1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲስ አበባ የቤት ኪራይ ችግር

ሰኞ፣ የካቲት 11 2011

የቤት ኪራይ ችግር ዛሬም እንዳልተፈታ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ይናገራሉ። የቤት ኪራይ ዋጋው መናሩም ገቢያቸውን ያላገናዘበ እየሆነ ይገልጻሉ።  

https://p.dw.com/p/3DblU
Blick aus meinem Fenster Addis Abeba Äthiopien
ምስል Solomon Mengist


በኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ የቤት ኪራይ ችግር ዛሬም አልተቀረፈ፤ እንደውም ብሶታል፤ እንደ ነዋሪዎቿ አስተያየት። በመዲናዋ መኖር ከጀመሩ ሊያስጨንቅዎት የሚችለው ዋነኛው የመኖሪያ ነገር እንደሆነም ብዙዎች ይናገራ። የሚከራይ ቤት በመፈለግ መንገላታቱ፤  «አከራዮች ከዛሬ ነገ ምን ይሉኝ» የሚለውን ስጋት ችለው የተቀመጡ ተከራዩችም ቤቱ ይቁጠራቸው ሲሉም ያማርራሉ። አከራዮች የቤት ኪራይ ዋጋ ሲጨምሩ ምንም አያገናዝቡም ይላሉ አቶ እስክንድር መለሰ። የጋራ መኖሪያ ቤቶች መገንባትም ለጥቂት ሰዎች ብቻ መጠቀሚያ እንደሆነ ያመለከቱ ሌላው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው፤ ህዝቡ በራሱ አቅም ቤት የሚሠራበት ዕድል እንዳልተመቻቸ ይናገራሉ፤
ባለሁለት ክፍል ስድስት ቤቶችን ያከራዩት አቶ ሳሙኤል ለማ ያከራዩዋቸው ግለሰቦች በትንሹ ከአራት ዓመታት እስከ ዘጠኝ ዓመታት እዚያው ኖረዋል ባይ ናቸው። ሆኖም ተከራዮች ቤቱን እንደቤታቸው ያለማየት ችግር እንዳለ ይጠቅሳሉ። ዶ/ር የራስወርቅ አስማቴ በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ለረጅም ጊዜ በማስተማር ቆይተዋል። መንግሥት ባሠራቸውም የግል መኖሪያ ቤቶች ጨምሮ ምንም አይነት የኪራይ ዋጋ ቁጥጥር እንደሌለ ነው የሚናገሩት። በዚያም ላይ መንግሥት በግል መኖሪያ ቤቶች ምንም ቁጥጥር እንደማያደርግ ጠቅሰው ሆኖም ግን በሌላ ወገን ቁጥጥሩ መኖር የለበትም ብለው የሚከራከሩም እንዳሉ ዶ/ር የራስወርቅ ያመለክታሉ። በግንባታ ላይ ያሉትም በመንግሥት የሚገነቡ የግል መኖሪያ ቤቶች ሥራም እየተጓተተ እንደሆነ ያስረዳሉ።
የከተማ አስተዳደሩ በሥሩ የሚያስተዳድራቸውን የቀበሌ ቤቶች ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍል ለማስተላለፍ እየሠራ እንዳለ ኢንጅነር ሰናይት ዳምጠው የአዲስ አበባ ቤቶች ኤጀንሲ ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ለ«DW» ገልጸዋል። በከተማዋ ያለውን የቤት ኪራይ መቀነስ እንዲቻል ሪል ስቴቶች አጋዥ መሆናቸውን በማመልከትም፤ ለረጅም ዓመታት ያልገነቡ ጥቂት የማይባሉ የቤት ግንባታ ድርጅቶች ላይም የከተማ አስተዳደሩ እርምጃ እየወሰደ እንደሆነም በቃለ መጠይቁ ወቅት ዘርዝረዋል። በ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች 40 በመቶ የቆጠቡ በዕጣ እንደሚካተቱም ጠቅሰዋል። ኅብረተሰቡ እንደየአቅሙ የሚጠቀምበት የቤት ግንባታ መርሃግብርም በተቻለ መጠን ሁሉንም እንዲያዳርስ እንደሚደረግም ኃላፊዋ ገልጸዋል።

ነጃት ዚብራሂም

 

ሸዋዬ ለገሰ