለመደ የፖለቲካ «አክሮባት» ነዉ ያሉት አቶ አበባዉ ።እሳቸዉ በተናገሩት መንገድ ግን የሴቶች አስተዋፅኦ ለሁሉም ይገባል።እንዲያዉም እኔ ንግግሩን በተከታተልኩበት ካፌ አስተናጋጁም ሁሉም ያለቀሰ በዚህ ንግግር ነዉ።ምክንያቱም ልብ የሚነካ ትልቅ ንግግር ነዉ።» 
ጠቅላይ ሚንስር ዶክተር አብይ አህመድ ከንግግራቸዉ ባለፈ  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋትና በእኩል የሀብት ተጠቃሚነት ላይ በርትተዉ በመስራት የተናገሩትን ወደተግባር እንዲቀይሩ  ሙህራኑ  ጨምረዉ አመልክተዋል።

Äthiopien Vereidigung Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/AA/M. W. Hailu
Äthiopien Vereidigung Premierminister Abiy Ahmed
ምስል picture-alliance/AA/M. W. Hailu

 

ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ