1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲሱ 2014ዓ,ም የመሪዎች መልዕክት

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 23 2006

ጎርጎሪዮሳዊዉን የዘመን ቀመር የሚከተለዉ ዓለም አዲሱን 2014ዓ,ም ዛሬ አንድ ብሏል።

https://p.dw.com/p/1Ak7H
ምስል Getty Images

የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ በመጀመሪያዉ የዘመን መለወጫ ንግግራቸዉ ዓለም ጠንካራ ትብብር እንደሚያስፈልጋት አመልክተዋል። ዛሬ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ዓለም እርስ በእርሱ የሚከባበር እና ልዩነቶችን ተቀብሎ አንዱ ለሌላዉ የሚያስብ ማኅበረሰብ እንዲኖረዉ የማድረጉ ኃላፊነት የሁሉም መሆኑን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አሳስበዋል። የብሪታንያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካምሮን በበኩላቸዉ በአዲስ ዓመት መልዕክታቸዉ ስኮትላንዶች ከብሪታንያ እንዳይነጠሉ ተማፅነዋል።

Papst Franziskus Neujahrsansprache Predigt Petersdom
ምስል FILIPPO MONTEFORTE/AFP/Getty Images

የዘንድሮዉ መልዕት ከኢንግላንድ፣ ዌልስና ሰሜን አየርላንድ ወደስኮትላንድ ይድረስ ያሉት ካምሮን፤ ስኮቲሾችን ከእኛ ጋ እንድትሆኑ እንፈልጋለን፤ በጋራ ጠንካራዋን የተባበረች መንግስት ለልጆችና ለልጅ ልጆቻችን እናዉርስ የሚል ጥሪያቸዉን አስተላልፈዋል። ስኮትላንዶች በመጪዉ መስከረም ወር ለ300ዓመታት ከብሪታኒያ ጋ አንድ ሆነዉ የቆዩበትን ታሪክ በህዝበ ዉሳኔ ሊያከትሙ እንደሚችሉ ይጠበቃል። የጋምቢያ ፕሬዝደንት ያህያ ጃማህ ደግሞ ታግደዉ የቆዩ አንድ ጋዜጠና የራዲዮ ጣቢያ ዳግም ሥራ እንዲቀጥሉ ፈቅደዋል። የፕሬዝደንቱ ርምጃ ለአዲሱ ዓመት የበጎ ሃሳብ መገለጫ በሚል ተወድሷል። የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በአዲሱ ዓመት ንግግራቸዉ ወጣቶች የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ ጥረት እንደሚደረግ አመልክተዋል፤

ACHTUNG SPERRFRIST Angela Merkel Neujahrsansprache 30.12.2013
ምስል David Gannon/AFP/Getty Images

«በተለይ ለእኔ አስፈላጊዉ ጉዳይ፤ ለቀጣዩ ትዉልድ የምናስረክበዉ የተቀናጀ የፋይናንስና የኃይል ዘርፉን ለዉጥ አሳክተን በሀገራችን ጥሩ ሠርተን እና በህብረት መልካም ኑሮ መኖር መቻላችን ነዉ። ምክንያቱም ማኅበረሰባችን እያረጀና ይበልጥም እየተቀየጠ በመምጣቱ፤ የኅብረተሰባችን ማዕከሎች ናቸዉና የቤተሰብ ደጋፊዎች እንፈልጋለን። ስለዚህም ልጆችና ወጣቶች ምርጥ የተባለዉን ትምህርት ቀስመዉ የተሻለ ኑሮ መምራት እንዲችሉ እንሻለን።»

ከዚህም ሌላ ሜርክል እያንዳንዱ ዜጋ ስላለበት ኃላፊነት፤ ማኅበራዊ ተሳትፎና ችግር ከደረሰባቸዉና ከተበደሉ ጎን መቆም እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ