1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር ሀዲድ ግንባታ ፕሮዤ

ረቡዕ፣ መጋቢት 4 2005

ሁለት የቻይናውያን ኩባንያዎች አዲስ አበባን ከጅቡቲ ጋ የሚያገናኝ የባቡር ሀዲድ ስራ መጀመራቸውን የፈረንሣይ ዜና ወኪል ያወጣው ዘገባ ገለጸ። የባቡር ሀዲዱ ቀድሞ በፈረንሣውያን የተሰራውን የባቡር መስመር የሚተካ ይሆናል።

https://p.dw.com/p/17vh8
ምስል DW


የቻይናውያን ኩባንያዎች አሁን የሚገነቡት ይኸው ወደ 800 ኪሎሜትር የሚጠጋው የባቡር ሀዲድ መስመር ኢትዮጵያ የጀመረችው የዕድገትና ለውጥ መርሀግብርዋ ከፊል መሆኑ ተገልጾዋል።
ኢትዮጵያ በዚሁ አሁን በአጋማሽ በሚገኘው በዋና ዋና ዘርፎች ላይ ከዕቅድ በታች  ውጤት ባስገኘው የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ለውጥ መርሀግብሯ በቻይና እና በቱርክ ኩባንያዎች የሚሰሩ ስምንት የተለያዩ 4,744 ኪሎሜትር ርዝመት የሚኖራቸው በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ ባቡሮች የሚሽከረከሩባቸው የባቡር ሀዲዶች ለመገንባት ዕቅድ ይዛለች። ይኸው የባቡር ሀዲድ ግንባታ ፕሮዤ እአአ በ 2025 ዓም ራሷን ወደ መካከለኛ ገቢ ሀገር ለማሳደግ የያዘችውን ዕቅዷን ለማሳካት እንደሚረዳት የፈረንሣይ ዜና ወኪል ያወጣው ዘገባ አስታውቋል። በድሬዳዋ የሚገኝ  ኮስታ የተባለ አንድ የኢጣልያውያን ኩባንያ ከቀድሞው ፈረንሣይ ከሰራችው የባቡር ሀዲድ መካከል አንድ መቶ አርባ ኪሎሜትሩን እንዲያድስ ከአምስት ዓመት በፊት የተሰጠው በአውሮጳ ህብረት ርዳታ የተነቃቃው ኮንትራት ባንድ በኩል እና የኢትዮጵያና የጅቡቲን ምድር ባቡር ኩባንያን እአአ በ 2006 ዓም ወደ ግሉ እጅ ለማዞር ከአንድ የደቡብ አፍሪቃ ኩባንያ ጋ የተደረገው ሙከራ በሌላ ወገን ከከሸፈ በኋላ የተቋቋመው የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ግዙፉ የባቡር ሀዲድ ግንባታ ፕሮዤ ለምዕራባውያን ሳይሆን ለቻይና፡ ለቱርክ ሰጥቶዋል፤ ለዚህም ምክንያቱ፡ ይላሉ ስለ ኢትዮጵያና ጅቡቲ የባቡር ሀዲድ ታሪክ ከጥቂት ጊዜ በፊት አንድ መጽሐፍ ያሳተሙት ፈረንሣዊው ደራሲ ኢውግ ፎንቴን።
« ኢትዮጵያ  ፊትዋን አሁን ወደ አዳዲስ ባለሀብቶች ያዞረችው በንዲህ ዓይነቱ ግዙፍ እና ውድ ፕሮዤ ላይ ገንዘባባቸውን ለማሰራት የሚፈልጉት የቻይና፡ የቱርክ እና የሕንድ ኩባንያዎች እንጂ የምዕራባውያት ኩባንያዎች ባለመሆናቸው ነው። »

የቻይናውያኑ ኩባንያዎች ከአዲስ አበባ እስከ መኢሶ፡ ከመኢሶ እስከ ጅቡቲ የሚገነቡት ወደ 800 ኪሎሜትር ገደማ ርዝመት የሚኖራቸው የባቡር ሀዲዶች ወደ ሦስት ነጥብ ሁለት ዩኤስ ዶላር የሚፈጅ ሲሆን፡ ይኸው ግዙፍ ፕሮዤ እንደታቀደው እአአ እስከ 2016 ዓም መጠናቀቁ ብዙዎችን የሚያነጋግር ጉዳይ ሆኖዋል፤ ይሁንና፡ ኢውግ ፎንቴን ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ወደብ ጋ የሚያገናኘውን የሀዲድ ግንባታ ፕሮዤ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ጠንክራ መስራቷ አይቀርም የሚል ግምት እንዳላቸው ገልጸዋል።
« ሁኔታዎች የተለወጡ ይመስለኛል። በተለይ ፡ ከደቡብ አፍሪቃው ኩባንያ ጋ የተደረገው የኢትዮጵያና የጅቡቲን ምድር ባቡር ኩባንያን ወደ ግሉ ይዞታ ለማዛወር የተደረገው ከከሸፈ ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህንኑ የበቡር ሀዲድ ለማሻሻል ወስኖዋል። እርግጥ ፡ የወጪው ጉዳይ፡ በጣም ውድ እንደመሆኑ መጠን  የሚያጠያይቅ ነው። ግን በኢትዮጵያ አሁን፡ በኤሌክትሪኩ እና በመንገድ ግንባታው ላይ እያነው ያለው ልማት የባቡሩ ሀዲድ ግንባታ፡ ምንም እንኳን ውድ ቢሆንም፡ የፖለቲካው ፍላጎት በመኖሩ፡ ያለኝ መረጃ ትክክለኛው ከሆነ፡ ቢያንስ፡ ዋናው መስመር፡ ማለትም፡ አሁን በግንባታ ላይ ይገኛል የሚባለው የጅቡቲ አዲስ አበባ መስመር በጥቂት ዓመታት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አምናለሁ »
በድሮው ፈረንሣውያኑ በሰሩት የጅቡቲ አዲስ አበባ የባቡር ሀዲድ መስመር አካባቢ አልፎ አልፎ የዓማፅያን ቡድኖች ጥቃት መጣላቸው የሚታወስ ቢሆንም፡ ኢውግ ፎንቴን እንደሚገምቱት፡  አዲሱ የባቡር ሀዲድ ግንባታ ላይ ተመሳሳይ የፀጥታ ችግር ስጋት አይኖርም።
« በአዲስ አበባ እና በጅቡቲ መስመር መካከል ዓቢይ የፅጥታ ችግር ያለ አይመስለኝም። እርግጥ፡ የድሬዳዋ አካባቢ አማካኝ የተለያዩ ብሔረሰቦች መተላለፊያ አማካይ ቦታ ነው። ይህ አንዳንዴ ውጥረት ሊፈጥር ይችል ይሆናል። ችግር ሊኖር ይችላል ከተባለ በሶማልያ ከበርበራ ወደብ ጋ እንዲያገናኝ የታሰበው የባቡር ሀዲድ ፕሮዤ ይሆናል። እንደሚታወቀው ጅቡቲ ከአሥራ ዘጠነኛው ምዕተ ዓመት ማብቂያ ወዲህ ለኢትዮጵያ አገልግሎት የምትሰጥ ወደብ ናት። እና ወደ በርበራ የባቡር ሀዲድ የመዘርጋቱ አዲስ ሀሳብ በፀጥታ ችግር ገሀድ ሊሆን የሚችል አይመስለኝም። »

Hafen von Dschibuti Arbeiter
ምስል AP
Stadtansicht von Dschibuti in Äthiopien
ምስል picture-alliance/ dpa

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ